ሪፖርት | ባህር ዳር ከተማ ከመመራት ተነስቶ ኢትዮ ኤሌክትሪክን አሸንፏል

በደጋፊያቸው ፊት ከከፍተኛ ሊጉ የመጣው ኢትዮ ኤሌክትሪክን የተቀበሉት የጣና ሞገዶቹ በስንታየሁ ዋለጬ ድንቅ ግብ ቢቆጠርባቸውም በመጨረሻ 2-1 መርታት ችለዋል።

ጨዋታው በኢትዮጵያ ብሔራዊ ህዝብ መዝሙር እና በቅርቡ ህይወቱ ላለፈው የቀድሞው ታሪካዊ ተጫዋች ሎቻኖ ቫሳሎ የህሊና ፀሎት በማድረግ የተጀመረ ነበር።

ዝግ ባለ ፍጥነት በኢትዮ ኤሌክትሪክ የተሻለ የኳስ ቁጥጥር በጀመረው ጨዋታ ባህር ዳሮች የበላይ ሆኖ ለመታየት ብዙ ደቂቃ አልወሰደባቸውም። በ6ኛው ደቂቃ ቻርለስ ሪባኑ ከቀኝ በ10ኛው ደቂቃ ደግሞ ሄኖክ ኢሳይያስ ከግራ ወደ ግብ ባሻገሯቸው ኳሶች ያገኟቸውን ዕድሎች ዳዊት ወርቁ እና ሀብታሙ ታደሰ ሳይጠቀሙባቸው ቀሩ እንጂ ቡድኑ በጊዜ መሪ የመሆን አጋጣሚው ነበረው።

ከኋላ ኳስ መስርተው ለመውጣት ይሞክሩ የነበሩት ኤሌክትሪኮች በቀላሉ በባህር ዳር ጫና ውስጥ ወድቀው ሲታዩ ቅብብሎቻቸው በታጋጣሚ ተጫዋቾች እየተቋረጡ እንዲሁም ከኋላ ግለሰባዊ ስህተቶች እየሰሩ ለአደጋ ሲጋለጡ ይታይ ነበር። ሆኖም 12ኛው ደቂቃ ላይ ጉዳት የገጠመው ፍቅረሚካኤል ዓለሙን በአለልኝ አዘነ ለመቀየር የተገደዱት ባህር ዳሮች ኳስ ከማስጣል ባለፈ ሳጥን ውስጥ የገቡባቸውን አጋጣሚዎችም ሆነ ከማዕዘን ምት የሚፈጥሯቸውን ዕድሎች መጠቀም ተስኗቸው ታይተዋል። በዚህም የተጋጣሚያቸውን ድክመት ወደ ውጤት መቀየር ሳይችሉ ቀርተዋል።

በአጋማሹ በተለይ በማጥቃት ሽግግሩ ፍፁም የመናበብ ችግር የታየባቸው ኤሌክትሪኮች ከፈጠሯቸው እና ባልተሳኩ ቅብብሎች ከተቋጩ የመልሶ ማጥቃት ጥቂት ጥረቶች ውጪ ይሄ ነው የሚባል ሙካራ ማድረግ አልቻሉም። በደጋፊያቸው ፊት ችኩልነት ይታይባቸው በነበሩት ባህር ዳሮች በኩልም በተለይ ጥሩ ሲንቀሳቀስ ከነበረው አማካይ ቻርለስ ሪባኑ የሚነሱ ጥራት ያላቸው ኳሶች ይታዩ የነበረ ቢሆንም ዘሪሁን ታደለን የሚፈትን ሙከራ ሳያስመለክቱ ጨዋታው ተጋምሷል።

በሁለተኛው አጋማሽ ነቃ ብለው የተመለሱት ኤሌክትሪኮች ወዲያውኑ አስደንጋጭ ሙከራ አርገዋል። 47ኛው ደቂቃ ላይ አምበሉ ስንታየሁ ዋለጬ በተከላካዮች ላይ ከፍ አድርጎ ያደረሰውን ኳስ ፀጋ ደርቤ ሳጥን ውስጥ ተቆጣጥሮ ያደረገው ሙከራ በግቡ ቋሚ ተመልሶበታል። ከሙከራ ባለፈ ቡድኑ ከመጀመሪያው በታሻለ ኳስ መቆጣጠር እና በባህር ዳር የግብ ደጃፍ ላይ ገፍቶ የመሄድ ምልክትን አሳይቷል። በአንፃሩ ባህር ዳሮች 56ኛው ደቂቃ ላይ ሀብታሙ ታደሰ ከቀኝ ሳጥን ጠርዝ ላይ አክርሮ ከሞከረው ኳስ ውጪ ከዕረፍት መልስ ተቀዛቅዞ ታይቷል።

በሁለተኛው አጋማሽ የጀማረው የኤሌክትሪክ የጨዋታ ብልጫ ቀጥሎ 63ኛው ደቂቃ ላይ ስንታየሁ ዋለጬ ሳይታሰብ ከረጅም ርቀት ወደ ግብ የላካት ኳስ ድንቅ ግብ ሆና ተቆጥራ ቀይ ለባሾቹን ቀዳሚ አድርጋለች።

ከግቡ በኋላም ኤሌክትሪኮች ሜዳ ላይ የተሻለ ቡድን ሆነው ሲቀጥሉ ባህር ዳሮችም ከቀደመው በተሻለ ወደ እንቅስቃሴ ገብተው በጨዋታው ጥሩ ምልልስ መታየት ጀምሯል። ሆኖም 75ኛው ደቂቃ ላይ የኤሌክትሪክ የኋላ መስመር ስህተት አገርሽቶ የመሀል ተከላካዩ ማታይ ሉል በግንባሩ ለግብ ጠባቂ ለማድረስ የሞከረው ኳስ ተቆርጦ ያገኛው ዱሬሳ ሹቢሳ በፍጥነት ወደ ጎል በመድረስ የጣና ሞገዶቹን አቻ አድርጓል።

ከአቻነቱ በኋላ የጨዋታው ፍሰት ወደ መመጣጠን ብሎም ወደ ባህር ዳሮች የበላይነት መጥቶ ታይቷል። በርግጥ ተቀይሮ ገብቶ የነበረው አጥቂ ሄኖክ አየለ 80ኛው ደቂቃ ላይ ከቅጣት ምት ሞክሮ በግቡ አግዳሚ የተመለሰበት ኳስ ኤሌክትሪክን ዳግም መሪ ለማድረግ ተቃርቦ ነበር። ሆኖም ጨዋታው ወደ ማብቂያው ሲቃረብ ሌላ ስህተት ኤሌክትሪክን ዋጋ አስከፍሏል። 87ኛው ደቂቃ ላይ ግብ ጠባቂው ዘሪሁን ታደለ ከማዕዘን የተነሳን ኳስ ወጥቶ ለማዳን ያረገው ጥረት ሳይሳካ ተስፋዬ ታምራት በግንባር በመግጨት አስቆጥሯል። በዚህም በሁለተኛው አጋማሽ ከፍተኛ መሻሻል ያሳየው ኢትዮ ኤሌክትሪክ ውጤቱን ማስጠበቅ ሳይችል በደጋፊያቸው ፊት የተጫወቱት ባህር ዳር ከተማዎች የውድድር ዓመቱን በ2-1 ድል መጀመር ችለዋል።

ከጨዋታው በኋላ በተሰጡ አስተያየቶች  “በአዲስ አበባ ከተማ ዋንጫ ላይ የሰራነውን ስህተት ዛሬም ደግመናዋል” ያሉት አሰልጣኝ ክፍሌ ቦልተና ተጋጣሚያቸው ስህተታቸውን በመጠቀም እንዳሸነፋቸው ገልፀው ሁለተኛው ጎል የተቆጠረበት መንገድ ላይ በግብ ጠባቂያቸው ላይ ጥፋት እንደተሰራበት እንደሚያምኑ ተናግረዋል።

የባህር ዳር ከታማው አሰልጣኝ ደግአረገ ይግዛው በበኩላቸው ቡድናቸው የተሻለ ዕድል ቢፈጥርም በሦስተኛው የሜዳ ክፍል ላይ ድክመት እንደነበረባቸው ገልፀው ተጫዋቾቻቸው እስከመጨረሻው የነበራቸውን የአዕምሮ ጥንካሬ አድንቀዋል።