ቅድመ ዳሰሳ | ሲዳማ ቡና ከ ቅዱስ ጊዮርጊስ

የ20ኛ ሳምንት ተጠባቂ ጨዋታ ዙርያ ተከታዩ ዳሰሳ ተሰናድቷል።

በዋንጫ ፉክክር ውስጥ ያሉት ሲዳማ ቡና እና ቅዱስ ጊዮርጊስ ነገ 12 ሰዓት የሚያደርጉት ፍልሚያ ትልቅ ትኩረት ተሰጥቶታል። ወረቀት ላይ ባለ ሜዳ የሆነው ሲዳማ ቡና ባሳለፍነው ሳምንት ሰበታ ላይ ባገኘው ድል ተነሳስቶ ያለመሸነፍ ግስጋሴውን ወደ 13 ለማሳደግ እና የሊጉ መሪ ላይ ለመድረስ የሚያደርገውን ግስጋሴ ለማፋጠን በነገው ጨዋታ ሦስት ነጥብን ለማግኘት እንደሚጥር ሲጠበቅ በደረጃ ሰንጠረዡ አናት የተቀመጠው ቅዱስ ጊዮርጊስ በበኩሉ በሊጉ ያለውን ያለመሸነፍ ግስጋሴ ለማስቀጠል፣ ከአራት ተከታታይ ድሎች በኋላ ከገጠመው የአቻ ውጤት ለማገገም እና ቀጥተኛ ተፎካካሪው የሆነውን ሲዳማን ረቶ ግስጋሴውን ለማሳመር ድልን እያሰላሰለ ጨዋታውን እንደሚቀርብ ይገመታል።

ከነገ ተጋጣሚው ቅዱስ ጊዮርጊስ በመቀጠል በሊጉ ጥቂት ጨዋታዎችን የተረታው ሲዳማ ቡና በአምስቱም የጨዋታ ምዕራፎች ራሱን ከጨዋታ ጨዋታ እያጎለበተ ይገኛል። ባሳለፍነው ሳምንትም በደረጃ ሰንጠረዡ ግርጌ የተቀመጠውን ነገር ግን በእንቅስቃሴ እያደገ የመጣውን ሰበታ ገጥሞ ሦስት ግብ እና ነጥብ ወስዶበታል። ቡድኑ የፈጣሪው የአጥቂ አማካይ ፍሬው ሰለሞን አለመኖርን ተከትሎ መሐል ለመሐል ከሚደረጉ ጥቃቶች ወደ መስመር በማድላት የግብ ምንጭ ለማግኘት የታተረ ሲሆን የመስመር ተከላካዮቹ አማኑኤል እንደለ እና መሐሪ መና ወደ ፊት ተጠግተው እንዲጫወቱ ተደርጎ ድሮም ችግር ያለበትን የሰበታ የኋላ መስመር ይበልጥ ለመዘርዘር ጥረው ፍሬያማ ሆኗል። የነገው ተጋጣሚ ጊዮርጊስ ግን የሊጉ ጠንካራው የኋላ መስመር ባለቤት ስለሆነ እንዲሁ በቀላሉ የግብ መረቡን ለማግኘት አይቻልም።

የቡድኑን የግብ ማስቆጠር ሀላፊነት ለብቻው እስከሚመስል ድረስ ተሸክሞ የነበረው ይገዙ ቦጋለ ባሳለፍነው ሳምንት ጫናውን የሚጋራለት ሁነኛ ሰው ያገኘ መስሏል። በዚህም በአጋማሹ የዝውውር መስኮት ቡድኑን የተቀላቀለው ሳላዲን ሰዒድ ሐት-ሪክ በመስራት የፊት መስመሩን የበለጠ አስሎታል። ይህ ሳላ-ይገዙ ጥምረት ደግሞ በደንብ እየተዋሀደ ሲሄድ የገብረመድህን ስብስብ የበለጠ አስፈሪ ሊሆን ይችላል። ሳላዲን ወደ ጨዋታ በተመለሰ በአጭር ጊዜ ግብ ማምረት መጀመሩ የሚፈጥርለት የራስ መተማመን በነገው ጨዋታ ለጊዮርጊስ ተከላካዮች ፈተናቸውን የሚያብስ ነው። ከሳላዲን በተጨማሪ በቅጣት ምክንያት የሰበታው ጨዋታ ያለፈው ፍሬው ሰለሞን መመለስ በማጥቃቱ በኩል ያለውን እንቅስቃሴ የሚያጠናክር ነው። በመከላከሉ ረገድ ካለፉት 12 ጨዋታዎች 5 ጊዜ ብቻ ግቡን ያስደፈረው የኋላ መስመር ካለፉት ጨዋታዎች አንፃር የተሻለ የፊት መስመር ያለው ቡድን ስለሚገጥም በሚገባ ተጠንቅቆ መጫወት ይጠበቅበታል።

በብዙ መስፈርቶች በየጨዋታው ድንቅ የሆነው ቅዱስ ጊዮርጊስ በበኩሉ በአስቆጪ ሁኔታ በመከላከያ ሁለት ነጥብ በጣለበት ፍልሚያ ከቡድኑ እንቅስቃሴ በላይ መነጋገሪያ የነበረው ዕድለ ቢስነቱ ነበር። በጨዋታው ተቆጥሮ ሳይፀድቅ ከቀረው ጎል ውጪም በርካታ የጠሩ የግብ ዕድሎችን ፈጥሮ ወደ ግብ መቀየር ሳይሳካለት ቀርቷል። በተለይ በሁለተኛው አጋማሽ ከየአቅጣጫው ሲሰነዘሩ የነበሩ አጋጣሚዎችን የመከላከያው የግብ ዘብ በጥሩ ብቃት ማዳኑ ሦስት ነጥብ እንዳያገኙ አድርጓቸዋል። የሆነው ሆኖ ግን ቡድኑ እንደ ተለመደው በፈጣን እና ቀጥተኛ አጨዋወት እንዲሁም በቆሙ ኳሶች መሪ ለመሆን የተንቀሳቀሰ ሲሆን ለወትሮ የነበረው ስልነት ግን አለመኖሩ ዋጋ አስከፍሎታል። የነገው ተጋጣሚ ሲዳማ ደግሞ በመከላከል አደረጃጀት ጥሩ የሆነ እና ለተጋጣሚ እምብዛም ክፍተት የማይሰጥ በመሆኑ የፊት መስመሩን አይምሬነት አሳድጎ መምጣት ይገባዋል። ከዚሁ ጋር ተያይዞ ግን ሲዳማ እንደ መከላከያ በጣም ወደ ታች ወረድ ብሎ የሚከላከል ባለመሆኑ መጫወቻ ቦታን ከተከላካይ ፊት እና ኋላ ሊያገኝ ይችላል።

ኳስን በመቆጣጠር ፣ ሽግግሮችን እና የመልሶ ማጥቃትን በመተግበር እንዲሁም የቆሙ ኳሶችን በመጠቀም ራሱን ያጠናከረው ጊዮርጊስ የመከላከያው ጨዋታ ከተገባደደ በኋላ የቡድን አባላቱ ላይ የታየው ቁጭት እና ረሀብ አስገራሚ ነበር። ይህ የማሸነፍ ፍላጎት ደግሞ ነገ አድጎ ከመጣ ለሲዳማ እጅግ ፈተና ነው። ከወገብ በላይ ያሉት ተጫዋቾች ፍጥነት ደግሞ ጨዋታውን የመወሰን ሀይል ስላለው ሲዳማዎች እንደ ሰበታው ጨዋታ በሙሉ ሀሳባቸው ወደ ፊት መሄድ ብቻ መሆን የለበትም። ጊዮርጊስ ከፍተኛ ግብ አስቆጣሪውን ኦሮ-አጎሮን ቢያጣም ከየአቅጣጫው ግብ የሚያስቆጥርለት አላጣም። በጨዋታ በአማካይ ወደ ሁለት የተጠጋ (1.8) ጎል የሚያገባው ቡድኑም ጥሩ ጥምረት ላይ ያሉ ለሚመስለው ጊት እና ያኩቡ ከፍ ያለ የሜዳ ላይ ስራ እንደሚሰጥ ይገመታል።

ሲዳማ ቡና ይገዙ ቦጋለን በ5 ቢጫ ምክንያት በነገው ጨዋታ የማያገኝ ሲሆን ቅዱስ ጊዮርጊስ ደግሞ ከደረሰበት ጉዳት በመጠኑ እያገገመ ከሰሞኑን ቀለል ያለ ልምምድ የጀመረው እስማኤል ኦሮ-አጎሮን ያጣል።

ተጠባቂውን ጨዋታ ቢኒያም ወርቅአገኘሁ ከረዳታቸው ፋሲካ የኋላሸት እና አማን ሞላ እንዲሁም ከአራተኛ ዳኛው ተካልኝ ለማ ጋር በመሆን የሚመሩት ይሆናል።

እርስ በርስ ግንኙነት

– 23 ጊዜ ተገናኝተው ቅዱስ ጊዮርጊስ 14 በማሸነፍ ቀዳሚ ሲሆን 7 ጨዋታዎች አቻ ተለያይተው ሲዳማ ቡና 2 ጊዜ አሸንፏል። በ23ቱ ግንኙነት ጊዮርጊስ 31 ግቦችን ሲያስቆጥር ሲዳማ ደግሞ 11 ጊዜ ኳስ እና መረብን አገናኝቷል።

ግምታዊ አሠላለፍ


ሲዳማ ቡና (4-2-3-1)

ተክለማርያም ሻንቆ

አማኑኤል እንዳለ – ጊት ጋትኩት – ያኩቡ መሐመድ – መሐሪ መና

ዳዊት ተፈራ – ሙሉዓለም መስፍን

ብሩክ ሙሉጌታ – ፍሬው ሰለሞን – ሀብታሙ ገዛኸኝ

ሳላዲን ሰዒድ

ቅዱስ ጊዮርጊስ (4-2-3-1)

ቻርለስ ሉኩዋጎ

ሱለይማን ሀሚድ – ምኞት ደበበ – ፍሪምፖንግ ሜንሱ – ሄኖክ አዱኛ

ጋቶች ፓኖም – ሀይደር ሸረፋ

አቤል ያለው – የአብስራ ተስፋዬ – ቸርነት ጉግሳ

አማኑኤል ገብረሚካኤል