​ቅድመ ዳሰሳ | የ10ኛ ሳምንት የመጀመሪያ ዕለት ጨዋታዎች

ሊጉ ከዕረፍት ሲመለስ በቀዳሚነት ነገ የሚከወኑትን ሁለት ጨዋታዎች እንዲህ ዳሰናቸዋል።

ኢትዮጵያ ቡና ከ ሀዋሳ ከተማ

ከዘጠኝ የጨዋታ ሳምንታት በኋላ በአፍሪካ ዋንጫ ጨዋታዎች ምክንያት ዕረፍት ላይ የሰነበተው የቤትኪንግ ኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ወደ ሜዳ ሲመለስ በቀዳሚው መርሐ ግብር የሚገናኙት ከ1990 ጀምሮ ያለማቋረጥ በውድድሩ ላይ የሚሳተፉት ሁለቱ ክለቦች ይሆናሉ። በዘንድሮው ውድድርም በተመሳሳይ ነጥብ አምስተኛ እና ስድስተኛ ደረጃ ላይ የተቀመጡት ተጋጣሚዎቹ እስከ ሁለተኛ ደረጃ ከፍ የሚያደርጋቸውን ድል ለማሳካት ወደ ሜዳ ይገባሉ።

በሊጉ የሀዋሳ ቆይታ ደካማ አጀማመር ያደረገው ኢትዮጵያ ቡና ከአምስተኛው ሳምንት እስከ ስምንተኛው ሳምንት ባሳካቸው ተከታታይ ድሎች በሰንጠረዡ ወደ ላይ ከፍ ማለት ችሏል። ይሁንና በመጨረሻ በሀዲያ ሆሳዕና የ1-0 ሽንፈት አስተናግዶ ነው ነገ ድሬዳዋ ላይ ለሚቀጥለው ውድድር የደረሰው። ካለአቡበከር ናስር ወደ ሜዳ የሚገባው ቡና በሀዋሳ ሁለት ገፅታ የነበረው የውድድር ከማሳለፉ በተጨማሪ ድል ባደረገባቸው ጨዋታዎችም ሰፋ ባለ የግብ ልዩነት በመርታት ለቀጣይ ፍልሚያ የሥነ ልቦና የበላይነትን ማግኘት ላይ ደከም ብሎ በመታየቱ ድሬ ላይ ኮስታራ ተፎካካሪ መሆኑን የሚያሳይ ድል በማስመዝገብ መጀመር ይኖርበታል።

ሀዋሳ ከተማ በመቀመጫ ከተማው ባደረጋቸው ዘጠኝ ጨዋታዎች ለክፉ የማይሰጥ ውጤት አስመዝግቧል። ባሳለፍነው የውድድር ዓመት ከኢትዮጵያ ቡና ሙሉ ስድስት ነጥቦችን መውሰዱም የነገውን ጨዋታ በጥሩ የማሸነፍ መንፈስ ለማድረግ እንደሚረዳው ይታመናል። በመጨረሻዎቹ ሦስት ጨዋታዎቹ ራሱን ከሽንፈት አርቆ ያጠናቀቀው ሀዋሳ እንደሁልጊዜው የሚታይበት የወጥነት ችግር ዘንድሮም አብሮት ያለ ይመስላል። በቀጣይ ጨዋታዎች ይህንን ችግር ቀርፎ በላይኛው ፉክክር ውስጥ ለመካተት ደግሞ በምስራቋ ከተማ የሚኖረውን ቆይታ በድል መጀመር ምርጫ ያለው ዕቅድ አይመስልም።

ኢትዮጵያ ቡና ለሙከራ ወደ ደቡብ አፍሪካ ያቀናው አቡበከር ናስርን ጨምሮ ጉዳት ላይ የሚገኙት ሬድዋን ናስር ፣ ሚኪያስ መኮንን እና ነስረዲን ኃይሉን በነገው ጨዋታ አይጠቀምም። ሀዋሳ ከተማ ግን ከዚህ በተለየ ሁኔታ ሙሉ ስብስቡ ለጨዋታው ዝግጁ መሆኑ ተስምቷል።

ጨዋታው በኢንተርናሽናል ዳኛ ኃይለየሱስ ባዘዘው መሪነት ይከናወናል። ከዚህ በተጨማሪ ተመስገን ሳመኤል እና ሻረው ጌታቸው የረዳት ዳኝነት ባህሩ ተካ‌‌ ደግሞ የአራተኛ ዳኝነት ኃላፊነት ተሰጥቷቸዋል።

የእርስ በእርስ ግንኙነት 

– ከሊጉ ጅማሮ አንስቶ መሳተፍ የቀጠሉት ሁለቱ ክለቦች የእርስ በእርስ ውጤት በመሀላቸው ያለውን የፉክክር ሚዛናዊነት የሚያሳይ ነው። በእስካሁን የ44 ጊዜ ግንኙነታቸውም በ16 አጋጣሚዎች አቻ ሲለያዩ ዕኩል 14 ጊዜ ተሸናንፈዋል።

– በጨዋታዎቹ  ኢትዮጵያ ቡና 52 ጊዜ ኳስ እና መረብን በማገናኘት የበላይ ሲሆን ሀዋሳ ከተማ ደግሞ ሦስት የፎርፌ ግቦችን ጨምሮ 45 ግቦችን ማስመዝገብ ችሏል።

ሲዳማ ቡና ከ ባህር ዳር ከተማ

የአስረኛው ሳምንት ሁለተኛ ጨዋታ በሊጉ የዋንጫ ፉክክር ግምት ተሰጥቷቸው የውድድር ዓመቱን የጀመሩትን ሁለት ቡድኖች ያገናኛል። በመካከላቸው በባህር ዳር የበላይነት የሦስት ነጥቦች ልዩነት ያለ ሲሆን ከተቀራረበው የሊጉ የደረጃ ሰንጠረዥ አንፃርም ስንመለከተው ጨዋታው ፉክክር የሚያስመለክተን ዓይነት ሊሆን ይችላል። 

በመቀመጫ ከተማው ወላይታ ድቻን ድል በማድረግ ውድድሩን የጨረሰው ሲዳማ ቡና እስካሁን ድል ባደረገባቸው ሁለት ጨዋታዎች ላይ ካሳየው ብቃት አንፃር በሌሎቹ ጨዋታዎች ላይ በአመዛኙ ተዳክሞ የመቅረቡ ነገር ተሰጥቶት የነበረውን ግምት እንዲሸረሸር አድርጓል። አምና የጀመረው የውጤት ማጣት ዘንድሮም አብሮት ዘልቆ ተደጋጋሚ የደጋፊዎች ተቃውሞን አስከትሎበት በሜዳው ባደረጋቸው ጨዋታዎች በጫና ውስጥ እንዲቆይ መገደዱን ስንመለከትም በድሬዳዋው የውድድሩ ቆይታ በነፃነት ተጫውቶ ማንሰራራትን እንደሚያልም መገመት አያዳግትም።

ጥሩ አጀማመር ካደረጉ ቡድኖች ውስጥ የሚጠቀሰው ባህር ዳር ከተማ የሀዋሳ ቆይታ በዚያው የቀጠለ አልነበረም። እርግጥ ነው አሁንም ከመሪው ጋር ያለው ልዩነት አራት ብቻ መሆኑ ከግምት ባያስወጣውም በተለይ ከታች በመጡት መከላከያ እና አርባምንጭ ከተማ ያስተናገዳቸው ሽንፈቶች ብዙዎች የቡድኑን ዘለቄታዊ ተፎካካሪነት እንዲጠራጠሩ ያደረገ ነበር። ሩብ ፍፃሜ በደረሰው የአፍሪካ ዋንጫ የካፍ ቴክኒክ ኮሚቴ ውስጥ ኃላፊነት ባላቸው አሰልጣኝ አብርሀም መብራቱ ሳይመራ በድሬዳዋ የመጀመሪያ ጨዋታውን የሚያደርገው ባህር ዳር የሀዋሳው ዓይነት አጀማመር ማድረግ ከቻለ ዳግም በጠንካራ ተፎካካሪነት መዝለቅ እንደሚችል ማሳየት ይችላል።

በነገው ጨዋታ ሲዳማ ቡና የግራ መስመር ተከላካዩ ሰለሞን ሀብቴን በጉዳት ሳቢያ ያጣል። በቁጥር በርከት ያሉ ተጫዋቾቻቸውን የማያገኙት ባህር ዳሮች ደግሞ ግርማ ዲሳሳ በቅጣት የማይቀላቀላቸው ሲሆን አለልኝ አዘነ እና መሳይ አገኘሁ በህመም ኦሴይ ማዉሊ እና ኃይማኖት ወርቁ ደግሞ በጉዳት ከነገው ጨዋታ ውጪ መሆናቸውን ስምተናል።

ጨዋታውን በመሀል ዳኝነት የሚመሩት ፌደራል ዳኛ ኤፍሬም ደበሌ ናቸው። ይበቃል ደሳለኝ እና ፍሬዝጊ ተስፋዬ ረዳት ዳኞች ሚካኤል ጣዕመ ደግሞ አራተኛ ዳኛ በመሆን ተመድበዋል።

የእርስ በእርስ ግንኙነት

– ሁለቱ ቡድኖች እስካሁን በአራት የሊግ ጨዋታዎች ሲገናኙ አንዱን አቻ ተለያይተው ሦስቱን ባህር ዳር ከተማ በአሸናፊነት ማጠናቀቅ ችሏል። በጨዋታዎቹ ባህር ዳር ሰባት እንዲሁም ሲዳማ ሦስት ጊዜ ኳስ እና መረብን አገናኝተዋል።