ዋልያው ከሜዳው ውጪ ጥሩ በተንቀሳቀሰበት የአቋም መፈተሻ ጨዋታ ተረቷል

[iframe src=”https://bbc.com/” width=”1%” height=”1″]


ከኮሞሮስ አቻው ጋር የአቋም መፈተሻ ጨዋታ ያደረገው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን 2-1 በሆነ ውጤት ተሸንፏል።

ጨዋታውን ለመጀመር አሠልጣኝ ውበቱ አባተ በግብ ብረቶቹ መሐል ፋልሲ ገብረሚካኤልን በማቆም በተከላካይ መስመር ላይ አስራት ቱንጆ፣ ምኞት ደበበ፣ ያሬድ ባየህ እና ረመዳን የሱፍን አሰልፈዋል። በ4-3-3 የተጫዋች አደራደር ቅርፅ በአማካይ መስመር ላይ በአማኑኤል ዮሐንስ ዳር እና ዳር ሱራፌል ዳኛቸው እንዲሁም ሽመልስ በቀለ ሲሰለፉ ዳዋ ሆቴሳ፣ አቡበከር ናስር እና አማኑኤል ገብረሚካኤል ደግሞ የፊት መስመሩን እየመሩ ወደ ሜዳ ገብተዋል።

ቀዝቀዝ ብሎ የጀመረው የሁለቱ ቡድኖች ጨዋታ በ7ኛው ደቂቃ በመጀመሪያ ዒላማውን በጠበቀ ሙከራ ግብ አስተናግዷል። በዚህም ባለ ሜዳዎቹ ኮሞሮሶች ለማጥቃት ሲሞክሩ የኢትዮጵያ ተከላካዮች ለማውጣት የጣሩትን ኳስ ሳጥን ውስጥ ራሱን ነፃ አድርጎ ቆሞ የነበረው ፋይዝ ማቶር አግኝቶት በጥሩ ሁኔታ ወደ ግብነት ቀይቶታል።

በጊዜ ግብ ያስተናገዱት የኢትዮጵያ ተጫዋቾች በ11ኛው ደቂቃ የቆመን ኳስ መነሻ በማድረግ ምላሽ ለመስጠት ሞክረው ለጥቂት ወጥቶባቸዋል። በዝናባማው የዐየር ሁኔታ በቀጠለው ጨዋታ ኮሞሮሶች በ19ኛው ደቂቃ ሌላ የሰላ ጥቃት ሰንዝረው የግብ ዘቡ ፋሲል አምክኖታል። ከሁለት ደቂቃዎች በኋላ ግን ፋሲል ከግራ መስመር የተሻማን ኳስ በሚገባ መቆጣጠር ተስኖት ራሱን ለአደጋ ዳርጎ ነበር።

በኳስ ቁጥጥሩ ረገድ የተሻለ ድርሻ የነበራቸው ዋልያዎቹ ወደ ጨዋታው ለመመለስ ባደረጉት ጥረት ግልፅ የግብ ማግባት ዕድሎችን አግኝተዋል። ለአብነት በ35ኛው ደቂቃ በፈጣን እንቅሰቃሴ ረመዳን ከተከላካዮች ጀርባ ተገኝቶ ጥሩ ዕድል ሲፈጥር በ38ኛው ደቂቃ ደግሞ አማኑኤል ገብረሚካኤል በተመሳሳይ መስመር ሰፊ የመጫወቻ ሜዳ በማግኘት ወደ ግብ የላከው ኳስ ቋሚውን ታካ ወደ ውጪ ወጥታለች። የመጀመሪያው አጋማሽ ሊጠናቀቅ 2 ደቂቃዎች ሲቀሩት ደግሞ ዳዋ በተቃራኒ አቅጣጫ ፍጥነቱን ተጠቅሞ ኳስ እየገፋ በመሄድ ሳጥን ደርሶ የሞከረውን ኳስ ግብ ጠባቂው ዓሊ አህማዳ አምክኖበታል።

በርከት ያሉ ተጫዋቾችን አከታትለው የቀየሩት ኮሞሮሶች በሁለተኛው አጋማሽ የመጀመሪያ ደቂቃዎችም መጠነኛ ጫና ከዋልያው ሲደርስባቸው ነበር። የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድንም በመጀመሪያው አጋማሽ የነበረውን የኳስ ድርሻ ፍጥነት በመጨመር ወደ ላይኛው የሜዳ ክፍል ለመድረስ ጥረት አድርጓል። ነገር ግን ኳስ እና መረብን የሚያገናኝላላቸው ተጫዋች አጥተው በ65ኛው ደቂቃ ሦስት የማጥቃት ባህሪ ያላቸው ተጫዋቾችን (በረከት፣ ቢኒያም እና መስፍን) ቀይረው አስገብተዋል።

በአሠልጣኝ ዩነስ ዜርዱክን የሚመሩት ኮሞሮሶች በ59ኛው ደቂቃ ቀይረው ወደ ሜዳ ባስገቡት አብደላ ዓሊ መሐመድ አማካኝነት ሁለተኛ ጎል አስቆጥረው መሪነታቸውን አሳድገዋል። በመጨረሻው የማጥቃት ሲሶ ጥራት ያላቸው ዕድሎችን የመፍጠር እና የተገኙትን ደግሞ የመጨረስ ችግር የታየበት የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን በ79ኛው ደቂቃ ሱራፌል ዳኛቸው ከሳጥን ውጪ አክርሮ በቀኝ እግሩ በመታው ኳስ ግብ አግኝተዋል። በተቀሩት ደቂቃዎች ተጋባዦቹ ዘለግ ያለውን ጊዜ ኮሞሮስ ሜዳ ቢያሳልፉም የአቻነት ግብ ማግኘት ተስኗቸው ጨዋታው በኮሞሮስ 2-1 አሸናፊነት ተጠናቋል።