​የአሰልጣኞች አስተያየት | ወልቂጤ ከተማ 1-1 ድሬዳዋ ከተማ

ወልቂጤ ከተማ ከድሬዳዋ ከተማ በአንድ አቻ ውጤት በተለያዩበት የምሽቱ ጨዋታ አሰልጣኞቹ አስተያየት ሰጥተዋል።

አሰልጣኝ ተመስገን ዳና – ወልቂጤ ከተማ

ስለ ጨዋታው

“የመጀመርያው አስር ደቂቃ ቡድናችን የተረጋጋ አልነበረም። ምክንያቱም መሀል ላይ ያሰለፍናቸው ተጫዋቾች አዲሶች ናቸው። በዚህ መነሻ የተወሰኑ አለመረጋጋቶች ነበሩ። ከዚህ በኋላ ራሳችንን ወደ ጨዋታው መልሰን ጥሩ መሆን ችለናል።

ስለአማካይ ክፍላቸው

“እንዲህ ሊመጡ እንደሚችሉ ገምተናል። የእኛ ቡድን መሀል ላይ ጥሩ እንደሆነ ስለሚታወቅ ያንን ማቆም እና ከዛ በኋላ በሚገኙ ዕድሎችን በመጠቀም ለማሸነፍ የሚፈልጉ ቡድኖች በርክተዋል። ዞሮ ዞሮ የእኛ አማካይ ያንን ትግል አሸንፈው መጨረሻ አቻ መውጣት ችለናል።

ግልፅ የጎል ዕድል መፍጠርን ስለማሻሻል

” እውነት ነው። ከባለፈው ጨዋታ ዛሬ የተሻሻልነው ነገር አለ። ግን ጎል መጨረስ ላይ ይቀረናል። አራት አምስት ተጫዋቾችን የተጋጣሚ የግብ ክልል ይደርሳሉ። የውሳኔ ችግሮች አሉብን። ያንን እያስተካከልን እንመጣለን።”

አሰልጣኝ ሳምሶን አየለ – ድሬዳዋ ከተማ

ስለጨዋታው

“ጨዋታው መጥፎ የሚባል አይደለም። ነገር ግን ጎል ያገባንበት ሰዓት መጀመርያ ሰዓት ስለነበር ምንአልበት ውጤት ለማስጠበቅ ስሜት ውስጥ ገብተው አብዛኛውን ሰዓት እነርሱ የጨዋታ ብልጫ ወሰዱብን። በሁለቱም አርባ አምስት የተለያየ የጨዋታ አቀራረብ ለመጠቀም ሞክረናል። የነበረው ነገር ግን ተመሳሳይ ነው። ምን አልባት ያለንበት ቀጠና የፈጠረው ነገር ነው። በቀጣይ በጎደለን ነገር ላይ ሰርተን ለመምጣት እንሞክራለን።

በመከላከል ላይ ስለማተኮራቸው

” እንደዛ ነው ማለት አይቻልም። ይዘው ይመጣሉ ብለን የገመትነው መሀል ሜዳ ላይ ብልጫ ይወስዳሉ ይሄንን ደግሞ ተቆጣጥረን በምናገኘው አጋጣሚ ለመጠቀም ነበር። ከዕቅድ አንፃር ጎሉን ያስቆጠርነው የዕቅዳችን አካል ነው። ነገር ግን የስሜት ጉዳይ ነው። ውጤት ለማስጠበቅ ማሰባችን ነው። አንዳንድ ጥፋቶቹ ጥፋት ነው ብዬ ለመውሰድ እቸገራለው ፤ ይህ የዳኛ ውሳኔ ነው። ዞሮ ዞሮ ውጤቱ መጥፎ አይደለም። በቀጣይ አስተካክለን እንመጣለን።

በሁለት ጨዋታ ስላሳከት አራት ነጥብ

“በምንፈልገው ልክ አይደለም። መጥፎ ነው ብሎ አይወሰድም። ከዚህ በተሻለ እንደሚጠበቅብን እናስባለን። ቀሪ አስር ጨዋታ ሠላሳ ነጥብ አለ። ሠላሳ ነጥብ እጅግ ብዙ ነው። ከፊት ከፊት ያለውን አስበን የቤት ሥራችንን ለማጠናቀቅ እንሞክራለን።”