ሪፖርት | የጨዋታ ሳምንቱ 5ኛ አቻ ተመዝግቦበታል

የምሽቱ የወልቂጤ ከተማ እና ድሬዳዋ ከተማ ጨዋታ በ1-1 ውጤት ተጠናቋል።

ወልቂጤ ከተማ ከሀዋሳው ሽንፈት ሰዒድ ሀብታሙ ፣ አበባው ቡታቆ እና አክሊሉ ዋለልኝን በማሳረፍ ለሮበርት ኦዶንካራ ፣ በኃይሉ ተሻገር እና ፋሲል አበባየሁን ወደ አሰላለፍ አምጥቷል።

በድሬዳዋ ከተማ በኩል ከጅማው ድል አንፃር ብሩክ ቃልቦሬ ፣ ከድር ኸይረዲን እና ዳንኤል ኃይሉ በአባይነህ ፊኖ ፣ አማረ በቀለ እና አብዱርሀማን ሙባረክ ቦታ ጨዋታውን ጀምረዋል።

ፈጠን ባለ እንቅስቃሴ የጀመረው ጨዋታ ጎል ለማስመልከትም ጊዜ አልወሰደበትም። ወልቂጤ ከተማዎች በኃይሉ ተሻገር ከቀኝ መስመር ያሻገረውን የቅጣት ምት ዮናስ በርታ በግንባር ሞክሮ ለጥቂት በወጣነት ኳስ ቀዳሚ ሙከራ ቢያደርጉም ድሬዎች ግን የመጀመሪያ ግብ አስቆጥረዋል። ይበልጥ በፈጠነ ከፍ ባለ የማጥቃት ሂደት ወደ ወልቂጤ ሜዳ ይደርሱ የነበሩት ድሬዳዋ ከተማዎች 4ኛው ደቂቃ ላይ እንየው ካሳሁን ከቀኝ መስመር ባሻገረው እና ሄኖክ አየለ ሁለተኛው ቋሚ ላይ ከተካላካዮች ጀርባ ገብቶ ባስቆጠረው ኳስ ቀዳሚ ሆነዋል።


በቀጣዮቹ ደቂቃዎች የድሬዳዋ ከተማዎች የማጥቃት ጫና ወዲያው ባይቀንም ወልቂጤዎች ቀስ በቀስ ወደ መረጋጋት በመምጣት በተሻለ ሁኔታ በተጋጣሚ ሜዳ ላይ መታየት ጀምረዋል። በዚህም ከአብዱልከሪም ወርቁ እና በኃይሉ ተሻገር በሚነሱ ኳሶች ጥሩ ዕድሎችን ቢፈጥሩም ደካማ አጨራረስ ኖሯቸው ታይተዋል። በተለይም 32ኛው ደቂቃ ላይ የፋሲል አበባየሁ እና ጌታነህ ከበደ ጥሩ ንክኪዎች ያለቀለት የሚባል ዕድል ፈጥረው በኃይሉ ከሳጥን ውስጥ ያደረገው ሙከራ ወደ ውጪ የወጣበት ቡድኑ ለግብ የቀረበበት ነበር።
በአጋማሹ ትኩረት ሳቢ ክስተት 40ኛው ደቂቃ ላይ ግቧን ያመቻቸው እንየው ካሳሁን በፋሲል አበባየሁ በደረሰበት ግጭት ከባድ ጉዳት አስተናግዶ በቢኒያም ጥዑመልሳን ተቀይሮ ለመውጣት ተገዷል።


ከዕረፍት መልስ ሁለቱም ቅያሪዎችን አድርገው ስመለሱ ወልቂጤዎች የአጥቂ ድሬዳዋዎች ደግሞ ጥሩ ሽፋን ለመስጠት በሚያስችል ቅርፅ የአማካይ ክፍላቸውን ቁጥር ጨምረው ተመልሰዋል። ድሬዳዋዎች እንደ ቀዳሚው አጋማሽ ሁሉ ጫና በመፍጠር የጀመሩ ሲሆን በሂደት ግን ወልቂጤዎች የኳስ ቁጥጥር የበላይነቱን በመውሰድ ጫና ፈጣሪነቱን ተረክበዋል። ሆኖም ቡድኑ በራሱ ሜዳ የሚቀረው ድሬዳዋን ለማስከፈት ጥረት ቢያደርግም የተሻሉ ዕድሎችን የፈጠረው ግን ከቆሙ ኳሶች ነበር። ድሬዳዋዎች በበኩላቸው ለመልሶ ማጥቃት የተመቸውን የተጋጣሚያቸውን ጀርባ ለማግኘት ጥረቶች ሲያደርጉ ነበር።
አካላዊ ንክኪዎች የበረከቱበት ጨዋታ ቀነስ ባለ ፉክክር የቀጠለ ሲሆን ወልቂጤዎች ኳስ ቁጥጥራቸው በፈለጉት መጠን ጥቃት ሰንዝረው ለመግባት ሳያስችላቸው ቀርተዋል። በተሻለ ሁኔታ 72ኛው ደቂቃ ላይ ተቀይሮ የገባው ያሬድ ታደሰ ከርቀት ያደረገው ሙከራ እና ከሦስት ደቂቃዎች በኋላ ጌታነህ ከበደ ከቅጣት ምት ያደረገውን ሙከራ ፍሬው ጌታሁን በአግባቡ ሳይቆጣጠር ቀርቶ ያገኙትን ዕድል ያልተጠቀሙበት ኳስ ተጠቃሽ ሙከራዎች ነበሩ።


በተመሳሳይ የወልቂጤ ኳስ ቁጥጥር እና የድሬዳዋ መልሶ ማጥቃት ጥረቶች በቀጠለው ጨዋታ የመሀል ዳኛው ዳንኤል ግርማይ ጋዲሳ መብራቴ በረመዳን የሱፍ ላይ በሰራው ጥፋት የፍፁም ቅጣት ምት ሰጠዋል። አጋጣሚውን ጌታነህ 82ኛው ደቂቃ ላይ አስቆጥሮ ጨዋታውን አቻ አድርጓል። ጌታነህ 86ኛው ላይም ከበኃይሉ ረጅም ኳስ በግንባሩ ያደረገው ሙከራ ለጥቂት የወጣ ነበር።
በቀሪዎቹ ደቂቃዎችም ድሬዎች ወደ ማጥቃት ጫናቸው መሸጋገር ከብዷቸው ሲታይ ወልቂጤዎች በተሻለ ሁኔታ አጥቅተው ቢጫወቱም ጨዋታው በአቻ ውጤት ተጠናቋል።

በዚህም መሰረት ወልቂጤ በ25 ነጥቦች 11ኛ ድሬዳዋ ከተማ ደግሞ በ21 ነጥቦች 13ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጠዋል።