ቤትኪንግ ለፕሪምየር ሊጉ ክለቦች ማሊያ እያሰራ ነው

የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ የስያሜ መብት ባለቤቱ ቤትኪንግ ለ16ቱም የሊጉ ክለቦች መለያ እያሰራ እንደሆነ ታውቋል።

የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ አክሲዮን ማኅበር የሊጉን የቴሌቪዥን እና የስያሜ መብት ዳጎስ ባለ ገንዘብ መሸጡ ይታወቃል። የስያሜ መብቱ ባለቤት የሆነው ቤትኪንግ ለሊጉ አሸናፊ ዋንጫ ከማዘጋጀቱ ባለፈ ከውል ውጪ ለሊጉ ተሳታፊ ክለቦች ወጥ የሆነ ማሊያ ለማሰራት ፍላጎት እንዳለው ከወራት በፊት ሲገለፅ ነበር። ነገርግን በተለያዩ ምክንያቶች እውን ያልሆነው ይህ ጉዳይ ለ2014 የውድድር ዘመን ተግባራዊ ለመሆን እንቅስቃሴ ላይ መኮኑን የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ አክሲዮን ማኅበር ሥራ-አስኪያጅ አቶ ክፍሌ ሠይፈ ነግረውናል።

እንደ ሥራ-አስኪያጁ ማብራሪያ ከሆነ በሊጉ የሚሳተፉት ክለቦች በተጠናቀቀው የውድድር ዘመን ወጥ ያልሆነ እና የተዘበራረቀ መለያ መጠቀማቸው ቤትኪንግን እንዳሳሰበውና ከውል ውጪ በመልካም ፍቃደኝነት በቀጣይ ዓመት ለክለቦቹ በፈለጉት ዲዛይን ሁለት አይነት መለያ (የሜዳ እና የሜዳ ውጪ) ለማቅረብ እንቅስቃሴ መጀመሩ ታውቋል። አሁን ላይ ሁሉም ክለቦች (አንዳንዶቹ ዘግይተውም ቢሆን) የራሳቸው ዲዛይን እና የሚፈልጉት መጠን (size) እንደላኩ የተገለፀ ሲሆን አንድ ክለብ በአጠቃላይ 54 ማሊያዎች (27 የሜዳ 27 የሜዳ ውጪ) እንደሚዘጋጅለት ተረድተናል። ከማሊያዎቹ በተጨማሪ 30 ቱታዎች እና የልምምድ ቲ-ሸርቶች እንደሚኖርም ተመላክቷል።

ከዚሁ ጋር በተያያዘ ይሄንን መለያ ቤትኪንግ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን የትጥቅ አቅራቢ ተቋም ከሆነው አምብሮ ጋር ተፈራርሞ እያሰራው እንደሆነ ሶከር ኢትዮጵያ አረጋግጣለች። ታዲያ በሊጉ የሚገኙ እና ከሌላ የትጥቅ አቅራቢ ተቋም ጋር አብረው የሚሰሩ ክለቦች ጉዳይን በተመለከተ ጥያቄ ያቀረብንላቸው አቶ ክፍሌ “እንዳልኩት ይህ አስገዳጅ አይደለም። ቤትኪንግም በውል የገባበት ግዴታ የለውም። የማሊያው ጉዳይ እንደ ቦነስ ነው። ስለዚህ የሚፈልጉ ክለቦች ይወስዳሉ። የማይፈልጉ ደግሞ የራሳቸው ምርጫ ነው። ስለዚህ ክለቦቹ ራሱ ማስታረቂያውን ይፈልጉ።” ብለውናል።

በአሁኑ ሰዓት በሂደት ላይ የሚገኘው የማሊያው ጉዳይ ለ2014 የውድድር ዘመን እንደሚደርስ ቤትኪንግ እንደገለፀ ነገርግን አስገዳጅ ነገር ስለሌለ በውል የታሰረ ስምምነት አለመኖሩ ተነግሮናል።