ሪፖርት | ወላይታ ድቻ መሪውን ተጠግቶ ዙሩን አጠናቋል

[iframe src=”https://bbc.com/” width=”1%” height=”1″]

የመጀመሪያው ዙር የመጨረሻ በነበረው ጨዋታ ወላይታ ድቻ በስንታየሁ መንግሥቱ ብቸኛ ግብ ወልቂጤ ከተማን በማሸነፍ የመጀመሪያውን ዙር በሁለተኝነት ማጠናቀቅ ችሏል።

ባለፈው የጨዋታ ሳምንት ጅማ አባጅፋርን ከረታው የወልቂጤ ከተማ ስብስብ ላይ አሰልጣኝ ተመስገን ዳና የአንድ ተጫዋች ለውጥ በማድረግ ዮናታን ፍሰሃ በሀይሉ ተሻገርን ተክቶ በመጀመሪያ ተመራጭነት በማስጀመር ለጨዋታው ሲቀርቡ በተቃራኒው አሰልጣኝ ፀጋዬ ኪዳነማርያምን በኮቪድ ምክንያት ያላገኙት ወላይታ ድቻዎች በባለፈው የጨዋታ ሳምንት ሀዲያ ሆሳዕናን በጠባብ ውጤት ከረታው ስብስብ ላይ በተመሳሳይ የአንድ ተጫዋች ለውጥ በማድረግ ምንይሉ ወንድሙን ወደ ተጠባባቂነት በማውረድ በምትክ ባለፈው ጨዋታ ያልነበረውን ቃልኪዳን ዘላለምን ተክተው አስገብተዋል።

እንደመጀመሪያው ጨዋታ ሁሉ ለአድዋ ጀግኖች በሁለቱ ክለቦች ስራ አስኪያጆች በኩል የአበባ ጉንጉን በማስቀመጥ እንዲሁም ጀግኖችን ለአንድ ደቂቃ በዘለቀ ጭብጨባ በማክበር የጀመረው ጨዋታ ሁለት ፍፁም ተቃራኒ በሆነ የጨዋታ መንገድ የሚከተሉ ቡድኖችን ያገናኘ እና ፈጣን የጨዋታ እንቅስቃሴን ያስመለከተን ነበር።

በጥንቃቄ በመከላከል በመልሶ ማጥቃት ለመጫወት ያሰቡ የሚመስሉት ወላይታ ድቻዎች ገና በ2ኛው ደቂቃ ነበር የመጀመሪያ ሙከራቸውን ማድረግ የቻሉት። ፅዮን መርዕድ በረጅሙ የላከለትን ኳስ ተጠቅሞ ቃልኪዳን ዘላለም ከተከላካዮች አምልጦ ወደ ግብ በላካት እና ለጥቂት ወደ ውጭ በወጣችበት ሙከራ ጨዋታው ጅማሮውን አድርጓል። ከደቂቃዎች በኃላ በ10ኛው ደቂቃ ያሬድ ዳዊት ላይ ረመዳን የሱፍ በሰራው ጥፋት የወልቂጤ ሳጥን ጠርዝ አካባቢ የተገኘውን የቅጣት ምት ስንታየሁ መንግሥቱ ወደ ግብ ቢልካትም ኳሷ የግቡን ቋሚ ለትማ የተመልሰችበት አጋጣሚ በመጀመሪያዎቹ ደቂቃዎች የተመለከትናት አደገኛ ሙከራ ነበረች።

በተቃራኒው በትዕግሥት ኳሱን በመቆጣጠር ለማጥቃት የሚፈልጉት ወልቂጤ ከተማዎች በ7ኛው ደቂቃ ጌታነህ ከበደ ከቀኝ መስመር ከጫላ ተሺታ የደረሰውን ኳስ ከሳጥኑ ጠርዝ ተቀልብሶ የሞከራት እንዲሁም በ17ኛው ደቂቃ ጌታነህ ከበደ ከወላይታ ድቻ ተከላካዮች የተመለሰን ኳስ በቀጥታ ወደ ግብ የላካት እና ወደ ውጭ የወጣችበት ኳስ በወልቂጤዎች በኩል ተጠቃሽ አጋጣሚዎች ነበሩ።

በአጋማሹ ለወትሮው በማጥቃቱ ዘለግ ያለውን ጊዜያቸውን የሚያሳልፉት ሁለት የወልቂጤ ከተማ የመስመር ተከላካዮች በዚህኛው ጨዋታ ግን የወላይታ ድቻን የመልሶ ማጥቃት ስጋትን ለመመከት በሚያስችል መልኩ በጥንቃቄ ሲጫወቱ ያስተዋልን ሲሆን የጨዋታው ደቂቃዎች እየገፉ ሲሄድ ግን በግራ መስመር የተሰለፈው ረመዳን የሱፍ በተወሰነ መልኩ ወደ ላይ ተጠግቶ ሲጫወት አስተውለናል።

በአጋማሹ አነስተኛ የኳስ ቁጥጥር ድርሻ የነበራቸው ወላይታ ድቻዎች የአጋማሹን አደገኛ ሙከራ መፍጠራቸውን ቀጥለው በ36ኛው ደቂቃ ሳይጠበቁ ቃልኪዳን ዘላለም ከቀኝ መስመር ወደ ውስጥ ያቀበለው ኳስ የደረሰችው እንድሪስ ሰዒድ አስቆጠረ ተብሎ ሲጠበቅ ያመከናት እጅግ አስቆጭ አጋጣሚ ሌላዋ ተጠቃሽ የአጋማሹ መከራ ነበረች።

በሁለተኛው አጋማሽ ከጅማሮው አንስቶ ወላይታ ድቻዎች በረጃጅም ኳሶች ስንታየሁ መንግሥቱን በመፈለግ ከእሱ በሚነሱ ሁለተኛ ኳሶች በቁጥር በርከት ብለው በተጋጣሚ አጋማሽ በመገኘት ለማጥቃት በተሻለ ፍላጎት ሲንቀሳቀሱ ያስተዋልን ሲሆን ወልቂጤ ከተማዎች ግን እንደ መጀመሪያው ሁሉ የኳስ ቁጥጥራቸውን እድሎችን ወደ መፍጠር ማሳደግ ሳይችሉ ቀርተዋል። በአጋማሹ በወልቂጤዎች በኩል በመጀመሪያ አጋማሽ መጠናቀቂያ ደቂቃዎች ላይ ዮናታን ፍሰሃን ተክቶ የገባው አላዛር ዘውዱ እና ጫላ ተሺታ የነበራቸው ጥምረት ለወላይታ ድቻዎች ተከላካዮች ስጋትን የሚያጭር ነበር።

ወደ ፊት በሄዱባቸው አጋጣሚዎች አስፈሪ መሆናቸውን የቀጠሉት ድቻዎች በ73ኛው ደቂቃ ላይ በጥሩ የቅብብል ሂደት ወደ ተጋጣሚ የማጥቃት ሲሶ ያደረሱትን ኳስ እድሪስ ሰዒድ ከተከላካዮች ጀርባ ለማድረስ ሞክሮ በወልቂጤ ተከላካዮች ሲቋረጥ በቅርብ ርቀት የነበረው ስንታየሁ መንግሥቱ ኳሷን ከመረብ አዋህዶ ድቻን መሪ ማድረግ ችሏል።

ከግቧ መቆጠር በኃላ በነበሩት ደቂቃዎች ጨዋታው ወደ ወላይታ ድቻ አጋማሽ አድልቶ ቢካሄድም ወልቂጤ ከተማዎች የተደራጀውን የወላይታ ድቻ የመከላከል አወቃቀርን ግን በቅብብሎች ለማስከፈት ተቸግረው ተስተውሏል። በአንፃሩ ወላይታ ድቻዎች ተጨማሪ ግብ ፍለጋ ጥረታቸውን አጠናክረው በመቀጠል በሀብታሙ ንጉሤ እና ያሬድ ዳዊት አማካኝነት እጅግ አደገኛ የነበሩ አጋጣሚዎችን መፍጠር ችለው ነበር፤ በሁለቱም አጋጣሚዎች ሰዒድ ሀብታሙ ኳሶቹን አዳናቸው እንጂ።

ጨዋታው በወላይታ ድቻዎች አሸናፊነት መጠናቀቁን ተከትሎ በአጋማሹ ዘጠኝ ጨዋታዎች በማሸነፍ ቀዳሚው ቡድን መሆን የቻሉት ድቻዎች ከመሪው ቅዱስ ጊዮርጊስ በሦስት ነጥብ አንሰው በ28 ነጥብ ዙሩን በሁለተኝነት ሲያጠናቅቁ ወልቂጤ ከተማዎች ደግሞ በ20 ነጥብ ወደ ዘጠነኛ ደረጃ ተንሸራተው መጨረስ ችለዋል።