ሪፖርት | የሄኖክ አየለ የመጨረሻ ደቂቃ ግብ ለድሬዳዋ ነጥብ አስግኝታለች

በሰንጠረዡ ግርጌ ትልቅ ዋጋ በነበረው ጨዋታ ሄኖክ አየለ በጭማሪ ደቂቃ ያስቆጠራት ግብ ድሬዳዋ እና አዲስ አበባ ነጥብ እንዲጋሩ አድርጋለች።

አዲስ አበባዎች ከሀዋሳ ከተማ ጋር አቻ ከተለያየው ስብስብ ሁለት ለውጥ ያደረጉ ሲሆን በዚህም ፍራኦል መንግሥቱ እና አቤል ነጋሽን አስወጥተው በምትካቸው ሮቤል ግርማ እና እንዳለ ከበደን አስገብተዋል።

በአንፃሩ ድሬዳዋ ከተማዎች ደግሞ ሀዲያ ሆሳዕናን ከረታው ስብስብ ሦስት ለውጥ ያደረጉ ሲሆን አቤል አሰበ ፣ ጋዲሳ መብራቴ እና ሱራፌል ጌታቸውን አስወጥተው በምትካቸው ዳንኤል ደምሴ ፣ ዳንኤል ኃይሉ እና ሙኸዲን ሙሳን ተክተው አስገብተዋል።

ለሁለቱም ቡድኖች የጨዋታው ውጤት ከነበረው ዋጋ አንፃር ውጥረት የበዛበት በነበረው ጨዋታ የመጀመሪያ አጋማሽ የጨዋታ ክፍለ ጊዜ ጥንቃቄ የበዛበት አጋማሽ ነበር። በተነፃፃሪነት በአጋማሹ ጥሩ የተንቀሳቀሱት አዲስ አበባ ከተማዎች በሙከራ ረገድ የተሻሉ ነበሩ። 

ገና ከጅምሩ ፍፁም ጥላሁን በግንባሩ ገጭቷት አውዱ ናፊዩ ከግብ መስመር ባዳነበት ኳስ ሙከራ ማድረግ የጀመሩት አዲስ አበባዎች በአጋማሹ በተነፃፃሪነት አደገኛ ሙከራዎችን አድርገዋል። በ22ኛው እና በ47ኛው ደቂቃ ላይ ሙሉቀን አዲሱ እና ሮቤል ግርማ በቀጥታ ከቅጣት ምት ያደረጓቸው እንዲሁም በ24ኛው ደቂቃ ደግሞ ኤልያስ አህመድ ከቀኝ የሳጥን ጠርዝ ሰብሮ በመግባት ያደረጋትን ሙከራ ጨምሮ ሦስቱንም አጋጣሚዎች ፍሬው ጌታሁን በግሩም ንቃት አምክኖባቸዋል።

በ30ኛው ደቂቃ ላይ ባለፈው ጨዋታ ጉዳት አስተናግዶ ከሜዳ ለመውጣት ተገዶ የነበረው ፍፁም ጥላሁን በዛሬውም ጨዋታ ዳግም በመጀመሪያ ተሰላፊነት ቢጀምርም ሜዳ ላይ ከ30 ደቂቃ በላይ ለመቆየት ሳይችል ቀርቶ በቢኒያም ጌታቸው ተቀይሮ ለመውጣት ተገዷል። በአጋማሹ ይበልጥ ጠንቀቅ ብለው ለመከላከል ፍላጎት የነበራቸው ድሬዳዋ ከተማዎች በማጥቃት የሚታይ ሂደትን ለማሳየት የተቸገሩበት ነበር። በዚህም በመጀመሪያው አጋማሽ ምንም ዓይነት የግብ ሙከራ ማድረግ ሳይችሉ ቀርተዋል።


በሁለተኛው አጋማሽ ከጅማሮ አንስቶ በተወሰነ መልኩ በማጥቃት ረገድ ድሬዳዋ ከተማዎች ፍላጎታቸው የማደግ ምልክት ቢያሳይም ዕድሎችን በመፍጠር ረገድ ግን በዚህኛው አጋማሽም አመርቂ አልነበሩም። በአንፃሩ ከጨዋታው መሉ ሦስት ነጥብ ለማግኘት መታተራቸውን የቀጠሉት አዲስ አበባ ከተማዎች በ62ኛው ደቂቃ ላይ ጥረታቸው ፍሬ አፍርቷል። ወደ ቀኝ ካደላ አቋቋም የተሻማውን የቆመ ኳስ ድሬዳዋ ከተማዎች በአግባቡ መከላከል አለመቻላቸውን ተከትሎ ሪችሞንድ አዶንጎ ከእንዳለ ከበደ የደረሰውን ኳስ በግንባሩ በመግጨት አስቆጥሯል።

አዲስ አበባዎች መሪ የሆኑባትን ግብ ካገኙ ወዲህ በተወሰነ መልኩ አሉታዊ ቅያሬዎችን በማድረግ በጥንቃቄ በእጃቸው የገባውን ነጥብ ለማስጠበቅ ጥረት ቢያደርጉም በመልሶ ማጥቃት ግን እጅግ አደገኛ ዕድሎችን መፍጠራቸውን ቀጥለዋል። በተለይም በ73ኛው እና 87ኛው ደቂቃ በመልሶ ማጥቃት በተገኙ አጋጣሚዎች ቢኒያም ጌታቸው ከግብ ጠባቂ ጋር ተገናኝቶ ሳይጠቀምባቸው የቀሩት አጋጣሚዎች አጅግ አስቆጭ ነበሩ።

በአንፃሩ የአቻነቷን ግብ ፍለጋ በተቻላቸው አቅም ጥረት ማድረግ የጀመሩት ድሬዳዋ ከተማዎች የግብ ዕድሎችን ለመፍጠር ተቸግረው ቆይተዋል። በአጋማሹ በ88ኛው ደቂቃ ላይ ከግራ መስመር መሀመድ አብዱለቲፍ ካሻማው የቆመ ኳሶ የተገኘን አጋጣሚ ሱራፌል ጌታቸው በሚያስቆጭ ሁኔታ አምክኗታል። የጨዋታው መደበኛ 90 ደቂቃ ተጠናቆ የተሰጠው አምስት ጭማሪ ደቂቃ ሊጠናቀቅ ሲል ግን ሄኖክ አየለ ከቀኝ መስመር የተሻማን ኳስ በግንባሩ በመግጨት ቡድኑን አቻ አድርጓል።

ውጤቱን ተከትሎ ድሬዳዋ ከተማዎች በ28 ነጥብ ወደ 10ኛ ደረጃ ከፍ ሲሉ በአንፃሩ አዲስ አበባ ከተማዎች ደግሞ በ24 ነጥብ በነበሩበት 14ኛ ደረጃ ቀጥለዋል።