ሪፖርት | መከላከያ እና ድሬዳዋ ነጥብ ተጋርተዋል

ሊጉ በመከላከያ እና ድሬዳዋ ያለግብ በተጠናቀቀ ጨዋታ ለብሔራዊ ቡድን ጨዋታዎች ወደ ዕረፍት አምርቷል።

መከላከያ የፋሲል ከነማውን ሽንፈት ጨምሮ ሰሞኑን ሲጠቀምበት የነበረውን አሰላለፍ ሳይቀይር ጨዋታውን ጀምሯል። በድሬዳዋ በኩል ደግሞ አቤል አሰበ ፣ ሱራፌል ጌታቸው እና ጋዲሳ መብራቴ በአዲስ አበባው ጨዋታ በጀመሩት ዳንኤል ደምሴ ፣ ዳንኤል ኃይሉ እና ሙኸዲን ሙሳ ምትክ ወደ ሜዳ ገብተዋል።

የመጀመሪያው አጋማሽ መከላከያዎች በሙከራ የተሻለበት እና ድሬዳዋ በመከላከል ላይ ያሳለፈበት ነበር። በጨዋታው ቀዳሚ ሙከራ 3ኛው ደቂቃ ላይ ክሌመንት ቦዬ ከግብ ክልሉ የጠለዘውን እስራኤል እሸቱ ሁለተኛ ኳስ በማሸነፍ ያሳለፈለትን ተሾመ በላቸው ቀኝ አቅጣጫ ወደ ሩቁ ቋሚ ሞክሮ በግቡ ቋሚ ተመልሶበታል። በተሻለ ጫና የቀጠሉት መከላከያዎች ከዚሁ የቀኝ መስመር ደጋግመው አደጋ ለመፍጠር ጥረዋል። ከተሾመ በላቸው ሙከራ ሁለት ደቂቃ በኋላ ግሩም ሀጎስ በዚሁ መስመር ገብቶ ወደ ውስጥ የላከውን ጨምሮ ምንተስኖት አዳነ በ16ኛ እና 17ኛ ደቂቃ ላይ ከቀኝ መስመር ጥሩ የሚባሉ የግብ ዕድሎችን ፈጥረው ነበር። ሆኖም በተለይም የ16ኛ ደቂቃውን ኳስ ተሾመ ሳይደርስበት በግሩም ሸርተቴ አውጥቶበታል።

12ኛው ደቂቃ ላይ መሀመድ አብዱልጢፍ ከግራ መስመር ያሻገረውን በቀኝ ወደ ግብ የደረሰው ጋዲሳ መንራቴ በግንባሩ ሞክሮ ቦዬ ሲይዝበት የተሻለ የማጥቃት ሂደትን ያሳዩት ድሬዳዋዎች በአመዛኙ ከግብ ክልላቸው በቅብብል ለመውጣት ያደረጉት ጥረት ስኬታማ አልነበረም። ቡድኑ ከውሃ ዕረፍቱ በኋላ በኳስ ቁጥጥሩ የተሻለ ሆኖ መታየት የጀመረ ቢሆንም ቀጣዩ ከባድ ሙከራም የታየው በጦሩ በኩል ነበር። በዚህም 26ኛው ደቂቃ ላይ ተሾመ በቀኝ ሳጥን ጠርዝ ላይ ተከላካዮችን አታሎ ያዘጋጀውን አዲሱ አቱላ አክርሮ ሞክሮ ለጥቂት ወደ ውጪ ወጥቶበታል።

የድሬዎች የኳስ ቁጥጥር 33ኛው ደቂቃ ላይ ብሩክ ቃልቦሬ ከርቀት ካደረገው ቀላል ያለ ሙከራ ሌላ ተጨማሪ የግብ ዕድል ያላስገኘላቸው ሲሆን በተለይም የቀኝ መስመር ጥቃታቸው የተቀዛቀዘው መከላከያዎችም 38ኛው ደቂቃ ላይ ከማዕዘን ምት በተነሳ የተጨራረፈ ኳስ ግብ ለማስቆጠር ያደረጉት ጥረት የተሻለው አደገኛ አጋጣሚ ነበር።

ሁለተኛው አጋማሽ በድሬዎች ከባድ ጥቃት የጀመረ ነበር። 47ኛው ደቂቃ ላይ አብዱርሀማን ሙባረክ ከተከላካይ ጀርባ የጣለለትን ኳስ ሄኖክ አየለ ወደ ግብ ሞክሮ ክሌመንት ቦዬ እንደምንም ሲያድንበት እንየው ካሳሁን ደርሶ በድጋሚ ለማስቆጠር ያደረገውን ጥረት አሌክስ ተሰማ ቀድሞ በመድረስ አውጥቶበታል። አብዱርሀማን ከአንድ ደቂቃ በኋላም በቀኝ በኩል ተጫዋቾች አልፎ የገባበት አጋጣሚም በጦሩ ተከላካዮች ርብርብ ነበር የወጣው። ከዚህ በኋላ ግን መከላከያዎች ጨዋታውን ወደ ራሳቻው በማምጣት በጥሩ ጫና ተጫውተዋል። ሆኖም በግራ ቢኒያም በላይን በጥሩ ሁኔታ የተቆጣጠሩት ድሬዎች አልፎ አልፎ በቀኝ አደጋ የሚጥሉ እንቅስቃሴዎች ቢገጥሟቸውም በአመዛኙ ጦሩን ተቆጣጥረዋል። ይልቁኑም 59ኛው ደቂቃ ላይ አብዱርሀማን ሙባረክ ከተሰለፈበት የቀኝ መስመር ከርቀት ያደረገው ሙከራ ለግብ የቀረበ ነበር።

የጨዋታው ቀሪ 30 ደቂቃዎች በቡድኖቹ ያልተሳኩ የማጥቃት እንቅስቃሴዎች ታጅቦ የቀጠለ ሲሆን በሁለቱ ግቦች ፊት የተከላካዮች ጥቃቶችን የማቋረጥ ሂደት እስከፍፃሜው ቀጥሏል። መከላከያ በፅፅር የተሻለ የማጥቃት የበላይነት ኖሮት ቢታይም ጥረቱ ኢላማቸውን ካልጠበቁ ሙከራዎች አላለፈም። እየተቀዛቀዘ የመጣው ጨዋታም ያለ ግብ እንዲጠናቀቅ የግድ ሆኗል።

ውጤቱን ተከትሎ መከላከያ በ31 ነጥቦች ወደ 8ኛ ደረጃ ከፍ ሲል ድሬዳዋ ከተማ በ 29 ነጥቦች 13ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል።