የባህር ዳር ከተማ የሴቶች ቡድን አሠልጣኝ ውሏን አራዝማለች

የባህር ዳር ከተማን የሴቶች ቡድን ከታችኛው የሊግ እርከን ወደ ዋናው ሊግ ያሳደገችው አሠልጣኝ ሰርካዲስ እውነቱ በዛሬው ዕለት ውሏን አራዝማለች።

ባሳለፍነው የውድድር ዓመት በኢትዮጵያ ሁለተኛ ዲቪዚዮን የሴቶች ውድድር 41 ነጥቦችን በመሰብሰብ ወደ ዋናው ሊግ ያደገው ባህር ዳር ከተማ የአሠልጣኙን ውል ለማደስ ከሰሞኑን ንግግር ሲያደርግ ነበር። ክለቡም ከምስረታው አንስቶ አሠልጣኝ የነበረችውን ሰርካዲስ እውነቱን ለማስቀጠል ሲያደርግ የነበረው ጥረት ፍሬ አፍርቶ አሠልጣኟ በዛሬው ዕለት ውሏን ማራዘሟ ታውቋል።

የአሠልጣኝነት ህይወቷን በዳሽን ቢራ ረዳት አሠልጣኝነት የጀመረችሁ ሰርካዲስ በመቀጠል በክለቡ በዋና አሠልጣኝነት ሚና ማገልገሏ ይታወሳል። ከዛም ጥረት ኮርፖሬትን ካሰለጠነች በኋላ ባህር ዳር ከተማን 2012 ላይ ተቀላቅላለች። አሁንም ከሰማያዊ ለባሾቹ ጋር ለቀጣዮቹ ሁለት ዓመታት ለመዝለቅ ፊርማዋን አኑራለች።