ካሜሩን 2016፡ ሉሲዎቹ ለአልጄርያው ጨዋታ እየተዘጋጁ ነው

በሴፕቴምበር 2016 ካሜሩን ላይ ለሚስተናገደው የአፍሪካ ሴቶች ዋንጫ ለማለፍ ከአልጄርያ ሴቶች ብሄራዊ ቡድን ጋር የመልስ ጨዋታውን በመጪው ቅዳሜ የሚያደርገው የኢትዮጵያ ሴቶች ብሄራዊ ቡድን ዝግጅቱን ቀጥሏል፡፡

PicsArt_1458745781924

ብሄራዊ ቡድኑ ከአልጀርስ የ1-0 ሽንፈት አስተናግዶ ከተመለሰ በኋላ በቀን ሁለት ጊዜ ሲሰራ የቆየ ሲሆን ከወንድ ወጣት ቡድኖች ጋርም የዝግጅት ጨዋታዎች አድጓል፡፡ ከሰኞ ጀምሮ ደግሞ በቀን አንድ ጊዜ አዲስ አበባ ስታድየም ላይ በመስራት ላይ ይገኛል፡፡ አሰልጣኝ ብርሃኑ ግዛው በዛሬው ልምምድ ሰሞኑን በተደጋጋሚ ሲሰሩት እንደነበረው በማጥቃት ላይ ያተኮረ ልምምድን ያሰሩ ሲሆን ቋሚ ተሰላፊ ይሆናለሉ ተብለው የሚጠበቁት ተጫዋቾችን በመለየት የግብ ማስቆጠር ልምምዶችን ሲሰሩ ተስተውሏል፡፡ በግማሽ ሜዳ ለሁለት በመከፈል መጫወትም ችለዋል፡፡ ሉሲዎቹ በአሁኑ ሰአት 24 ተጫዋቾችን በመያዝ ዝግጅት በማድረግ ላይ ሲሆን የዳሽን ቢራዋ አጥቂ ሄለን እሸቱ በጉዳት በትላንትናው ልምምድ ላይ በመጎዳቷ የዛሬ ልምምድ አምልጧታል፡፡ ሄለን ከጉዳቷ አገግማ አልጄርያን በሚገጥመው ቡድን ውስጥ የመካተት እድሏ አጠራጣሪ ነው ተብሏል፡፡ ተጋጣሚው የአልጄርያ ሴቶች ብሄራዊ ቡድን ዛሬ ምሽት አዲስ አበባ እንደሚገባ የሚጠበቅ ሲሆን ነገ እና ከነገ በስቲያ ጨዋታቸውን በሚያደርጉበት አዲስ አበባ ስታድየም ልምምድ ያደርጋሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡

የሁለቱ ቡድኖች ጨዋታ ቅዳሜ በአዲስ አበባ ስታድየም 10፡00 ላይ ሲካሄድ ኢትዮጵያ ወደ ተከታዩ የማጣርያ ዙር ለማለፍ ግብ ሳታስተናግድ በሁለት የግብ ልዩነት እና ከዚያ በላይ በሆነ ውጤት ማሸነፍ ይጠበቅባታል፡፡ በሉሲዎቹ ዙርያ የአሰልጣኝ እና ተጫዋቾችን አስተያየቶች ከጨዋታው ቀደም ብለን ወደ እናንተ እናደርሳለን፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *