​ሪፖርት | ወደ ከተማው የተመለሰው ድሬዳዋ ድል ቀንቶታል

ከቀትር በኋላ በተደረገው የቤትኪንግ ኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ጨዋታ ድሬዳዋ ከተማ መከላከያን 1-0 አሸንፏል።

በሁለቱ ተጋጣሚዎች ፈጥኖ ወደግብ ለመድረስ የሚደረግ ጥረት እየተንፀባረቀበት የጀመረው ጨዋታ የተቆራረጡ የማጥቃት ሂደቶችን እያሳየ የቀጠለ ነበር። ሆኖም 7ኛው ደቂቃ ላይ ሳይታሰብ የእንየው ካሳሁንን ሚዛን መሳት ተከትሎ ብሩክ ሰሙ በረጅሙ ከተላከለት ኳስ ያገኘው ግልፅ የማግባት ዕድል የጨዋታው የመጀመሪያ አስደንጋጭ ቅፅበት መሆን ቢችልም የብሩክ የግንባር ሙከራ ኢላማውን ሳይጠብቅ ቀርቷል። 

በሂደት ድሬዳዋዎች የተሻለ ኳስ ተቆጣጥረው ተጋጣሚያቸውን ወደ ራሱ ሜዳ ገፍተው መንቀሳቀስ ጀምረዋል። ነገር ግን የመከላከያን የመልሶ ማጥቃት ከማደብዘዝ ባለፈ በቅብብሎቻቸው የተደራጀ የማጥቃት ሂደትን ሳይተገብሩ ቆይተው 24ኛው ደቂቃ ላይ የሰነዘሩት ቀጥተኛ ጥቃት ፍሪያማ ሆኖላቸዋል። ከቀኝ መስመር ይነሳ የነበረው አብዱርሀማን ሙባረክ ከኋላ ከመሳይ ጻውሎስ በረጅሙ የተላከለትን ኳስ ወደ ውስጥ ሰበር አድርጎ ከሳጥን ውጪ በመምታት የክሌመንት ቦዬ ድክመት ተጨምሮበት ድሬዎችን ቀዳሚ ያደረገች ግብ አስቆጥሯል።

ግብ አስተናግደው ከውሀ ዕረፍት የተመለሱት መከላከያዎች አንፃራዊ ንቃት አስይተዋል። ረዘም ካሉ ኳሶች ፈጠን ብለው ወደ ድሬዳዋ ሳጥን ውስጥ በመገኘት እና በቆሙ ኳሶች ጫና ለመፍጠር ሞክረዋል። በተለይ 33ኛው ደቂቃ ላይ ከቅጣት ምት የተነሳን ኳስ ሰመረ ሀፍተይ ሲያበርድለት ኢብራሂም ሁሴን ከግቡ አፋፍ ላይ ያደረገው የመቀስ ምት ሙከራ ለጥቂት ነበር በፍሬው ጌታሁን ቅልጥፍና የዳነው።

የመጨረሻዎቹ ደቂቃዎች በሙከራዎች ተሞልተዋል። 41ኛው ደቂቃ ላይ የድሬዎች የኳስ ፍሰት ሳጥን ውስጥ ዘልቆ በግራ በሄኖክ ኢሳያስ እና ሙኸዲን ሙሳ ጥሩ ጥምረት የግብ ዕድል ቢፈጥሩም አብዱልፈታ ዓሊ ከቅርብ ርቀት ወደ ላይ ልኮታል። መከላከያዎችም በመጨረሻ ደቂቃዎች ከዳንኤል ኃይሉ በተቀማ ኳስ ሰመረ ከሳጥን ውጪ ባደረገው ሙከራ እና ከማዕዘን ምት በተሻማ ኳስ ልደቱ ጌታቸው በግንባር ገጭቶ ፍሬው እና መሳይ ባዳኑባቸው ኳሶች ለግብ ቀርበው ነበር።

ከዕረፍት መልስ ቀዝቅዝ ባለው ጨዋታ ኦኩቱ ኢማኑኤልን ወደ ሜዳ ያስገቡት መከላከያዎች ጫና ፈጥረዋል። ሆኖም ቡድኑ የቆመ ኳስ ዕድሎችንም ጭምር ቢያገኝም የድሬዳዋዎች ጠንቀቅ ብለው ክፍተቶችን ይዘጉ የነበሩበት መንገድ ከሙከራ አርቋቸዋል። በአንፃሩ የድሬዎች የማጥቃት ኃይላቸው ከመጀመሪያው ቀነስ ብሎ ጥንቃቄ አዘል ለመልሶ ማጥቃት የቀረበ አጨዋወት ሲከተሉ ተስተውለዋል።

ከ70ኛው ደቂቃ በኋላ በቢኒያም በላይ መሪነት የጦሩ የግራ መስመር ፈጣን ጥቃት ደጋግሞ ይታይ ነበር። ነገር ግን ችኮላ የሚታይበት የቡድኑ የማጥቃት ጥረት ግልፅ ዕድል ሳይፈጥር ቆይቷል። ይልቁኑም ድሬዎች ወደመጨረሻው ላይ ጫና የመፍጠሩን ተራ ሲወስዱ የተሻሉ ዕድሎችን ፈጥረዋል። 

በተለይ 80ኛው ደቂቃ ላይ አብዱርሀማን ሙባረክ ከኋላ ከደረሰው ተንጠልጣይ ኳስ ከሳጥን ውስጥ ወደ ግብ የላከው ኳስ ለጥቂት ተነሳበት እንጂ ሁለተኛ ግብ ለመሆን ተቃርቦ ነበር። ክሌመንት ቦዬን እምብዛም አልፈተነም እንጂ ሙኸዲን ሙሳም ከሁለት ደቂቃዎች በኋላ ከቀኝ የሳጥኑ ክፍል የመታው እንዲሁም ሔኖክ ኢሳያስ ከቅጣት ምት ያደረገው ሙከራ ኢላማቸውን ጠብቀው ነበር። ሌላ ግብ ያላስተናገደው ጨዋታ ግን በዛው ውጤት ተቋጭቷል።

ድሉን የከትሎ ነጥቡን 14 ያደረሰው ድሬዳዋ ከተማ ደረጃውን ከ13 ወደ 8ኛ ከፍ ማድረግ ችሏል።