ሀዋሳ ከተማ የሁለት ተጫዋቾችን ዝውውር አጠናቀቀ

የአሰልጣኝ ዘርአይ ሙሉው ሀዋሳ ከተማ በዛሬው ዕለት ሁለት ተጫዋቾችን በይፋ አስፈረሟል።

በቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ የዘንድሮውን የውድድር ዓመት አራተኛ ደረጃን በመያዝ ያጠናቀቀው የአሰልጣኝ ዘርአይ ሙሉው ሀዋሳ ከተማ ለቀጣዩ የውድድር ዓመት ተጠናክሮ ለመቅረብ ይረዳው ዘንድ በዛሬው ዕለት የሁለት ተጫዋቾችን ዝውውር ማጠናቀቁን ክለቡ ለሶከር ኢትዮጵያ አረጋግጧል፡፡

በረከት ሳሙኤል የክለቡ የመጀመሪያው ፈራሚ ሆኗል፡፡ የቀድሞው የሱሉልታ፣ ሙገር እና ድሬዳዋ ከተማ ተጫዋች የምስራቁን ክለብ ድሬዳዋ ከተማን ከለቀቀ በኋላ በዘንድሮው የውድድር ዓመት በሰበታ አሳልፎ ለቀጣዮቹ ሁለት የውድድር ዓመታት ሀዋሳን ለማገልገል በዛሬው ዕለት ፊርማውን አኑሯል፡፡


ሌላኛው ፈራሚ እዮብ አለማየሁ ነው፡፡ ከወላይታ ድቻ ወጣት ቡድን 2008 ከተገኘ በኋላ ለአራት አመታት በክለቡ ዋናው ቡድን ግልጋሎት መስጠት የቻለው የመስመር አጥቂው በጅማ አባ ጅፋር አመቱን ካሳለፈ በኋላ ሀዋሳን የተቀላቀለ ሁለተኛው ፈራሚ መሆን ችሏል፡፡