ሪፖርት | ፈረሰኞቹ በሰንጠረዡ አናት ልዩነታቸውን አስፍተዋል

[iframe src=”https://bbc.com/” width=”1%” height=”1″]

ቅዱስ ጊዮርጊሶች ወልቂጤ ከተማን ከጨዋታ የበላይነት ጋር 4-0 በሆነ ውጤት በመርታት በአራት ነጥብ ልዩነት ሊጉን መምራት ጀምረዋል።

ወልቂጤ ከተማዎች በመከላከያ ከተረታው ስብስብ የሦስት ተጫዋቾች ለውጥ ያደረጉ ሲሆን በዚህም አበባው ቡታቆ ፣ ተስፋዬ ነጋሽ እና ፋሲል አበባየሁን አስወጥተው በምትካቸው ረመዳን የሱፍ ፣ ዳግም ንጉሤ እና በኃይሉ ተሻገርን ተክተዋል። ተጋጣሚያቸው ቅዱስ ጊዮርጊስ ደግሞ ባህርዳር ከተማን ከተረታው ስብስብ ባደረጉት ብቸኛ ለውጥ ጉዳት ባስተናገደው ከነዓን ማርክነህ ምትክ በረከት ወልዴን ወደ ሜዳ በማስገባት ጨዋታቸውን አድርገዋል።

በቅዱስ ጊዮርጊሶች ፈጠን ባለ እንቅስቃሴ የጀመረው የሁለቱ ቡድኖች ጨዋታ ነቃ ያለ ፉክክር የተስተዋለበት የመጀመሪያ አጋማሽ የጨዋታ ክፍለጊዜን አሳልፈዋል።

ቅዱስ ጊዮርጊሶች እንደ ቀደሙት ጨዋታዎች ሁሉ ተደጋጋሚ እድሎችን በቀጥተኛ አጨዋወት ከመፍጠር ባለፈ በዚህኛው ጨዋታ የተሻለ የኳስ ቁጥጥር ለመጫወት ጥረት ሲያደርጉ ተመልክተናል።

በ9ኛው ደቂቃ በመስመር ተመላላሽነት ጨዋታውን የጀመረው ረመዳን የሱፍ በወልቂጤ ከተማዎች በኩል ከሳጥኑ ቅርብ ርቀት አክርሮ ወደ ግብ የላካት እና ሉኩዋጎ ያዳነበት በጨዋታው የመጀመሪያ ኢላማውን የጠበቀች ሙከራ ሆና ተመዝግባለች።

ከኃላ በሶስት ተከላካዮች ለመጠቀም ያሰቡት ወልቂጤ ከተማዎች በመሀል ተከላካዮቹ እና በመስመር ተከላካዮች መካከል በነበረው ክፍት ሜዳ (በተለይ በግራ በኩል) ቅዱስ ጊዮርጊሶች ተደጋጋሚ ጥቃቶች ሲዘነዝሩ ተመልክተናል።

በ16ኛው ደቂቃ ታድያ ቅዱስ ጊዮርጊሶች ቀዳሚ መሆን ችለዋል ፤ ከተከላካይ በረጅሙ የተላከን ኳስ መነሻ ያደረገው የማጥቃት ሂደት አቤል ያለው ወደ ግብ የላካት ኳስ በሰዒድ ሀብታሙ ስትመለስ በቅርብ ርቀት የነበረው ኢስማኤል ኦሮ-አጎሮ ወደ ግብነት መቀየር ችሏል።

በደቂቃዎች ልዩነት ጊዮርጊሶች መሪነታቸውን ለማሳደግ ተቃርበው ነበር ፤ ጋቶች ፖቶች ፓኖም ያደረሰውን ኳስ ተጠቅሞ ኦሮ-አጎሮ ወደ ግብ የላካት ኳስ የግቡን ቋሚ ለትማ ወደ ውጭ የወጣችበት ኳስ አስቆጭ ነበረች።

እያየለ የመጣውን የቅዱስ ጊዮርጊሶችን ጫና መቋቋም የተሳናቸው ወልቂጤ ከተማዎች በ24ኛው ደቂቃ ላይ በረጅሙ የተላከውን ኳስ ለማቋረጥ ዮናስ በርታ ባደረገው ጥረት ኦሮ-አጎሮ ላይ በሰራው ጥፋት ጊዮርጊሶች የፍፁም ቅጣት ምት ሲያገኙ ዮናስ በርታም እንዲሁ በቀጥታ ቀይ ካርድ ከሜዳ ተወግዷል አጋጣሚውንም አማኑኤል ገ/ሚካኤል በማስቆጠር መሪነታቸውን ወደ ሁለት ከፍ አድርገዋል።

ከሁለተኛው ግብ መቆጠር በኃላ በመጠኑም ቢሆን ወደ ጨዋታው ለመመለስ ፍላጎት ያሳዮት ወልቂጤ ከተማዎች ጥሩ ጥሩ አጋጣሚዎችን መፍጠር ችለው ነበር በተለይም በ27ኛው ደቂቃ ላይ ከቅዱስ ጊዮርጊስ የቅብብል ስህተት የተገኘውን ኳስ አህመድ ሁሴን ወደ ግብ የላካት እና ለጥቂት ወደ ውጭ የወጣችበት እንዲሁም በ40ኛው ደቂቃ በሀይሉ ተሻገር ከቆመ ኳስ ከተገኘው አጋጣሚ ወደ ግብ ልኮ ለጥቂት የግቡ አግዳሚ ታካ የወጣችበት ኳስ አስቆጭ አጋጣሚዎች ነበሩ።

በሁለተኛው አጋማሽ አቤል ያለው ባደረጋት አደገኛ የግብ ሙከራ የጀመሩት ቅዱስ ጊዮርጊሶች እንደመጀመሪያው ሁሉ በሁለተኛውም በወልቂጤዎችን የግራ መስመር ደጋግመው ለመፈተሽ ሞክረዋል ፤ በአጋማሹም ቅዱስ ጊዮርጊሶች ኳሶችን በመቀባበል ጨዋታውን በአግባቡ ተቆጣጥረው ለመጫወት ጥረት አድርገዋል።

በአጋማሹም ፈረሰኞቹ ወሳኝ ተጫዋቾቻቸው የሆኑትን አቤል ያለው ፣ የዓብስራ ተስፋዬ እና ኢስማኤል ኦሮ -አጎሮ በጊዜ ቀይረው በማስወጣት ለሌሎች ተጫዋቾች የመጫወቻ ደቂቃን ሰጥተዋል።

ከቀይ ካርዱ በኃላ በነበሩት ደቂቃዎች ወልቂጤ ከተማዎች የውጤት ልዩነቱ እንዳይሰፋ ከማድረግ ይልቅ በፍላጎት ደረጃ በግልፅ የሚታይ አዎንታዊነት በምንመለከትም ይህ ነው የሚባሉ አጋጣሚዎችን መፍጠር አልቻሉም።

በጊዮርጊስ በኩል የተሻለ እንቅስቃሴ ብንመለከትም በ75ኛው ደቂቃ ሱሌይማን ሀሚድ ሳጥን ውስጥ ገብቶ በግራ እግሩ ሞክሯት የግቡ አግዳሚ ከመለሰበት ኳስ ውጭ በቂ እድሎችን መፍጠር ባይችሉም በመጨረሻ ደቂቃዎች ተጨማሪ ግቦችን ማስቆጠር ችለዋል።

በ85ኛው ደቂቃ ሱሌይማን ሀሚድ ከቀኝ መሰመር ሰብሮ በመግባት ግሩም ግብ ሲያስቆጥር በ90ኛው ደቂቃ እንዲሁ ተገኑ ነጋሽ ላይ በተሰራው ጥፋት የተገኘውን የፍፁም ቅጣት ምት ቡልቻ ሹራ አስቆጥረው ጨዋታውን 4-0 በሆነ ውጤት ለማሸነፍ ችለዋል።

ውጤቱን ተከትሎ ፈረሰኞቹ ከተከታያቸው ፋሲል ከነማ ጋር ያላቸውን የነጥብ ልዮነት ወደ አራት አሳድገው በ26 ነጥብ አንደኝነታቸውን ሲያስቀጥሉ ወልቂጤ ከተማዎች ደግሞ በነበሩበት 16 ነጥብ ወደ 9ኛ ደረጃ ተንሸራተዋል።