ቅዱስ ጊዮርጊስ የወጣቱን የግብ ዘብ ውል አድሷል

በቅርቡ አዲስ አሠልጣኝ የሾሙት ቅዱስ ጊዮርጊሶች ከደቂቃዎች በፊት የወጣቱን ግብ ጠባቂ ውል ማደሳቸውን ይፋ አድርገዋል።

ዩጋንዳዊውን ግብ ጠባቂ ቻርለስ ሉክዋጎን ወደ ስብስባቸው ለመቀላቀል ከጫፍ የደረሱት ቅዱስ ጊዮርጊሶች ከደቂቃዎች በፊት ከ17 ዓመት በታች ቡድናቸው ጀምሮ ሲያገለግላቸው የነበረውን ወጣቱን ግብ ጠባቂ ተመስገን ዩሐንስን ውል ለተጨማሪ ዓመት አድሰዋል። ከ17 እና ከ20 ዓመት በታች ቡድን ውስጥ የነበረው ተመስገን የክለቡ ተስፋ ቡድን ድረስ መጫወት መቻሉ ይታወቃል። ያለፉትን ሁለት ዓመታት ወደ ዋናው ቡድን አድጎ ልምምድ ሲሰራ የነበረ ቢሆንም በሊጉ የመጫወት ዕድል ማግኘት ሳይችል ቀርቶ ነበር።

በአሠልጣኝ ተመስገን ዳና በሚመራው የኢትዮጵያ ከ20 ዓመት በታች ብሔራዊ ቡድን ውስጥ የነበረው ተመስገን በተጠናቀቀው የውድድር ዘመን እስከ ባህር ዳሩ ዙር ድረስ ከክለቡ ጋር አብሮ የነበረ ቢሆንም ከዛ በኋላ ከዋናው ቡድን ጋር አላሳለፈም ነበር። አሁን ግን ከአዲሱ ግብ ጠባቂ ቻርለስ ሉክዋጎ እና ባህሩ ነጋሽ ጋር ለመፎካከር የሁለት ዓመት ውል መፈረሙ ታውቋል።