ሪፖርት | የፈረሰኞቹ ያለመሸነፍ ጉዞ እንደቀጠለ ነው

በተጠባቂው ጨዋታ ቅዱስ ጊዮርጊስ በጋቶች ፓኖም ብቸኛ ጎል ባድል ሆኗል።

ሲዳማ ቡና በሳላዲን ሰዒድ ሦስት ጎሎች ሰበታ ከተማን ከረታበት ስብስብ ይገዙ ቦጋለን በቅጣት እንዲሁም ተመስገን በጅሮዎንድን በማሳረፍ ፍሬው ሰለሞን እና ብርሀኑ አሻሞን ወደ አሰላለፍ ሲቀላቅል በአንፃሩ ቅዱስ ጊዮርጊስ ከመከላከያ ጋር ነጥብ ከተጋራበት ጨዋታ አጥቂውን አቤል ያለውን ብቻ በአዲስ ግዳይ በመተካት ለጨዋታው ቀርቧል።

በፈጣን እንቅስቃሴዎች ወደ ጎል በሚደረግ ምልልሶች እና የጎል ሙከራዎች ይደምቃል ተብሎ የተጠበቀው ጨዋታ ቀዝቀዝ ብሎ በጥንቃቄ የመጫወት ፍላጎቶችን ተስተውሎበታል። የጠራ የጎል ሙከራም ለማየት ስምንት ደቂቃዎች ለመጠበቅ ግድ ሆኗል። በተጠቀሰው ደቂቃም ቅዱስ ጊዮርጊስ ከግብ ጠባቂው ቻርለስ ሉክዋጎ በረጅሙ የተላከን ኳስ የአብስራ ተስፋዬ በጥሩ ሁኔታ ቢቆጣጠርም የመጨረሻው ውሳኔው ትክክል ባለመሆኑ ወደ ጎልነት ሳይቀይረው የቀረው አጋጣሚ አስቆጪ ነበር። በመስመር በሚገኙት ተጫዋቾች ላይ ያነጣጠረው ጨዋታ ቀጥሎ በ22ኛው ደቂቃ በሲዳማ በኩል የግብ ማግባት አጋጣሚ ተፈጥሮበታል። በዚህም ከሳጥኑ ውጭ ሀብታሙ ገዛኸኝ ኳሱን ለመቆጣጠር በሚያደርገው ጥረት ድንገት ሳላዲን ሰዒድ አግኝቶት ወደ ጎልነት ለመቀይር የመታው ኳስ ግብ ጠባቂው ሉክዋጎ አምክኖበታል። ብዙ ሳይቆይ ከዳዊት ተፈራ ከተከላካይ ጀርባ በጥሩ ሁኔታ የተጣለለትን ኳስ ሀብታሙ ገዛኸኝ ሳይቆጣጠራት ቀርቶ በቀላሉ ግብ ጠባቂው ቻርልስ በፍጥነት ደርሶ የያዘበት ሌላ ጎል ለማስቆጠር ሲዳማ ቡናዎች የቀረቡበት አጋጣሚ ነበር።

በጨዋታ እንቅስቃሴ ውስጥ በሚሰሩ ስህተቶች የጎል አጋጣሚ ለመፍጠር በሚደረግ ሁኔታ ካልሆነ በቀር ሁለቱ ቡድኖች መሐል ሜዳ ላይ በሚደረጉት የኳስ ንኪኪዎች ተጠምደው ወደ ፊት ለአጥቂዎች የሚደርሱ ኳሶች ሳንመለከት ዘለግ ያሉ ደቂቃዎችን ለመቆየት ተገደናል። ሆኖም ግን በአርባ ሦስተኛው ደቂቃ ፈረሰኞቹ ከቆሙ ኳስ የመጀመርያ ጎላቸውን አስቆጥረዋል። በተጠቀሰው ደቂቃም ቅዱስ ጊዮርጊስ ከቆሙ ኳሶች ለሚቆጠሩ ጎሎች መነሻ የሆነው ሄኖክ አዱኛ ያሻገረውን ኳስ የሲዳማ ቡና ተከላካዮች በሚገባ ማፅዳት ተስኗቸው ከመሐከላቸው ጋቶች ፓኖም ተገኝቶ ቀዳሚውን ጎል አግብቷል። አጋማሹም በፈረሰኞቹ መሪነት ተገባዷል።

ከመጀመርያው አጋማሽ የተለየ የሆነው የሁለተኛው አጋማሽ የጨዋታ ክፍለ ጊዜ በጅማሮው ከሀይደር ሸረፋ የተቀበለውን ኳስ ቸርነት ጉግሳ በጠባብ ሜዳ ተከላካይ በማለፍ ወደ ጎል ያሳለፈውን የሚጠቀም ተጫዋች ጠፍቶ የባከነው ኳስ ለፈረሰኞቹ ጨዋታውን ለመቆጣጠር የሚያስችል የጎል አጋጣሚ ነበር።

በይበልጥ በቸርነት ጉግሳ የግል ጥረት ታግዞ የማጥቃት አቅሙን ለማሳደግ ጥረት ያደረገው ቅዱስ ጊዮርጊስ በተደራጀ አጨዋወት የጎል ዕድሎችን ለመፍጠር ሲቸገር የተስተዋለ ሲሆን በአንፃሩ ከሁለት የተከላካይ አማካኝ መካከል ብርሃኑ አሻሞን ቀንሰው ተመስገን በጅሮንድን ቀይረው ካስገቡ በኋላ ለማጥቃት ፍላጎት ያሳዮት ሲዳማ ቡናዎች በ65ኛው ደቂቃ ከግራ መስመር አቅጣጫ ከቅጣት ፍሬው ሰለሞን በቀጥታ ወደ ጎል የመታውን ግብ ጠባቂው ሉክዋጎ እንደምን ወደ ውጭ ያወጣው ተጠቃሽ ነው። ፈረሰኞቹ በ67ኛው ደቂቃ ቀይረው ያስገቡት ከነዓን ማርክነህ በመጀመርያው ንክኪው ከቆመ ኳስ የተሻገረለትን ኳስ በግንባሩ ገጭቶ የግቡን አቅጣጫ ያለገኘው ኳስ እስከ ጨዋታው መጠናቀቂያ ድረስ ወደ ጎል የቀረቡበት አጋጣሚ ነው።

76ኛው ደቂቃ የጨዋታውን መንፈስ የሚቀይር ክስተት ተፈጥሯል። ይህውም ተቀይሮ ለመውጣት ሀይደር ሸረፋ የዕለቱን ዳኛ ቢኒያም ወርቅአገኘውን ውሳኔን በፀጋ ከመቀበል ይልቅ ያልተገባ ባህሪ በማሳየቱ በሁለት ቢጫ በቀይ ካርድ ወጥቷል። ከዚህ በኋላ ባሉት ቀሪ ደቂቃዎች ሲዳማ ቡናዎች የቅዱስ ጊዮርጊስን የቁጥር ማነስን ለመጠቀም ጥረት ቢያደርጉም ስኬታማ አልነበሩም።

ሙሉ የጨዋታ ክፍለ ጊዜው ተገባዶ በተጨማሪው ደቂቃ አማኑኤል ገብረሚካኤል ከመሐል ሜዳ የግል ጥረቱን በመጠቀም ወደፊት በመሄድ ከእርሱ በተሻለ አቋቋም ለሚገኙት የቡድን አጋሮቹ ማቀበል ሲችል በቀጥታ ወደ ጎል የመታውን ኳስ ግብ ጠባቂው ተክለማርያም ሻንቆ አድኖበታል። ቅዱስ ጊዮርጊሶች አንበላቸው ሀይደር በቀይ ካርድ ከወጣባቸው በኋላ በሙሉ አቅማቸው ለመከላከል የነበራቸው ጥንካሬ ዋጋ አስገኝቶላቸው ወሳኙን ሦስት ነጥብ አሳክተዋል።

ውጤቱን ተከትሎ ፈረሰኞቹ መሪነታቸውን አጠናክረው ነጥባቸውን አርባ አራት ሲያደርሱ ሲዳማዎች ደግሞ በዛው ሰላሳ አራት ነጥብ ረግተው ይቆያሉ።