የሲዳማ ጎፈሬ ዋንጫ ውድድር የእጣ ማውጣት ሥነ-ስርዓት ነገ ይካሄዳል

ለመጀመሪያ ጊዜ የሚካሄደው የሲዳማ ጎፈሬ ዋንጫ ውድድር የፊታችን ቅዳሜ ሲጀመር የእጣ ማውጣት መርሐ-ግብሩም ነገ ከሰዓት ይከናወናል።

ከተቋቋመ ገና አንድ ዓመት እያስቆጠረ የሚገኘው የሲዳማ እግርኳስ ፌዴሬሽን እንደ ቅድመ ውድድር ዝግጅት የሚቆጠረውን የክልሉ ዋንጫ ፍልሚያ ዘንድሮ ለመጀመሪያ ጊዜ እንደሚያከናውን ይታወቃል። የስፖርት ትጥቅ አምራች ተቋሙ ጎፈሬ’ን የሥያሜ አጋር በማድረግ ከመስከረም 15 ጀምሮ የሚካሄደው ውድድርም በሲዳማ ቡና፣ ሀዋሳ ከተማ፣ ሀዲያ ሆሳዕና፣ ድሬዳዋ ከተማ፣ ጅማ አባጅፋር እና ሰበታ ከተማ መካከል ይደረጋል ተብሎ ቢጠበቅም ጅማ አባጅፋር ሀሳቡን እንደቀየረ እየተሰማ ይገኛል።

የሲዳማ እግርኳስ ፌዴሬሽን ምክትል ፕሬዝዳንት አቶ አንበስ አበበ ለሶከር ኢትዮጵያ እንደገለፁት ከሆነ ጅማ አባጅፋር በሚገኝበት ክልል ፌዴሬሽን አማካኝነት የአሳትፉኝ ጥያቄ አቅርቦ ስራዎች ከተሰሩ በኋላ ባለቀ ሰዓት ሀሳቡን ቀይሯል። ክለቡ ቀድሞ እወዳደራለሁ በማለቱ የትጥቅ እና አስፈላጊ ነገሮች በመዘጋጀታቸው ኪሳራ እንዳይከሰት ንግግሮች እየተደረጉ እንደሆነም ምክትል ፕሬዝዳንቱ አስረድተውናል።

ምንም እንኳን ጅማ በለወጠው አቋም ቢፀናም ሲዳማ ቡና፣ ሀዋሳ ከተማ፣ ሀዲያ ሆሳዕና፣ ድሬዳዋ ከተማ፣ እና ሰበታ ከተማ በአሁኑ ሰዓት ውድድሩን ለማድረግ በከተማው እንደሚገኙ ተጠቁሟል። ነገ አመሻሽ 10 ሰዓትም ሀዋሳ በሚገኘው ሌዊ ሪዞርት የእጣ ማውጣት ሥነ-ስርዓት እንደሚከናወን ታውቋል። በዕለቱም ጎፈሬ ለክለቦች ያዘጋጀውን የውድድር ትጥቅ እንደሚያስረክብ ተመላክቷል።

የሲዳማ ጎፈሬ ዋንጫ የሚዲያ አጋር የሆነችው ድረ-ገፃችን ሶከር ኢትዮጵያ በውድድሩ ዙሪያ የሚኖሩ አዳዲስ ጉዳዮችን እየተከታተለች የሚታቀርብ መሆኑን መግለፅ ትፈልጋለች።