ሪፖርት | ፈረሰኞቹ ወደ ድል ተመልሰዋል

የጋቶች ፓኖም የቅጣት ምት ጎል ቅዱስ ጊዮርጊስ ጅማ አባ ጅፋርን 1-0 እንዲያሸንፍ አድርጋለች።

ጅማ አባ ጅፋር ከሰበታ ከተማው ሽንፈት መልስ አራት ለውጦችን ሲያደርግ ሽመልስ ተገኝ ፣ ዳዊት እስጢፋኖስ ፣ አድናን ረሻድ እና ሙሴ ካበላ በየአብስራ ሙሉጌታ አስጨናቂ ፀጋዬ ፣ ቦና ዓሊ እና ዱላ ሙላቱ ተተክተዋል። ቅዱስ ጊዮርጊስ ደግሞ ከወላይታ ድቻው ጨዋታ ደስታ ደሙን በሱለይማን ሀሚድ እንዲሁም ከነዓን ማርክነህን በሀይደር ሸረፋ በመተካት ጨዋታውን ጀምሯል።

በሁለቱም ቡድኖች በኩል ፈጠን ያለ አጀማመርን ያስተናገደው ጨዋታ ጥሩ ፉክክርን በማሳየት ጀምሯል። አንድ ደቂቃ ሳይሞላ ከግብ ጠባቂው በረጅሙ በተላከ እና አማኑኤል ገብረሚካኤል በግንባሩ ሞክሮ ወደ ላይ በወጣበት ኳስ ወደ ግብ መድረስ የጀመሩት ጊዮርጊሶች የሻታለ ጫና ፈጥረው ነበር። ከሄኖክ አዱኛ ከመስመር በሚነሱ እንዲሁም ከኋላ በሚላኩ ረዘም ያሉ ኳሶች ጊዮርጊሶች ወደ ሳጥን ደርሰው ቢታይም አማኑኤል ፣ ቸርነት እና ቡልቻን መዳረሻቸው ያደረጉት አጋጣሚዎች ወደ መጨረሻ የግብ ዕድልነት ሳይቀየሩ ቆይተዋል።

ይልቁኑም በጥልቀት መከላከልን ያልመረጡት ጅማዎች ቀስ በቀስ ፈጠን ባለ ጥቃት ከሜዳቸው መውጣት ሲጀምሩ ቀዳሚውን ከባድ ሙከራ ከቆመ ኳስ አድርገዋል። በዚህም 19ኛው ደቂቃ ላይ መሐመድኑር ናስር የሱራፌል ዐወልን የቀኝ መስመር ቅጣት ምት በግንባሩ በመግጨት ያደረገው ሙከራ በግቡ ቋሚ ተመልሷል። በቀጣዮቹ ደቂቃዎች የጨዋታው የማጥቃት ምልልስ ጋብ ብሎ ሲቀጥል የጅማ ወደ ፊት የመሄድ ጥረት እየጎላ መጥቷል። ከዚህ ውስጥ 32ኛው ደቂቃ ላይ ጅማዎች ወደ ሳጥን ቀርበው ባደረጉት ቅብብል ሱራፌል ዐወል ከመሐመድ ኑር የደረሰውን ኳስ ፍሪምፖንግ ሜንሱን በማለፍ ከግማሽ ጨረቃው ላይ ያደረገው ሙከራ በቻልርለስ ሉኩዋጎ ተይዞበታል።

በጉዳት ምክንያት ቡልቻ ሹራን በዳግማዊ አረዓያ ለመቀየር የተገደዱት ቅዱስ ጊዮርጊሶች በጀመሩበት መንገድ ጅማን ጫና ውስጥ መክተት ባይችሉም በቀጥተኛ ኳሶች አልፎ አልፎ ወደ ግብ ሲደርሱ ከማዕዘን ምት በተሻገረ ኳስ ምኞት ደበበ ያደረገው ደካማ ሙከራ ብቻ በበድኑ በኩል የተሻለ ነበር። የአጋማሹ የመጨረሻ ደቂቃዎች በዚህ መልኩ በንፅፅር በተሻለ ሁኔታ ጅማዎች በጊዮርጊስ ሜዳ ላይ በመቆየት እና ከተጋጣሚያቸው ጀርባ ያለውን ቦታ ለመጠቀም በመሞከር አጠናቀዋል።

ከዕረፍት መልስ እንደመጀመሪያው ሁሉ ጊዮርጊሶች በተሻለ ጫና ጀምረዋል። ጅማዎች አልፎ አልፎ የመልሶ ማጥቃት ዕድሎችን ቢያገኙም የተሳካ ሽግግር ማድረግ ሳይችሉ ቆይተው ጊዮርጊሶች መሪ የሚሆኑበትን እና የጨዋታውን መንፈስ የቀየረ አጋጣሚ ፈጥረዋል። ከጊዮርጊስ የግብ ክልል የተላከ ረጅም ኳስ ከጅማ ተከላካዮች ጀርባ ሲደርስ ከቸርነት ጉግሳ ቀድሞ ኳሱን ለማዳን ጥረት ያደረገው የጅማው ግብ ጠባቂ አላዛር ማርቆስ ከሳጥን ውጪ በእጅ በመንካቱ በቀጥታ ቀይ ካርድ ከሜዳ ወጥቷል። ይህንን ተከትሎ የተሰጠውን የቅጣት ምትም 56ኛው ደቂቃ ላይ ጋቶች ፓኖም በቀጥታ በመምታት ጊዮርጊስን ቀዳሚ አድርጓል።

ከግቡ በኋላ ጊዮርጊሶች በቁጥር በሚበልጡት ተጋጣሚያቸው የመከላከል ወረዳ ላይ የተሻሉ ክፍተቶችን አግኝተው በተደጋጋሚ ጥቃቶችን ቢሰነዝሩም የመጨረሻ የግብ ዕድል አልፈጠሩም። ወደ ፊት ለመሄድ ቸግሯቸው በቆዩት ጅማዎች በኩል ግን 67ኛው ደቂቃ ላይ ከየአብስራ ተስፋዬ በተቀማ ኳስ በግራ መስመር መሐመድኑር ናስር ከግራ ያስጀመረውን ፈጣን ጥቃት ከእዮብ ዓለማየሁ እና ዱላ ሙላቱ ጋር በመቀባበል ሳጥን ውስጥ ደርሶ ያደረገው አደገኛ መከራ በቻርለስ ሉኩዋጎ ተመልሷል።

በመጨረሻዎቹ 10 ደቂቃዎች የጅማ የማጥቃት ጥረት እየቀዘቀዘ ሲሄድ የእዮብ ዓለማየሁ የርቀት ሙከራ ብቻ በቡድኑ በኩል ታይቷል። 84ኛው ደቂቃ ላይ አማኑኤል የሄኖክ አዱኛን የግራ መስመር የአየር ላይ ኳስ በአግባቡ ሳይገጭ በቀረበት ሙከራ መሪነታቸው ሳያጠናከሩ የቀሩት ጊዮርጊሶች ጨዋታው ላይ የውጤት ለውጥ ሳይኖርበት ለመጨረስ ግን አልተቸገሩም። በመሆኑም እንቅስቃሴውን አብርደው 1-0 እንዲያልቅ አድርገዋል።

ውጤቱን ተከትሎ ቅዱስ ጊዮርጊስ ነጥቡን 54 በማድረስ መሪነቱን ሲያጠናክር ጅማ አባ ጅፋር በወራጅ ቀጠናው 19 ነጥብ ላይ ቀርቷል።