የአሰልጣኞች አስተያየት | ጅማ አባ ጅፋር 0-1 ቅዱስ ጊዮርጊስ

ቅዱስ ጊዮርጊስ ጅማ አባ ጅፋርን መርታት ከቻለበት ጨዋታ በኋላ አሰልጣኞች ሀሳባቸውን አካፍለዋል።

አሰልጣኝ ዘሪሁን ሸንገታ – ቅዱስ ጊዮርጊስ

ስለ ጨዋታው

“ጥሩ ጨዋታ ነው፡፡ መጀመሪያ ስንገባም ተናግሪያለሁ ከባድ ጨዋታ እንደሚገጥመን። ኳስ ተጫውቶ ለማጥቃት አውት ኦፍ ፖዝሽን ውስጥ በሆንክበት ሰዓት እነርሱ ለማጥቃት ወደ ማጥቂያ ቦታ ይመጣሉ፡፡ እኛ ግን ያንን ዲፌንሲቭ የሆነውን ድክመት አስተካክለን ተረጋግተን ማድረግ እንችል ነበር፡፡ በፈለግንበት ሰዓት ላይ ጎሉን አግኝተናል፡፡

ቀይ ካርዱን ስለመጠቀማቸው

“ኮምፕሊትሊ በቀይ አንድ ተጫዋች ያጣንበትን ፖዚሽን በደንብ አላገኘነውም፡ ፤ ውጥረት ነው፡፡ ማሸነፍ አለብን ፤ ከአቻ ውጤት የመጣን ስለሆነ ከባድ ጨዋታ ስለነበር፡፡ ለማሸነፍ የነበራቸው ጉጉት እና ለማሸነፍ የሄዱበት መንገድ በጣም ፐርፌክት ነው፡፡

ስለ ቡልቻ ሹራ እና ሌሎች አጥቂዎች ጉዳት

“ትልቅ ተፅዕኖ አለው፡፡ አጥቂዎቻችን ሜዳ ላይ የሚሰጡትን ግብዓት በጊዜ እና በአግባቡ አላገኘነውም ፤ በጉዳት እየወጡብን ስለሆነ፡፡ ግን እንደ ቡድን እየተጫወትን የተሻለ ነገር ሰርተን አሁንም የጀመርነውን መንገድ እንቀጥላለን ብዬ አስባለሁ፡፡

ስለ ቀጣዩ የፋሲል ጨዋታ

“የዛሬው ጨዋታ የራሱ ገፅታ አለው ፤ ትልቅ ጨዋታ ነበር፡፡ ጥሩ ነገር ሰርተን አሸንፈን ወጥተናል፡፡ የነገው ደግሞ የተለየ ወይንም የሚከተለንን ሁለተኛ ላይ ያለውን ነው የምንገጥመው፡፡ ለዛ ደግሞ በደንብ ተዘጋጅተን እንመጣለን፡፡

አሰልጣኝ የሱፍ ዓሊ – ጅማ አባ ጅፋር

ስለ ዘጠና ደቂቃው

“ዘጠና ደቂቃውን በምንፈልገው መንገድ እየተጫወትን ነበር፡፡ ልጆች ጥሩ ናቸው ፤ ታክቲካል ዲሲፕሊናቸውም ሁሉ ነገር አሪፍ ነበር፡፡ በራሳችን ባመጣነው ስህተት ከጨዋታው ውጪ ወጥተናል፡፡ ከጨዋታው ስለወጣን የግድ መቀየር ስላለብን ተጫዋቾችን ስንቀየር አጨዋወቱ ተቀየረ፡፡

ስላቀጥተኛ አጨዋወታቸው

“መጀመሪያ ኳስ ሳይቆጠር በፊት አጥቂ ላይ ነበር የቀየርነው፡፡ ውጤቱ ከተቀየረ በኋላ ግን አጥቂ ማስገባት ስላለብን ተከላካይ ቀንሰናል፡፡

ስለ አላዛር ማርቆስ

“ከአላዛር የመጣው ስህተት ነው፡፡ ባላንሱን አልጠበቀም ነበር፡፡ በዚህ በመጣው ስህተት ነው ውጤትም ያጣነው፡፡

ስለ ተከታታይ ሽንፈት

“መነሳሳቱ ጥሩ ነው፡፡ መጀመሪያ ላይ እንደገለፅኩት የምትፈልገውን ለማጫወት የምትፈልጋቸውን ልጆች ማግኘት አለብህ፡፡ በመሀል በየአራት ፣ አራት ቀኑ ተጫዋቾች ይወጡብሀል፡፡ እንደሱ እየሰራን ነው ለዚህ የደረስነው፡፡

ስለወራጅነት ስጋት

“ላለመውረድ ያለንን እየጠበቅን ከዚህ በኋላ ያሉትን ጨዋታዎች በጥሩ ሁኔታ ውጤት እያመጣን የሚቀጥለውን ነገር ማየት ነው፡፡