የዋልያውን የማላዊ ቆይታ የተመለከቱ አስተዳደራዊ ጉዳዮች ገለፃ ተደርጎባቸዋል

👉”…የመስከረሙ ጨዋታ ከመድረሱ በፊት በተቻለ መጠን የአዲስ አበባ ስታዲየምን ለውድድር ለማድረስ እንደሚሰራ ተነግሮናል” ባህሩ ጥላሁን

👉”የባህር ዳር ስታዲየም ጥቃቅን ስራ ብቻ አይደለም የሚቀረው። በጣም ብዙ ነገር ነው የሚቀረው” ባህሩ ጥላሁን

👉”…አዲስ አበባ ስታዲየምን ተመልክቶ ‘ለውድድር አይደለም ለልምምድ አልፈቅድላችሁም’ ነው ያለው” ባህሩ ጥላሁን

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን የአፍሪካ ዋንጫ የምድብ የመጀመሪያ ሁለት ጨዋታዎችን አስመልክቶ በአሠልጣኙ ውበቱ አባተ አማካኝነት የተሰጠውን መግለጫ ቀድመን አቅርበን የነበረ ሲሆን አሁን ደግሞ አስተዳደራዊ ጉዳዮችን በተመለከተ የፌዴሬሽኑ የጽሕፈት ቤት ሀላፊ አቶ ባህሩ ጥላሁን የተናገሩትን ሀሳብ ይዘን ቀርበናል። በቅድሚያም ሀላፊው ተከታዩን ሀሳብ በስፍራው ለተገኙ የብዙሃን መገናኛ አባላት ካጋሩ በኋላ ለቀረበላቸው ጥያቄዎች ምላሽ ሰጥተዋል።

“በመጀመሪያ ደረጃ ግብፅ ላይ ባስመዘገብነው ውጤት መላው የኢትዮጵያ ህዝብን እንኳን ደስ አላችሁ ማለት እወዳለው። እንደዚሁም ደግሞ ደረጃውን የጠበቀ ስታዲየም ባለመኖሩ ምክንያት ወደ ማላዊ ተጉዘን ጨዋታውን ስናደርግ ጥያቄያችንን ለተቀበለው የማላዊ እግር ኳስ ፌዴሬሽን እና የማላዊ ህዝብ ለነበራቸው ድጋፍ እንደ ኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ምስጋናችንን ማቅረብ እንፈልጋለን።” ካሉ በኋላ ከወጪ ጋር የተያያዙ ማብራሪያዎችን መዘርዘር ይዘዋል።

“ጨዋታዎቹን ከሜዳችን ውጪ እንደመጫወታችን መጠን አስተዳደራዊ የሆኑ ወጩዎቻችን ላይ ከፍተኛ የሆነ ጫና ነበር። እነዚህን አስተዳደራዊ ወጪዎች በተለያዩ መንገዶች ለመሸፈን ሞክረናል። ከእነዚህ መካከል ከአንድ የእንግሊዝ ተቋም ጋር በመሆን የሜዳ ዳር ማስታወቂያዎችን ለማምጣት ተነጋግረናል። በዚህም በአንዱ 2500 ዶላር በመደራደር 22 ቦርዶችን ተጠቅመን 55 ሺ ዶላር አካባቢ አግኝተናል። ከዚህ ውጪ እንደ ፌዴሬሽን ከማላዊ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ጋር ስንነጋገር ያስቀመጡልን የገንዘብ መጠን ነበር። እውነት ለመናገር ያስቀመጡት ነገር ከፍተኛ የሆነ የውጪ ምንዛሬን የሚጠይቅ ነበር። በወቅቱ ከየትኛውም ባንክ ለሚያስፈልጉ ወጪዎች ምንም አይነት ገንዘብ ከዚህ ይዘን አልተጓዝንም። በአንፃሩ ለማላዊ እግር ኳስ ፌዴሬሽን 2 ምክረ ሀሳቦችን ነበር ያቀረብነው። አንደኛው ከስታዲየም ከሚገኘው ገቢ ድርድር በማድረግ የሚወጡ ወጪዎችን መሸፈን ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ ገንዘብ ከዚህ የምንልክበትን መንገድ እንዲያመቻቹ ነበር።

“በእነዚህ ጉዳዮች እስከ መጨረሻው ድረስ መግባባት ላይ አልደረስንም ነበር። ግን ከፍተኛ የሆነ ሪስክ ወስደን የመጀመሪያውን አማራጭ ተጠቅመናል። ይህንን የመረጥነው ደግሞ ቀደም ብለን የላክናቸው ባለሙያዎች እዛ ጥናት አድርገው ስለነበር ነው። የሆነው ሆኖ ፌዴሬሽናችን በውድድሩ 54 ሺ ዶላር አካባቢ ገቢ ማግኘት ችሏል። ይሄ ብር ከትኬት ሽያጭ የተገኘ ነው። ከዚህ ላይ ለስታዲየም፣ ለማላዊ እግር ኳስ ፌዴሬሽን እና ለትኬት ምርት ተቀናሽ ተደርጓል። ለስታዲየሙ በአጠቃላይ 36,885 ዶላር ነው ተያያዥ ወጪዎችን ጨምሮ የተከፈለው። በአጠቃላይ ከግብፅ ጨዋታ ጋር በተገናኘ አስፈላጊ የሚባሉ ወጪዎችን ያገኘነው ገቢ ሸፍኖልናል። ከወጪ ገቢ 10,680 ዶላር ከማላዊ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ጋር ለሁለት ተካፍለናል። በአጠቃላይ 54 ሺ አካባቢ ከማስታወቂያዎቹ አግኝተናል ከስታዲየም ገቢ የተካፈልነውም 10 ሺ የተገኙ ገቢዎች ናቸው። ጨዋታዎቹ እዚህ ሀገራችን ቢሆኑ ኖሮ ደግሞ ሊገኝ የሚችለውን ነገር ማሰብ ቀላል ነው።”

ቀጣይ የሜዳ ጨዋታዎች ጉዳይ….?

“እንደ ኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ቡድናችን በሜዳው መጠቀም እንዳለበት እናስባለን። አሁን ባሉ መረጃዎች ፕሬዝዳንታችን ከባህል እና ስፖርት ሚንስቴሩ ጋር ተነጋግረው ነበር። እነርሱ ባስቀመጡት ዕቅድ መሰረት የመስከረሙ ጨዋታ ከመድረሱ በፊት በተቻለ መጠን የአዲስ አበባ ስታዲየምን ለውድድር ለማድረስ እንደሚሰራ ተነግሮናል። ይሄንን ማድረግ ከተቻለ ጥሩ ነገር ነው። ቅድም ስለ ገቢዎች ተናግረናል። ግን አሁንም መርሳት የሌለብን ነገር ካገኘነው ያጣነው ይበዛል። ይሄ ጨዋታ ኢትዮጵያ ውስጥ ቢሆን ኖሮ የሚፈጠረውን ማሰብ ነው። እኛ ሊፈጠር የሚችለውን ችግር ነው ለመቀነስ የሞከርነው። ይሄ ጨዋታ ባህር ዳር ላይ ተደርጎ ቢሆን ኖሮ አስቡት። በዚህ ከፍተኛ ገንዘብ መስራት ይቻል ነበር። ለምሳሌ እንኳን ለአንድ ዳኛ ለፕሌን ትኬት ብቻ እስከ 140 ሺ ብር አውጥተናል። ከብሩንዲ አዲስ አበባ ቢመጡ ኖሮ ይቀንስ ነበር። ለኮሚሽነሩም ከትራንስፖርታቸው ውጪ እስከ 4 ሺ ዶላር ሸፍነናል። ይሄ ትልቅ ዋጋ ነው የሚያስከፍለው። ለዚህ ነው ካገኘነው ያጣነው ይበዛል ያልኩት።

“ስለቀጣይ ለማውራት ከባድ ነው ግን ማላዊ ያለው ነገር በጣም ጥሩ ነው። ግን ይሄንን የሚወስነው የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን የሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ ነው። ስለዚህ አንዱ ሀገር ላይ ውሳኔው ይተላለፋል። እኛ ግን አሁንም ይሄኛው የሚያልቅልን ከሆነ ስቃያችን ይቀንሳል ብለን ነው የምናስበው። ያለበለዚያ ግን ከፍተኛ ችግር ውስጥ ነው እየገባን የምንሄደው።

“ከማላዊ ስንመለስ ማላዊያን ስታዲየማችሁ ካላለቀ እኛ ጋር ተጫወቱ እያሉን ነበር። ቢዝነስ መስራቱ እንዳለ ሆኖ ለኢትዮጵያም ሆነ ለኢትዮጵያዊያን ጥሩ ነገር አላቸው። ግን ወደ እግርኳሱ ስንመጣ ጊኒን እዛ ብንጫወት ማላዊን እዛ ልንገጥም አንችልም። ምንም አይነት እግር ኳሷዊ ምክንያት ልናስቀምጥ አንችልም። ስታዲየሞቻችን እስከዛ ካልደረሱ ሌላ ቦታን ነው የምንፈልገው።”

‘ድጋፍ ካላገኘን ከውድድር እንወጣለን’ ስለተባለው ጉዳይ…?

“አሁን ላይ በተለያዩ አማራጮች ማርኬቲንጋችንን አስፍተን ገንዘብ መስራት ችለናል። መንግስትም ደግሞ አሁን የተመዘገበውን ድል በመመልከት የሆነ ነገር ያደርግልናል ብለን እንጠብቃለን። ምክንያቱም አስቀድመን ጥያቄያችንን ስላቀረብን። ይሄ ነገር ይሆናል የሚል እምነት አለን። ዳሜጁን ቀንሰዋል ግን አሁንም በዚሁ መልኩ የሚቀጥል ከሆነ ፌዴሬሽኑ አቅሙ እየተሟጠጠ ነው የሚመጣው። በነገራችን ላይ ኢትዮጵያ ከግብፅ እና ከጊኒ ስትጫወት የሚኖረው የማስታወቂያ መጠን ሊለያይ ይችላል። አሁን ከግብፅ ስለሆነ 22 የሜዳ ዳር ማስታወቂያ አግኝተናል። ከጊኒ ሲሆንስ የሚለውን ካየን የተወሰነ ልናገኝ አልያም ላናገኝ የምንችልበት ሁኔታ ሊፈጠር ይችላል። ስለዚህ የተረጋጋ የፋይናንስ ጉዞ ላይ ነን ብሎ መናገር ትንሽ ይከብዳል።

“ከስታዲየም ጋር ተያይዞ እኛ ከባህል እና ስፖርት ሚኒስቴር ጋር ነው እየተነጋገርን ያለነው። በተጨማሪም በአንድ መድረክ ከጠቅላይ ሚኒስቴር ማኅበራዊ ዘርፍ አንድ ተወካይ መጥተው ጥያቄያችንን አቅርበናል። ገና ድልድሉ ሳይታወቅ እንደ ኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን አቋማችንን አሳውቀን ነበር። እንግዲህ ለሚመለከተው አካል ጥያቄው ቀርቧል ወይስ አልቀረበም የሚለውን ማጣራት ያስፈልጋል። ባህር እና ስፖርት ሚኒስቴር ጉዳዩን በደንብ ያውቀዋል። እንዳልኩት የጠቅላይ ሚኒስቴር ቢሮም እንደዛው ግን ጥያቄው ለሚመለከተው አካል ቀርቧል የሚለው መታየት አለበት። እኛ አሁንም መግፋታችንን እንቀጥላለን።

“እኛ ስለ አዲስ አበባ ስታዲየም ብቻ አይደለም የምናወራው። የባህር ዳር ስታዲየምን ተጠቅሞ ተጠቅሞ ትቷል የሚል ሀሳብ አለ። ይህ ትክክል አይደለም። የባህል እና ስፖርት ሚኒስቴር በባለቤትነት ከሚያስተዳድራቸው ስታዲየሞች መካከል የአዲስ አበባ ስታዲየም ይገኛል። እነርሱም የማሻሻያ ስራዎችን እየሰሩ ነው። ቶሎ ለማድረስም ሙከራ ላይ ናቸው። እኛም የተመለከትናቸው ነገሮች አሉ። የእኛ ፍላጎት የትኛውም ስታዲየም ቶሎ እንዲደርስልን ነው። ብቻ ሀሳባችን በሀገራችን ጨዋታችንን እናድርግ የሚል ነው።

“የባህር ዳር ስታዲየም ጥቃቅን ስራ ብቻ አይደለም የሚቀረው። ይሄንን ሁሉም ሰው ሊያውቀው ይገባል። በጣም ብዙ ነገር ነው የሚቀረው። ስታዲየሙ ትልቅ ነው ግን የጎደሉት ነገሮች ጥቃቅን ናቸው ብለን የምንተዋቸው ናቸው ብለን መመርመር አለብን። ቢያንስ አንድ ቦታ ላይ የስትራልቸር ችግር እንዳለበት (የሚዲያ እና የቪ አይ ፒ) ተነስቷል። ይሄንን ለማስተካከል ምን ያህል ወጪ ይጠይቃል። ሌሎችን የተዘረዘሩትን ነገሮችንም መመልከት ያስፈልጋል። አሁን እኩል ትኩረት ተሰጥቶ ስታዲየም እንዲደርስልን እንፈልጋለን። ግን በአጭር ጊዜ ውስጥ የሚደርስ ስታዲየም ካለ እሰይ የሚያሰኝ ስለሆነ እዛ ላይ ትኩረት ይደረግልን ነው እያልን ያለነው።”

የሚገነቡት ስታዲየሞች በካፍ ይገመገማሉ ወይ…?

“የአደይ አበባ ስታዲየም ለመጀመሪያ ጊዜ የታየው እኔ ወደ ፌዴሬሽኑ ስመጣ አህመድ ሀራስ በሚባል የክለብ ላይሰንሲንግ ባለሙያ ነው። ባለሙያው ሁሉንም ስታዲየሞች ተመልክቷል። እንደውም አዲስ አበባ ስታዲየምን ተመልክቶ የተናገረው ‘ለውድድር አይደለም ለልምምድ አልፈቅድላችሁም’ ነው ያለው። የመጫወቻ መጫወታውን አይቶ ነው ይሄንን አስተያየት የሰጠው። የአደይ አበባ ስታዲየም ስታንዳርዱን የሚያሟላ ስራ እየተሰራ እንደሆነ ተናግሮ ነው የሄደው።”

ለአሠልጣኙ ኮንትራት ጋር በተያያዘ ንግግር ስለመጀመሩ…?

“እውነት ለመናገር አልተጀመሩም። እስካሁን ድረስ ጊዜ እንዳለ ነው እያሰብን ያለነው። ስለኮንትራት አሁን ስታነሱ ነው ደንገጥ እያልኩ ያለሁት እንጂ ስለኮንትራት ንግግር በይፋ የጀመርናቸው ነገሮች እንደሌሉ ለመግለፅ እወዳለው።”