ካፍ ጋቦን ለምታስተናግደው የ2017 የአፍሪካ ዋንጫ ማጣሪያ በምድብ 10 ስታደ ሙስጠፋ ቻክር ላይ አልጄሪያ እና ኢትዮጵያ የሚያደርጉት ጨዋታ እንዲመሩ የደቡብ አፍሪካ ዳኞችን ሲሾም አራተኛው ዳኛ ከሞሮኮ የጨዋታው ኮሚሽነር ደግሞ ከጋቦን ሆነዋል፡፡ ብልዳ ከተማ ላይ በሚደረገው ጨዋታ የመሃል ዳኛ ሆነው የሚመሩት ቪክቶር ጎሜዝ ናቸው፡፡ የ33 ዓመቱ ጎሜዝ ከ2011 ጀምሮ የፊፋ ኢንተርናሽናል የሆኑ ሲሆን የአብሳ ፕሪምየርሺፕ ጨዋታዎችን ከ2008/09 የውድድር ዘመን ጀምሮ መምራት ችለዋል፡፡ የ2012/13 የአብሳ ፕሪምየርሺፕ የዓመቱ ምርጥ ዳኛ ተብለውም ተሸልመዋል፡፡ የጎሜዝ ረዳት ሆነው ጨዋታውን እንዲመሩ የተመረጡት የሃገራቸው ሰው የሆኑት ሞቲቢዲ ኩማሎ እና ሊንዲካያ ቦሎ ናቸው፡፡ የ36 ዓመቱ ቦሎ ከ2011 ጀምሮ የፊፋ ኢንተርናሽናል ረዳት ዳኛ ሲሆን ሩዋንዳ ባስተናገደችው የአፍሪካ ሃገራት ዋንጫ /ቻን/ ላይ በረዳት ዳኛነት ያገለገሉት የ29 ዓመቱ ኩማሎ ከ2013 ጀምሮ የፊፋ ኢንተርናሽናል ረዳት ዳኛ መሆን ችለዋል፡፡
ካፍ ለጨዋታው አራተኛ ዳኛ እንዲሆኑ የመረጣቸው የ37 ዓመቱን ሞሮኮዊ ኑረዲን ኤል-ጃፋሪ በአፍሪካ ዋንጫ ማጣሪያ ቱኒዚያ ጅቡቲን 8-1 የረታችበትን ጨዋታ በመሃል ዳኝነት የመራ ሲሆን በቻን ላይም አንድ የምድብ ጨዋታ መምራት ችሏል፡፡ የጨዋታው ኮሚሽነር ሆነው ጨዋታው የሚመሩት ዳይዶን ንዶምቦ ሊኮኒ በ2013 በጋቦን እግርኳስ ፌድሬሽን የፕሬዝዳታዊ ምርጫ ላይ በተፈጠረ ችግር ምክንያት ፊፋ ለአንድ ዓመት በግዜያዊ ፕሬዝደንትነት እና የኖርማላይዜሽን ኮሚቴው የበላይ አድርጓቸው ነበር፡፡