ሪፖርት | ብርቱካናማዎቹ ከወራጅ ቀጠናው የሸሹበትን ወሳኝ ድል አሳክተዋል

የመውረድ ስጋት የሚያንዧብብባቸው ድሬዳዋ ከተማ እና ሰበታ ከተማ ያደረጉት ጨዋታ በምስራቁ ክለብ አሸናፊነት ተጠናቋል።

ባሳለፍነው ሳምንት ከወልቂጤ ከተማ ጋር ነጥብ የተጋራው ድሬዳዋ ከተማ በዛሬው ጨዋታ በቅጣት፣ ጉዳት እና እረፍት ምክንያት ግማሽ ደርዘን ተጫዋቾችን ለውጧል። በዚህም በእንየው ካሣሁን፣ ዳንኤል ደምሱ፣ ከድር ሀይረዲን፣ ዳንኤል ኃይሉ፣ ብሩክ ቃልቦሬ እና ሙኸዲን ሙሳ ምትክ ያሲን ጀማል፣ መሐመድ አብዱለጢፍ፣ መጣባቸው ሙሉ፣ አቤል አሰበ፣ ማማዱ ሲዲቤ እና አቤል ከበደ ወደ አሰላለፍ መጥተዋል። በተመሳሳይ ባሳለፍነው ሳምንት አቻ ተለያይተው የዛሬውን ጨዋታ የቀረቡት ሰበታ ከተማዎች በበኩላቸው ከወላይታ ድቻው ጨዋታ ሁለት ለውጦችን አድርገዋል። በለውጦቹም በረከት ሳሙኤል እና ኃይለሚካኤል አደፍርስን ተክተው ቢያድግልኝ ኤሊያስ እና ታፈሰ ሰርካ ወደ ሜዳ ገብተዋል።

ከጨዋታው ሦስት ነጥብ እጅግ አጥብቀው የሚፈልጉት ሁለቱ ቡድኖች ከመጀመሪያው ደቂቃ አንስቶ ለማጥቃት ቅድሚያ የሰጡ በሚመስል መልኩ ቢጫወቱም እስከ ሩብ ሰዓት መዳረሻ ድረስ ዒላማውን የጠበቀ ሙከራ ማድረግ አልቻሉም። በንፅፅር በመጀመሪያዎቹ ደቂቃዎች በተሻለ ወደ ግብ ሲደርሱ የነበሩት ድሬዳዋዎች የጨዋታውን የመጀመሪያ ጎል አግኝተዋል። በዚህም በ14ኛው ደቂቃ አቤል አሰበ ከጋዲሳ መብራቴ የደረሰውን ኳስ ከሳጥን ውጪ በአስገራሚ ሁኔታ ከመረብ ጋር አዋህዶት ቡድኑን ቀዳሚ አድርጓል።

በኳስ ቁጥጥሩ ረገድ የተሻሉት ሰበታ ከተማዎች ከ2 ከደቂቃዎች በኋላ በዱሬሳ ሹቢሳ እና ዴሪክ ንስምባቢ አማካኝነት በሞከሩት ኳስ አቻ ለመሆን ጥረዋል። በተለይ ንስምባቢ በ17ኛው ደቂቃ ከተከላካዮች ጋር ታግሎ የመታው ኳስ ግብ ከመሆን የታደገው የግብ ዘቡ ፍሬው ጌታሁን ቅልጥፍና ነበር። ከዚህ ሙከራ በኋላ እጅግ የተቀዛቀዘው ጨዋታ ቀጣዩን ሙከራ ለማስተናገድ 22 ደቂቃዎችን መታገስ የግድ ብሏል። በዚህም በ39ኛው ደቂቃ ከመዓዘን የተሻገረውን ኳስ ከሳጥኑ ውጪ ሆኖ ሲጠብቅ የነበረው ዱሬሳ አግኝቶ ወደ ግብ መቶል ዒላማውን ስቶበታል። ከደቂቃ በኋላም ንስምባቢ ከሳሙኤል ሳሊሶ የደረሰውን ተከላካይ ሰንጣቂ ኳስ በግብ ጠባቂው አናት በመላክ ለማስቆጠር ቢያስብም ፍሬው ጨርፎበት ሀሳቡ ሳይሰምር ቀርቷል። የሚፈልጉትን በጊዜ ያገኙት ድሬዎች በመከላከሉ ሥራ ላይ ተጠምደው በጭማሪው ደቂቃ ማማዱ ሲዲቤ ከሞከረው ኳስ ውጪ አንድም ጊዜ ምንተስኖትን ሳይፈትኑ አጋማሹን ፈፅመዋል።

በሁለተኛው አጋማሽ ተቀይሮ ወደ ሜዳ የገባው ዳንኤል ኃይሉ ገና በ46ኛው ደቂቃ የቡድኑን መሪነት ወደ ሁለት ለማሳደግ ጥሮ መክኖበታል። ከጨዋታው አንዳች ነገር ለማግኘት የማጥቃት ባህሪ ያላቸው ተጫዋቾችን ለውጠው ወደ ሜዳ የገቡት ሰበታዎች በበኩላቸው ከመጀመሪያው አጋማሽ በተለየ ቀጥተኝነትን በመጨመር መንቀሳቀስ ይዘዋል።

ጨዋታው ገና ግማሽ ሰዓት ሲቀረው ድሬዳዋ ከተማ አጣብቂኝ ውስጥ የገባበት ሁነት ተፈጥሯል። በዚህም ቀድሞ በ24ኛው ደቂቃ ጥፋት አጥፍቶ የመጀመሪያ የማስጠንቀቂያ ካርድ የተመለከተው ያሲን ጀማል ሁለተኛ ቢጫ ካርድ የሚያሰጠው ጥፋት በኃይሉ ግርማ ላይ ሰርቶ ከሜዳ ተሰናብቷል። ከዚህ ደቂቃ በኋላም ድሬዳዋ በጎዶሎ ተጫዋች መጫወት ቢጀምርም 67ኛው ደቂቃ ላይ አውዱ ናፊዮ ከራሱ የግብ ክልል በግንባሩ ለመከላከል አስቦ በገጨው ኳስ ከሰበታ ተከላካዮች ጀርባ የተገኘው ሄኖክ አየለ ጥሩ ዕድል አግኝቶ በሚገርም ሁኔታ ሳይጠቀምባት ቀርቷል።

ከቀይ ካርዱ በኋላ አቻ ለመሆን ሲታትሩ የነበሩት ሰበታ ከተማዎች በርከት ያሉ ተጫዋቾችን ወደ ተጋጣሚ ሳጥን በመላክ ኳሶችን ወደ መስመር በማውጣት በተለይ ከቀኝ መስመር መነሻቸውን ባደረጉ ተሻጋሪ ኳሶች እድሎችን ለመፍጠር ጥረት ቢያደርጉም ንቁ የነበረው ፍሬው ጌታሁን ግን የሚቀመስ አልሆነም። ድሬዳዋ ላይ ጫና መፍጠራቸውን የቀጠሉት ሰበታዎች በተለይም በ83ኛው ጌቱ ኃይለማርያም ከቀኝ መስመር ያሻማውን ኳስ ቢስማርክ አፒያ በግንባሩ ገጭቶ ለጥቂት ከግቡ አናት በላይ የወጣችበት ኳስ አደገኛ አጋጣሚ ነበር።

በዚህ ሂደት ውስጥ ሰበታ ከተማዎች ትተው የሚሄዱትን የሜዳ ክፍል በፈጣን የመልሶ ማጥቃት በተደጋጋሚ መጎብኘት የጀመሩት ድሬዳዋ ከተማዎች በመጨረሻም ጥረታቸው ፍሬ አፍርቷል። በ86ኛው ደቂቃ በጋዲሳ መብራቴ የግል ጥረት ሰበታ ሳጥን የደረሰውን ኳስ አብዱለጢፍ መሀመድ ከግራ የሳጥን ጠርዝ ወደ ውስጥ ያቀበለውን ኳስ ሄኖክ አየለ በግሩም አጨራረስ አስቆጥቶት የጨዋታው የማሳረጊያ ጎል ተገኝቷል።

ውጤቱን ተከትሎ ወሳኝ ድል ያሳኩት ድሬዳዋ ከተማዎች ነጥባቸውን ወደ 24 አሳድገው በነበሩበት 13ኛ ደረጃ ሲቀጥሉ በአንፃሩ ሰበታ ከተማዎች በ13 ነጥቦች አሁንም በሊጉ ግርጌ ተቀምጠዋል።