የአሠልጣኞች አስተያየት | አርባምንጭ ከተማ 0-3 ወልቂጤ ከተማ

ሦስት ግቦች ከተስተናገዱበት ጨዋታ በኋላ አሠልጣኞች የድህረ-ጨዋታ አስተያየት ሰጥተዋል።

ተመስገን ዳና – ወልቂጤ ከተማ

ጨዋተቀው እንዴት ነበር?

ጨዋታውን ከእኛ የጨዋታ መንገድ ይልቅ ለማሸነፍ ያለን የማሸነፍ ጭንቀት መርቶታል ብዬ አስባለው። እንደ አጠቃላይ ማሸነፋችን ጥሩ ነው። ከዚህ በፊት ከነበሩት ጨዋታዎች የጎል ዕድል በመፍጠር እና በመጨረስ ላይ ተሻሽለናል። እንቅስቃሴያችን ግን እንደጠበቅነው አልነበረም።

ጨዋታው ሀይል የተቀላቀለበት ስለመሆኑ…?

የሁለታችን አጨዋወት ፍፁም የተለያየ ነው። የእኛ ቡድን ኳስ ተቆጣጥሮ የሚጫወት ነው። በተቃራኒው አርባ ምንጭ ቀጥተኛ አጨዋወት ነው የሚጫወተው። ከዚህ በፊት በነበራቸው ጨዋታ የሀይል አጨዋወት እንደሚጫወቱ እናውቃለን። ሜዳ ላይም የተፈጠረው ይሄ ነው።

ስለአበባው ጎል…?

ምንም ጥያቄ የለውም። ለእረፍት ስትወጣ አንድ ለባዶ እና ሁለት ለባዶ መምራት መልበሻ ክፍል የምታረገውን ምክር የተለየ ያደርገዋል። ስለዚህ የእርሱ ጎል ጨዋታውን ለማሸነፍ ቁልፉ ጎል ነው ማለት እችላለው።

ጌታነህ ከበደ ወደ ጎል አስቆጣሪነት መመለስ…?

ጌታነህ የሚታወቅ ነው። አስፈሪ አጥቂ ነው። ይበልጥ ያለፉትን አምስት ስድስት ጨዋታዎች እየጨመረ መጥቷል። ከዚህ በላይ መሄድ የሚያስችለው ነገርም አለው ብዬ አስባለው። ከፍተኛ ግብ አስቆጣሪ ሆኖ ይጨርሳል የሚል ተስፋም አለኝ።

ስለቀጣዩ የባህር ዳር ውድድር…?

በተወሰነ መልኩ ባህር ዳር ተጠናክረን እንሄዳለን ብዬ አስባለው። ባህር ዳር ለእኛ ቡድን አጨዋወት የሚሆን ነገር ይገጥመናል የሚል እምነት ይገጥመናል የሚል እምነት ስላለኝ እዛ የተሻለ ነገር እንጠብቃለን።

መሳይ ተፈሪ – አርባምንጭ ከተማ

ጨዋታው እንዴት ነበር?

ጨዋታው በመጀመሪያው አጋማሽ በሁለታችንም በኩል ጥሩ አልነበረም። እነሱ,(ወልቂጤዎች) በ3-4-3 ነበር የቀረቡት። እኛ ካለን ነገር አንፃር ቶሎ ቶሎ ከሜዳ እየወጣን ለመጫወት ጥረት አድርገናል። በሚፈለገው ልክ ግን በመጀመሪያው አጋማሽ የጎል ማግባት አጋጣሚዎችን አልፈጠርንም። ሁለት የቆመም ኳስ ተቆጥሮብናል። እሱን ለመቀየር በሁለተኛው አጋማሽ ለውጦችን አድርገናል። ያለን አማራጭ ተቀብለን ለሌላ ቀን መዘጋጀት ነው።

በጨዋታው ስለነበረው አካላዊ ጉሽሚያ…?

የተጫዋች አካላዊ ግጭቶች ሁለት ጊዜ የተፈጠሩት በረጃጅም ኳስ ነበር። እንደየ ጨዋታው ይዘከው የምትመጣው ነገር ይኖራል። እኛ ከሜዳችን ለመውጣት ጥረት ስናደርግ ነበር። በሰው ሜዳም 2 ጊዜ የጭንቅላት ግጭት ተፈጥሯል።

በቀጣዩ የባህር ዳር ቆይታ ማሻሻል ስላለባቸው ነገር…?

የዛሬውን ጨዋታ እንገመግምና የጎደለውን እና ማረም ያለብንን እንደዚሁም ባለፉት ጨዋታዎች ክፍተቶች የነበሩብንን ጎኖች አይተን ወደ ባህር ዳር እንሄዳለን።