ሪፖርት | ኤሌክትሪክ ደረጃውን ያሻሻለበትን ውጤት አስመዝግቧል

በኢትዮ ኤሌክትሪክ እና ጅማ አባጅፋር መካከል የተደረገው የሁለተኛ ቀን ሁለተኛ ጨዋታ በኢትዮ ኤሌክትሪክን አንድ ለምንም አሸናፊነት ተገባዷል።

በመጀመሪያው ጨዋታ በአዳማ ከተማ የተረቱት ኢትዮ ኤሌክትሪኮች ሦስት ነጥብ ካስረከቡበት ጨዋታ ሦስት ለውጥ አድርገዋል። በዚህም አሠልጣኝ ክፍሌ ቦልተና አቤል ታሪኩ፣ ብሩክ ጌታቸው እና አደም አባስን በየተሻ ግዛው፣ ፀጋ ደርቤ እና ነስረዲን ኃይሉ ምትክ ቋሚ አሰላለፍ ውስጥ አካተዋል። በተቃራኒው በዓርቡ ጨዋታ ከወልቂጤ ከተማ ጋር ተጫውተው ነጥብ የተጋሩት ጅማ አባጅፋሮች ምንም ለውጥ ሳያደርጉ ጨዋታውን ጀምረዋል።

ፍጥነት ያለው እንቅስቃሴ ማስመልከት የጀመረው የሁለቱ ቡድኖች ጨዋታ ገና ከጅማሮ የግብ ማግባት ሙከራዎች ማስተናገድ ይዟል። በመጀመሪያዎቹ ደቂቃዎችም ሁለቱም ቡድኖች በየተራ ከቆመ ኳስ ጥሩ ጥቃት ፈፅመው ነበር። በቅድሚያም ጅማ ከመዓዘን ምት መሪ ለመሆን ሲጥር ኤሌክትሪክ ደግሞ በመቀጠል ከቅጣት ምት ጎል ለማግኘት ሞክሯል። በ11ኛው ደቂቃ ደግሞ ጅማ እጅግ ለግብ የቀረበበትን አጋጣሚ ፈጥሮ ነበር። በዚህም ሐብታሙ ንጉሴ ከግራ መስመር ያሻገረውን ኳስ ተመስገን ደረሰ በሩቁ ቋሚ ሆኖ በማግኘት በቀጥታ ወደ ግብ ቢመታውም ኳስ ለጥቂት ዒላማዋን ስታ ወደ ውጪ ወጥታለች።

ፈጣን የመልሶ ማጥቃት እንቅስቃሴ መከተል የቀጠሉት ጅማዎች በ20ኛው ደቂቃ ጥሩ ጥቃት ሰንዝረዋል። በዚህ ደቂቃም በስል ሽግግር የኤሌክትሪክ የግብ ክልል ደርሰው በራሂም ኦስማኖ አማካኝነት ሙከራ አድርገው የነበረ ቢሆንም የግብ ዘቡ ዘሪሁን ታደለ ኳሱን አምክኖታል። ይሄንን ሙከራ ያደረገው ኦስማኖ ከሁለት ደቂቃዎች በኋላም ከቀኝ መስመር የተሻገረለትን ኳስ በመጠቀም በግንባሩ ኳስ እና መረብን ለማገናኘት ጥሮ ነበር። በተቃራኒው ከኳስ ጋር ዘለግ ያለ ደቂቃ የሚያሳልፉት ኢትዮ ኤሌክትሪኮች በበኩላቸው የመጨረሻው የሜዳ ክልል ላይ በሚፈጥሩት የቅብብል ስህተት እና የውሳኔ አሠጣጥ ችግር የጠራ የግብ ማግባት ሙከራ ማድረግ ተስኗቸው ታይቷል።

በ37ኛው ደቂቃ ዳግም ወደ ኤሌክትሪክ የግብ ክልል የደረሱት ጅማዎች አስደንጋጭ ሙከራ አድርገው ተመልሰዋል። በዚህም ተመስገም በቀኝ መስመር ያገኘውን ኳስ ወደ ሳጥን ሲያሻማው ለኤልፓ ተከላካዮች ፈተና ሆኖ የቀረበው ኦስማኖ በውስጥ እግሩ ወደ ግብነት ለመቀየር ጥሯል። ከዚህ በተጨማሪ በ42ኛው ደቂቃም ራሱ ኦስማኖ ሌላ የግንባራ ኳስ ሞክሮ ለጥቂት ወጥቶበታል። በቀሪ የአጋማሹ ደቂቃዎችም ተጨማሪ ሙከራ ሳይደረግ ተጫዋቾች ወደ መልበሻ ክፍል አምርተዋል።

በሁለተኛው አጋማሽ ተሻሽለው የመጡት ኢትዮ ኤሌክትሪኮች ከመጀመሪያው አጋማሽ በተሻለ በተደራጀ ሁኔታ ወደ ጅማ የግብ ክልል መድረስ ጀምረዋል። ይሄ ሂደት ፍሬ አፍርቶላቸውም በ56ኛው ደቂቃ መሪ የሆኑበትን ጎል አግኝተዋል። በዚህም ከርቀት የተመታውን ኳስ የግብ ዘቡ አቡበከር ሳኒ ሲመልሰው ወደ ግራ ባዘነበለ ቦታ ላይ የነበረው አቤል ታሪኩ ኳሱን ወደ መሐል መሬት ለመሬት ሲያሻግረው በጥሩ አቋቋም ላይ የነበረው አደም አባስ አግኝቶት ኳስ እና መረብ ተገናኝተዋል።

ጥሩ በሆኑበት ጊዜ ግብ ያላገቡት ጅማዎች በሁለተኛው አጋማሽ የመጀመሪያ ደቂቃዎች ባሳዩት የመዘናጋት ችግር ግብ ቢያስተናግዱም ወዲያው ወደ ጨዋታው ለመመለስ መጣር ቀጥለዋል። በዚህም ግብ ባስተናገዱ በደቂቃ ልዩነት ተመስገን እንዲሁም ፕሪንስ ሳጥን ውስጥ ሆነው በሞከሯቸው ኳሶች ወዲያው አቻ ለመሆን ሞክረዋል። በቀጣዮቹ ደቂቃም ቡድኑ የማጥቃት ባህሪ ያላቸው ተጫዋቾችን በማስገባት ግብ ፍለጋውን ቀጥሏል። በዋናነት ደግሞ ረጃጅም ኳሶችን ወደ ሳጥን በመላክ ሲጫወት ተስተውሏል። በዚህ አጨዋውትም በ77ኛው ደቂቃ ከመስመር የተሻገረውን ኳስ ኦስማኖ እንደተለመደው በግንባሩ ወደ ግብነት ለመቀየር ጥሮ መክኖበታል።

በእጃቸው የገባውን ሦስት ነጥብ አሳልፎ ላለመስጠት በቀሪዎቹ ደቂቃዎች ለመከላከል ቅድሚያ የሰጡት ኤሌክትሪኮች በዋናነት የጅማን ጥቃት መመለት ላይ ትኩረት ሰጥተው መንቀሳቀስ ጀምረዋል። አልፎ አልፎ ግን ፈጣን ሽግግር (ከመከላከል ወደ ማጥቃት) በማድረግ ተጨማሪ ጎል ለማግኘት ቢጥሩም ውጥናቸው እምብዛም ፍሬያማ አልነበረም። ጨዋታውም ተጨማሪ ጎል ሳይቆጠርበት በኢትዮ ኤሌክትሪክ አሸናፊነት ተጠናቋል።

ውጤቱን ተከትሎ የመጀመሪያ ድላቸውን ያሳኩት ኢትዮ ኤሌክትሪኮች ነጥባቸውን ሦስት በማድረስ በጊዜያዊነት ወደ ሁለተኛ ደረጃ ከፍ ብለዋል። ሦስት ነጥብ አሳልፈው የሰጡት ጅማ አባጅፋሮች በበኩላቸው በመጀመሪያው ጨዋታ ባገኙት አንድ ነጥብ አራተኛ ደረጃን (በአንድ የግብ እዳ) ይዘዋል።