የፕሪምየር ሊግ ጨዋታዎችን የሚያስተናግዱ ሜዳዎች መገምገም ሊጀምሩ ነው

በተቀመጠው ቀነ ገደብ የቀጣይ ዓመት የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ውድድር ለማስተናገድ ጥያቄ ያቀረቡት አራቱ ስታዲየሞች ምልከታ ሊደረግባቸው ነው

በደማቅ ሁኔታ ተጀምሮ የተገባደደው የ2013 የኢትዮጵያ ቤትኪንግ ፕሪምየር ሊግ በቀጣይ ዓመት በ16 ክለቦች መካከል እንደሚደረግ ይታወቃል። የሊጉ የበላይ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ አክሲዮን ማኅበሩም የክለቦች ምዝገባ አከናውኖ ከጨረሰ በኋላ በሳምንቱ መጀመሪያ (ሰኞ) የዕጣ ማውጣት ሥነ-ስርዓት አከናውኖ ነበር። ዘንድሮ የነበሩ ጠንካራ ጎኖችን ለማስቀጠል እንዲሁም የነበሩ ክፍተቶችን አስተካክሎ ለመቅረብ እንቅስቃሴ ላይ የሚገኘው አክሲዮን ማኅበሩም ከቀጣይ ሳምንት ጀምሮ የ2014 የሊጉን ጨዋታዎች ለማስተናገድ ፍቃድ ያሳዩትን ስታዲየሞች መመልከት እና መገምገም እንደሚጀምር አስታውቋል።

የአክሲዮን ማኅበሩ ሥራ-አስኪያጅ አቶ ክፍሌ ሠይፈ ለሶከር ኢትዮጵያ እንደገለፁት ከሆነ የቀጣይ ዓመት ውድድር ለማስተናገድ የባህር ዳር ዓለም አቀፍ ስታዲየም፣ የድሬዳዋ ስታዲየም፣ የሀዋሳ ዩኒቨርስቲ ስታዲየም እና የአዳማ ሳይንስ እና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርስቲ ስታዲየም በተቀመጠው ቀነ ገደብ ውድድሩን ለማስተናገድ ጥያቄ ማቅረባቸውን አመላክተዋል። የቀረበውን ጥያቄ ተመርኩዞም አክሲዮን ማኅበሩ አዲስ ኮሚቴ አቋቁሞ ከቀጣይ ሳምንት ጀምሮ ምልከታ እና ግምገማ እንደሚያደርግ ጠቁመዋል።

አቶ ክፍሌ አያይዘውም “በቀጣይ ዓመት የሚደረገው ውድድር በ16 ክለቦች መካከል እንደሆነ ይታወቃል። ይህ የክለቦች ቁጥር ማደግ ደግሞ የአስተናጋጅ ከተሞችን ዝግጁነት ከፍ እንዲል ያስገድዳል። በተለይ ደግሞ የሆቴል እና የመለማመጃ ሜዳዎች ጉዳይ በአትኩሮት ሊታይ ይገባዋል። ይህንንም ተከትሎ ከቀጣይ ሳምንት ጀምሮ ፍላጎት ያሳዩትን ስታዲየሞች እና ተያያዥ አስፈላጊ ነገሮችን መመልከት እንጀምራለን።” ብለዋል።

ሥራ አስኪያጁ በንግግራቸው ማብቂያ ላይም የቀጣይ ዓመት ውድድር ምሽት ላይ እንዲደረግ በዲ ኤስ ቲቪ በኩል ፍላጎት እንዳለ ጠቁመው ስታዲየሞች የምሽት ጨዋታዎችን እንዲያደርጉ የሚያስችል ብርሃን የሚያገኙበት መንገድ ሊመቻች እንደሚገባ አብራርተዋል።