ፋሲል ከነማ የመስመር ተከላካዮች አስፈርሟል

አፄዎቹ የኋላ መስመራቸውን በዝውውር ማጠከራቸውን በመቀጠል ሁለት የመስመር ተከላካዮችን ሲያስፈርሙ የአንድ ተጫዋች ዉልም አድሰዋል።

የውድድር ዓመቱን ሁለተኛ ደረጃ ይዘው ያጠናቀቁት ፋሲል ከነማዎች የዝውውር መስኮቱ ከተከፈተ ወዲህ ከተወሰኑ ተጫዋቾች ጋር ሲለያዩ የሌሎች ተጫዋቾችን ውል ማራዘም ላይ ትኩረት አድርገው ቆይተዋል። አዲስ ቅጥር በመፈፀሙ በኩል ትናንት መናፍ ዐወልን በመጀመሪያ ፈራሚነት ወደ ስብስባቸው የቀላቀሉ ሲሆን ዛሬ ደግሞ ሁለት ተጨማሪ ተጫዋቾችን ለሁለት ዓመታት በሚዘልቅ ውል የቡድናቸው አካል አድርገዋል።

ከአፄዎቹ ፈራሚዎች አንዱ ተስፋዬ ነጋሽ ሆኗል። በቀኝ መስመር ተከላካይነት አልፎ አልፎም በመስመር አጥቂነት ሚና የሚጫወተው ተስፋዬ ያለፉትን ሁለት ዓመታት በወልቂጤ ከተማ ሲጫወት የቆየ ሲሆን ከዛ ቀድመ ብሎ በጥቁር አባይ ፣ ዳሽን ቢራ ፣ አዳማ ከተማ እና ወልዲያ ማሳለፉ ይታወቃል። ሌላኛው አዲሱ የፋሲል ከነማ ተጫዋች ደግሞ በጅማ አባ ጅፋር የምናውቀው ወንድምአገኝ ማርቆስ ሆኗል። በመስመር እና በመሀል ተከላካይነት ሲጫወት የምናወቀው ወንድምአገኝ ከዚህ ቀደም ለሌላኛው የጅማ ክለብ ጅማ አባ ቡና ሲጫወት መቆየቱ የሚታወስ ነው።

ከእንየው ካሳሁን መልቀቅ በኋላ በቀኝ መስመር ተከላካይ ቦታ ላይ አሁን የሌሉትን አብዱልከሪም መሀመድ እና ሰዒድ ሀሰንን ሲጠቀም የቆየው ፋሲል በሳለፍነው የውድድር ዓመት አመዛኙን የመሰለፍ ዕድል ያገኘው ዓለምብርሀን ይግዛውን ውልም አራዝሟል። በመሆኑም ከዓለምብርሀን በተጨማሪ ሁለቱን ተጫዋቾች በመጨመር ክለቡ በተለይም የቀኝ መስመር ተከላካይ ቦታውን በማያዳግም መልኩ ለማጠናከር ያለሙ ዝውውሮችን ፈፅሟል ማለት ይቻላል።