​የአሠልጣኞች አስተያየት | ወልቂጤ ከተማ 0-1 ወላይታ ድቻ

[iframe src=”https://bbc.com/” width=”1%” height=”1″]

120ኛው የሊጉ መርሐ-ግብር በወላይታ ድቻ አሸናፊነት ከተጠናቀቀ በኋላ ሦስት ነጥብ ያገኙት እና ያስረከቡት አሠልጣኞች አስተያየት ሰጥተዋል።

ጣሰው ታደሠ – ወላይታ ድቻ (ምክትል አሠልጣኝ)

ጨዋታው እንዴት ነበር?

ጨዋታው ጥሩ ነበር። ዛሬ አሸንፈናል። ዋና አሠልጣኛችን አብሮን ሆኖ የደስታችን ተካፋይ ቢሆን ደስ ይለኝ ነበር። ግን አልሆነም። ጨዋታው ግን በሁለቱም በኩል ጥሩ ነበር። መጀመሪያም ትኩረት ሰጥተን ነበር። በወልቂጤ በኩል ልምድ ያላቸው እና አብዛኛው ነባር የሆኑ ስለነበር ትኩረት ሰጥተን ነው ወደ ሜዳ የገባነው። ፈጣሪ ረድቶን ስኬታማ ሆነናል።


ዛሬ ያስመዘገቡት ውጤት በሁለተኛው ዙር ስለሚያደርግላቸው መነቃቃት?

የምናስተካክላቸው ነገሮች ይኖራሉ። እቅድ አንድ እቅድ ሁለት የሚባል ነገር አለ። በጎደሉ ቦታዎች አሟልተን በእረፍት ጊዜ በደንብ ሰርተን ለሁለተኛው ዙር ጥሩ ተፎካካሪ ለመሆን ነው ሀሳባችን። በይበልጥ እኛ ወደ ሜዳ ስንገባ አልሸነፍ ባይነቱ አለ። ሁለተኛ የተቃራኒ ቡድን እና ዳኛን ያከብራሉ። በዚሁ አጋጣሚ የድሬዳዋ ህዝብ ኳስ የሚወድ ነው። ማመስገን ይገባኛል። በሜዳውም ደስተኛ ነኝ።


ተመስገን ዳና – ወልቂጤ ከተማ


ስለተሸነፉበት ምክንያት?

ተጋጣሚያችን ጠንካራ ቡድን ነው። በእርግጥ በመጀመሪያው አጋማሽ ከተጋጣሚያችን በተሻለ ወደ ጎል ደርሰናል። እነዛን ዕድሎች መጠቀም አለመቻላችን መጨረሻ ላይ ተጎጂ አድርጎን ውጤት እንድናጣ አድርጎናል። የተለየ አቀራረብ ነበር የቀረብነው። ማሸነፍ አልቻልንም። ይገጥማል።


የድቻን የጨዋታ መንገድ ለማምከን ሁለተኛ ዕቅድ ስላለመጠቀማቸው?

እኛ ሁለተኛ እቅድ ብለን የምናስበው በምንፈልገው አጨዋወት ውስጥ የተሻሉ ተጫዋቾችን እያስገባን ዕድሎችን መሞከር ነው። በቅያሪዎች ጨዋታውን ለመቀየር ሞክረናል። ነገርግን ሊሳካልን አልቻለም። የእነሱን አጨዋወት ለማቆም የመጣንበት መንገድ ግን እስከ ተወሰኑ ደቂቃዎች ጥሩ አድርጎናል። በኋላ ግን ያንን ማስቀጠል አለመቻላችን ነው።