የዋልያዎቹ አሰልጣኝ እና አምበል ከጨዋታው በፊት መግለጫ ሰጥተዋል

ብሔራዊ ቡድኑ ስላለበት ወቅታዊ ሁኔታ እና ተያያዥ ጉዳዮች የተሰጠው መግለጫ ይህን መሳይ ነበር።

ወደ ካሜሩኑ የ2022 የአፍሪካ ዋንጫ ለመጓዝ ከሚረዱት ሁለት ጨዋታዎች የመጀመሪያውን ነገ 10፡00 ላይ የሚያከናውነው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን የመጨረሻ ልምምዱን አከናውኖ ለፍልሚያው ዝግጁ ሆኗል። ከዚያ በፊት ግን የቡድኑ አለቃ አሰልጣኝ ውበቱ አባተ እና አምበሉ ጌታነህ ከበደ በባህር ዳሩ ብሉናይል (አቫንቲ) ሆቴል የእስካሁኑን ዝግጅት ፣ የወዳጅነት ጨዋታውን እና የቡድኑን ወቅታዊ ሁኔታ በተመለከቱ ጉዳዮች ላይ ያጠነጠነ ቆይታን በስፍራው ከነበሩ ጋዜጠኞች ጋር አድርገዋል።

በመድረኩ ቀዳሚ ተናጋሪ የነበሩት አሰልጣኝ ውበቱ አባተ ቡድኑን ከኒጀሩ ጨዋታ ጀምሮ ሲያዘጋጁ መቆየታቸውን እና በደርሶ መልሱ ጨዋታ የነበሩትን ተግዳሮቶች ከግምት በማስገባት የቀጣዮቹን ጨዋታዎች አቅጣጫ የሚጠቁም 109 ገፆች ያሉት ሪፖርት አዘጋጅተው ለፌዴሬሽኑ በማቅረብ ከዘንድሮው ውድድር አካሄድ አንፃር በተለያዩ ምዕራፎች በሚገኙ ክፍተቶች ቡድኑን ሲያዘጋጁ እንደቆዩ በመግለፅ ማብራሪያቸውን ጀምረዋል።

አሰልጣኙ የጠቀሷቸውን የዝግጅት ጊዜያት በዝርዝር ባነሱበት ንግግርም “ጅማ ላይ ለ 28 ተጫዋቾች ጥሪ አድርገን የተወሰኑት ባይገኙም የሦስት ቀን ዝግጅት አድርገናል። በመቀጠል ሊጉ ከጅማ ወደ ባህር ዳር ሲሸጋገር ከነበረው የ14 ቀን ክፍተት ውስጥ 6ቱን ለብሔራዊ በድን ዝግጅት በመውሰድ አዲስ አበባ ላይ ተዘጋጅተናል። በሁለቱ ወቅቶች በሥነ-ልቦና እና በታክቲክ ሥራዎች ላይ ሁለገብ የሆነ ዝግጅት አድርገናል። በዚህም ዝግጅት ላይ የተወሰኑ ተጫዋቾች ባለመገኘታቸው ሙሉ ነበር ማለት አይቻልም። ከሞላ ጎደል ግን የሚያስፈልጉ ነገሮችን ሰርተናል። በሦስተኛው ምዕራፍ ደግሞ ከመጋቢት 4 አንስቶ በባህር ዳር በቀን አንድ ጊዜ በሜዳ ላይ በክፍል ውስጥ ደግሞ ከሥነ-ልቦና ጋር የሚያያዙ ፣ ከታክቲክ ጋር የሚያያዙ ዝግጅቶችን ስንሰራ ቆይተናል።” ብለዋል።

በመቀጠል አሰልጣኙ በመጨረሻው የዝግጅት ምዕራፍ ላይ አብዱልከሪም ወርቁ እና አማኑኤል ዮሀንስ በቅርብ ደግሞ መናፍ ዐወልን በጉዳት አጥተው ይሁን እንዳሻው ፣ ወንድሜነህ ደረጄ እና መሳይ ጳውሎስን ተተክተው በ 25 ተጫዋቾች ልምምዳቸውን እንደቀጠሉ እና እነዚህ ተጫዋቾችም አሁን ላይ በሙሉ ጤንነት ላይ እንደሚገኙ አንስተዋል።

ከማላዊ ብሔራዊ ቡድን ጋር በነበረው ጨዋታ 70% የሚሆነው ስብስብ ተጠቅመው ጥሩ ተሞክሮ ማግኘታቸውን በማንሳትም በነገ ተጋጣሚያቸው ዙሪያ ስላደረጉት መሰናዶ ይህንን ብለዋል። “ለጨዋታው በሁሉም ረገድ ዝግጁ ነን። ተጋጣሚያችንን ማዕከል ያደረገ አቀራረብ እንዲኖረን መረጃዎችን ለመሰብሰብ ሰፊ ጥረት አድርገናል። ከኮቪድ ጋር በተያያዘ በፈረንሳይ ሊግ የሚጫወቱ ተጫዋቾቻቸው ቡድኑን አይቀላቀሉም ተብሎ የነበረ ቢሆንም በሀገሪቱ መንግሥት እና በፌዴሬሽናቸው ጥረት ሁሉም ተጫዋቾች በቻርተርድ አውሮፕላን ቡድኑን መቀላቀላቸውን አውቀናል። ሜሪ እና ሪያን የሚባሉ ሁለት ተጫዋቾች ብቻ በኮቪድ ኬዝ እንደማይገኙ ነው መረጃው ያለን። ተጋጣሚያችን በሙሉ ኃይሉ የአፍሪካ ዋንጫን ለመቀላቀል ስለሚመጣ ተገቢውን ክብር ሰጥተን በጥንቃቄ መዘጋጀት እንደሚገባን ነው የሚሰማን።”

በመጨረሻም አሰልጣኝ ውበቱ ከአቀራረብ አንፃር ተጋጣሚ ሊጠቀምባቸው የሚችሉ አጨዋወቶችን ለማየት መሞከራቸውን ለዛም በሚመጥን መልኩ ሙሉ በሙሉ እንደተዘጋጁ እና ጨዋታውን በጥሩ ሁኔታ በመልካም እንቅስቃሴ አሸንፈው ወደ አይቮሪኮስቱ ጨዋታ ለመሄድ በጥሩ ዝግጅት ላይ እንደሚገኙ ጠቁመዋል።

በመቀጠል ተናጋሪ የነበረው የዋልያዎቹ አምበል ጌታነህ ከበደ ስለቡድኑ አሁናዊ ዝግጅት ጠቅለል ያለ ሀሳቡን እንዲህ ሲል ገልጿል።

“ለማዳጋስካር ጨዋታ በደንብ ተዘጋጅተናል። ባለፈው ከኒጀር ጋር ስንጫወት ከኮሮና ጋር በተያያዘ ብዙ አርፈን ነበር የተጫወትነው። ያኔ ሰባት/ስድስት ወር አርፈን ስለነበር የወዳጅነት ጨዋታም ስንጫወት በጣም ተቸግረን ነበር። አሁን ግን ቀጥታ ከውድድር ነው የመጣነው። መሀል ላይ እየተገናኘንም ልምምዶችን ስንሰራ ነበር። እንደከዚህ በፊቱ ለወራት ባንዘጋጅም እሱን ለማካካስ በዚህ መልኩ መዘጋጀታችን ጥሩ ሆኖልናል። አሁን 18/19 ቀን ሆኖናል። ብዙም አልከበደንም። ምክንያቱም ውድድር ላይ መቆየታችን ጠቅሞናል። ከባለፈው የተሻለም ተዘጋጅተናል።”

በመቀጠል በነበረው የመግለጫው አካሄድ ከጋዜጠኞች ጥያቄዎች ለአሰልጣኙ እና ለአምበሉ የተወረወሩ ሲሆን በዋነኝነት ተከታዮቹ ምላሾች ከአሰልጣኝ ውበቱ አባተ ተሰጥተዋል።

ለተጋጣሚ ስለሚሰጡት ግምት

“ትናንት ከተጫዋቾ ጋር የነበረን ስብስባ አንዱ ክፍል እዚህ ላይ ያጠነጠነ ነበር። ተጫዋቾች በትኩረት እንዲጫወቱ በምስል አስደግፈን ተጋጣሚያችን በፕሬዝዳንቱ የተደረገለትን ሽኝት እና ንግግራቸውን አሳይተናቸዋል። (ያገኙትን ማስረጃ ለጋዜጠኞች እያሳዩ) ተጫዋቾችም በዚህ ጉዳይ ጥሩ መረዳት ላይ ነው ያሉት። ለጨዋታው ዝቅተኛ ግምት ከመስጠት ጋር የተያያዘ ችግር አይኖርብንም።”

ጨዋታውን ከተጋጣሚ አንፃር ስለተመለከቱበት መንገድ

“በባለፈው የማዳጋስካር ጨዋታ ላይ የተሳተፉ ተጫዋቾች አሁንም በሁለታችንም ስብስብ ውስጥ አሉ። በቅርቡ የእነሱም አምበል ስለቡዳናችን ጥንካሬ በማንሳት ጥንቃቄ የሚያስፈልገው ጨዋታ ስለመሆኑ መግለፁ ይታወሳል። በዛ ጨዋታ የእነሱን ጥንካሬ ማየት ችለናል። ግብ ማስቆጠር የምንችልባቸው በርካታ ዕድሎችም ነበሩ። ቡድናችን ከጊዜ ወደ ጊዜ በመሻሻል ጥሩ አቋም ላይ የሚገኝ በመሆኑ ከእነሱ ደካማ እና ጥንካሬ ይልቅ በራሳችን ጠንካራ ጎን ላይ ተመስርተን እኛን የሚመስል ነገር ለማሳየት ተዘጋጅተናል።”

የወዳጅነት ተጋጣሚያችን ስለነበረው የማላዊ ብሔራዊ ቡድን

“አንዳንዴ ስለራሳችን ያለን ግምት የተዛባ እንደሆነ ይሰማኛል። እኛ ማላዊን የምንንቅበት ምንም ዓይነት እግር ኳሳዊ ምክንያት የለንም። ከማላዊ ያነስን ነን ! በሁሉም ነገር ከማላዊ ያነሰ ሪከርድ ነው ያለን። ከዚህ በፊት በነበሩ አምስት ግንኙነቶች ማላዊ ሀገሯ እና አዲስ አበባ ላይ ሁለት ጊዜ አሸንፋናለች። እዚህ 3-1 እዛ 3-2። የቀሩትን ባዶ ለባዶ ነው የወጣነው። በአምስት ግንኙነት ሦስት ጎሎች ነው ማላዊ ላይ ያስቆጠርነው። አሁን በአንድ ጨዋታ አራት ጎል ነው ያስቆጠርነው። ስለዚህ ስለኛ ጥንካሬ እንጂ ስለማላዊ ድክመት ማውራት ለቡድናችንም የምንሰጠውን ዋጋ ማሳነስ ስለሆነ እኔ ማመስገን እና ማበረታታቱ ላይ ነው የማታኩረው። ማላዊ ቀላል ተጋጣሚ አይደለም። እኛ የገጠምንበት መንገድ ግን የማላዊን ጥንካሬ እንዳናይ ያደረገን ነው የሚመስለኝ። የብሔራዊ ቡድናችንን የረጅም ጊዜ ሪከርድ ለማየት ሞክረናል። ከብሩንዲ ፣ ከሌሶቶ ፣ ከጅቡቲ ፣ ከሶማልያ ጋር ካልሆነ ያን ያህል ውጤታችን የሚያስመካ አይደለም። ያንን ስል የአሁኑም ቡድን ቢሆን ገና ሥራ ላይ ያለ ቡድን ነው። በፊፋ ደረጃም ከ146ኛ እያሻሻልን ለመሄድ ነው የምናስበው። ማላዊ ለእኛ ጥሩ ተጋጣሚ እንደነበር ነው የማስበው። ክፍተቶቻችንንም ለማየት አግዞናል።”

ስለስብስቡ የጥራት ደረጃ

“ከስብስብ አንፃር እኛ ለመጫወት ለምንፈልገው አጨዋወት የቀረቡ ተጫዋቾች በየቦታው አሉ። እንደውም አንድ ዜና እያየሁ ፊንላንድ ውስጥ የሚጫወት አንድ የዛምቢያን ተጫዋች የሀገሩ ሚዲያዎች በቁጥሮች ከሀላንድ ጋር እያነፃፀሩ የተሻለ ስለመሆኑ ይናገሩ ነበር። ደቡብ አፍሪካዎች ደግሞ ‘ገና በአውሮፓ ትላልቅ ሀገራት ሳይጫወት ይህን ለማለት አልፈጠናችሁም ወይ ?’ እያሏቸው ነበር። እኛም ገና ነን ! ጥሩ ጥሩ ልጆች አሉን ፤ ያ ጥሩ ነገር ነው። ለእኔ ግን አንዱን ከሲቲ ምናምን አይደለም ያመጣነው። ያሉንን ተጫዋቾች ችሎታ እናከብራለን። ግን ለማሰለፍ የሚያስጨንቅ ዓይነት ስብስብ አይደለም ያለን። በየቦታው ከዚህ በላይ የሚያድጉ ጥሩ ጥሩ ተጫዋቾች አሉን። ወጣቶች እና ልምዳቸውን ለማካፈል ዝግጁ የሆኑ ተጫዋቾች አሉን። እነዛን አቀናጅተን ሥራችንን ውጤታማ ለማድረግ እንሞክራለን። ከምንም በላይ ግን የምንጫወተውን ጨዋታ ለመረዳት ቅርብ የሆኑ ተጫዋቾች ስለያዝን ዕድለኞች ነን ብለን እናስባለን።”


© ሶከር ኢትዮጵያ