ሪፖርት | ወልቂጤ ከተማ እና ሲዳማ ቡና ነጥብ ተጋርተዋል

በዕለቱ ሁለተኛ ጨዋታ ወልቂጤ ከተማ እና ሲዳማ ቡና አንድ አቻ ተለያይተዋል።

ባሳለፍነው ሳምንት በሊጉ መሪ ቅዱስ ጊዮርጊስ ሁለት ለምንም የተረቱት ወልቂጤዎች ሦስት ነጥብ ካስረከቡበት ጨዋታ የግብ ዘቡ ሮበርት ኦዶንካራን በሰዒድ ሀብታሙ፣ ረመዳን የሱፍን በዮናስ በርታ፣ በሀይሉ ተሻገርን በኢሞሞ ንጎይ እንዲሁም ቤዛ ገብረመድህን በሙሉጌታ ወልደጊዮርጊስ ለውጠው ወደ ሜዳ ሲገቡ ጅማ አባ ጅፋርን ሁለት ለአንድ አሸንፈው ለዛሬው ጨዋታ የተዘጋጁት ሲዳማ ቡናዎች በበኩላቸው በቅጣት ምክንያት የማይገኘው መኳንንት ካሣን ብቻ በጊት ጋትኩት ተክተዋል።

ጨዋታውን በጥሩ ተነሳሽነት የጀመሩት ሲዳማ ቡናዎች ገና በጊዜ መሪ ለመሆን ሲንቀሳቀሱ ነበር። በተለይ በ4ኛው ደቂቃ ከይገዙ ቦጋለ ጋር የተገናኘው የግብ ዘቡ ሮበርት ኦዶንካራ መሬት ለመሬት የመጣውን ኳስ መቆጣጠር ተስኖት ሳላዲን ሰዒድ አግኝቶት ለዳዊት ተፈራ ቢሰጠውም የአጥቂ አማካዩ ሳይጠቀምበት የቀረው እጅግ ለግብ የቀረበ ነበር። ከአምስት ደቂቃዎች በኋላ ደግሞ ወልቂጤዎች ለተሰነዘረባቸው ጥቃት ፈጣን ምላሽ በመስጠት ጥሩ ኳስ ወደ ግብ ልከዋል። በዚህም አቡበከር ሳኒ በቀኝ የሳጥኑ ክፍል ተገኝቶ የመታውን ኳስ ግብ ጠባቂው መክብብ ደገፉ በግራ እግሩ ከግብነት ታድጎታል።

በብዙ መስፈርቶች የተሻሉ የነበሩት ሲዳማዎች በጨዋታው ሩብ ደቂቃ ከቆመ ኳስ ሌላ ሙከራ አድርገው ነበር። ባሳለፍነው ሳምንት ጅማ ላይ ድንቅ የቅጣት ምት ጎል ያስቆጠረው ሳላዲን ከተመሳሳይ ቦታ የተገኘውን አጋጣሚ መሬት ለመሬት ቢልከውም ሮበርት በጥሩ ቅልጥፍና ይዞበታል። ሮበርት ከሁለት ደቂቃዎች በኋላ የተሞከረውን የሳላዲን ኳስ ግን መመለስ ሳይችል ቀርቷል። በተጠቀሰው ደቂቃም አማኑኤል እንዳለ ከቀኝ መስመር ያሻገረውን ኳስ አንጋፋው አጥቂ ሳላዲን ወደ ግብነት ቀይሮት ሲዳማ መሪ ሆኗል።

የአሠልጣኝ ተመስገን ተጫዋቾች ወደ ጨዋታው ለመመለስ ጥረት ማድረግ ይዘዋል። በ34 እና 35ኛው ደቂቃ የተሞከሩት ኳሶችም ውጥናቸውን የሚያሰምር ቢሆንም ግብ ጠባቂው መክብብ አድኖባቸዋል። በተለይ ቀድሞ የተደረገው የአብዱልከሪም ወርቁ የርቀት ጥብቅ ኳስ ግብ ለመሆን ከጫፍ የደረሰ ነበር። ከዚህ ሙከራ በተጨማሪ በ39ኛው ደቂቃ ዮናታን ፍሰሀ ከመስመር ያሻገረውን ኳስ ቤዛ መድህን ሞክሮት በድጋሜ መክብብ በሚገርም ሁኔታ ያመከነው ኳስ እጅግ አስቆጪ ነበር። አጋማሹም በሲዳማ ቡና መሪነት ተገባዷል።

ሁለተኛውን አጋማሽ በተሻለ ተነሳሽነት የቀረቡት ወልቂጤዎች በተደጋጋሚ የሲዳማ ቡና የግብ ክልል እየደረሱ ጥቃት ለመፈፀም ጥረው አቻ የሆኑበትን ግብ አግኝተዋል። በዚህም በሀምሳኛው ደቂቃ መባቻ ላይ ኳስ በእጅ ተነክቷል በሚል የፍፁም ቅጣት ምት ጠይቀው ቢከለከሉም ከደቂቃዎች በኋላ ጫላ ተሺታ ላይ ጥፋት ተሰርቷል በሚል የዕለቱ ዳኛ ዳንኤል ግርማይ የፍፁም ቅጣት ምት ሰጥተዋቸዋል። በ57ኛው ደቂቃ የተገኘውን የፍፁም ቅጣት ምትም ሀብታሙ ሸዋለም ግብ አድርጎታል።

በእጃቸው የገባው ሦስት ነጥብ ያመለጣቸው ሲዳማዎች አቻ ከሆኑ ከአራት ደቂቃዎች በኋላ ዳግም መሪ ሊሆኑ ነበር። የመዓዘን ምትን መነሻ ያደረገ ኳስም ሙሉዓለም ሞክሮት የግቡ አግዳሚ መልሶታል። በጥሩ ፉክክር ሲደረግ የነበረው ጨዋታ በመጨረሻዎቹ ደቂቃዎች ብዙም ለዐይን ሳቢ አልነበረም። ተጨማሪ ሙከራዎችም ሳይደረጉ ጨዋታው በአቻ ውጤት ተጠናቋል።

በውጤቱ መሰረት ወልቂጤ ከተማ እና ሲዳማ ቡና ነጥባቸውን 32 እና 44 ቢያደርሱም በቅደም ተከተል ባሉበት 10ኛ እና 3ኛ ደረጃ ላይ ፀንተው ተቀምጠዋል።