ሪፖርት | በታታሪነት የተጫወተው አዳማ ከተማ መቻልን ረቷል

በሁለቱ አጋማሾች የተቆጠሩት ሁለት ጎሎች አዳማ ከተማ መቻልን በማሸነፍ የውድድር ዓመቱን የመጀመሪያ ሦስት ነጥብ እንዲያገኝ አስችለዋል።

በመጀመሪያው የጨዋታ ሳምንት በፋሲል ከነማ ሁለት ለአንድ የተሸነፉት አዳማ ከተማዎች በዛሬው ጨዋታ የሁለት ተጫዋቾችን ለውጥ አድርገዋል። በዚህም አሠልጣኝ ይታገሱ እንዳለ የቀይ ካርድ ቅጣት ላይ የሚገኘው ዊሊያም ሠለሞንን በፍሬድሪክ አንሳህ እንዲሁም የግብ ዘቡ ሰዒድ ሀብታሙን በኩዋሜ ባህ ተክተው ጨዋታውን ቀርበዋል። በተቃራኒው ሀዲያ ሆሳዕናን አንድ ለምንም ያሸነፉት መቻሎች ግን ‘አሸናፊ ቡድን አይለወጥም’ በሚለው ብሂል ያመኑ በሚመስል መልኩ አንድም የተጫዋች ለውጥ ሳያደርጉ ወደ ሜዳ ገብተዋል።

ተጠባቂው ጨዋታ ገና በ3ኛው ደቂቃ ግልፅ የግብ ማግባት ሙከራ ተደርጎበታል። በዚህ ደቂቃም መቻሎች ያገኙትን የመጀመሪያ የመዓዘን ምት በፍፁም አማካኝነት አሻምተውት በተከላካዮች ሲመለስ ዳግም ተጫዋቹ ወደ ግብ ልኮት ምንይሉ ወንድሙ በግንባሩ መረብ ላይ ለማሳረፍ ሞክሮ በኢትዮጵያ የመጀመሪያ ጨዋታውን እያደረገ የሚገኘው የግብ ዘብ ኩዋሜ ባህ አድኖታል። በቀጣዮቹ ደቂቃዎችም መቻሎች ፈጣኖቹን አጥቂዎቻቸው በመጠቀም በተደጋጋሚ የአዳማን የግብ ክልል እየጎበኙ ነበር። ከኳስ ጋርም ከኳስ ውጪም ጫናዎች የበዛባቸው አዳማዎች ቀጥተኛ አጨዋወት በመከተል በጨዋታው ቅድሚያ ለመያዝ መንቀሳቀስ ይዘዋል። በ11 እና 12ኛው ደቂቃም ዳዋ ሁቴሳ እና ደስታ ዮሐንስ ከሳጥን ውጪ ተከታታይ ሙከራዎችን ሰንዝረው ለጥቂት ዒላማውን ስቶባቸዋል።

ከሳጥን ሳጥን የማያቋርጥ ምልልስ ማስመልከት የቀጠለው ጨዋታው በ19 ደቂቃ ግብ አስተናግዷል። ደቂቃ በደቂቃ እድገት እያሳዩ የመጡት አዳማዎች አሜ መሐመድ እና አማኑኤል ጎበና በአንድ ሁለት ቅብብል ግብ ለማስቆጠር ሲጥሩ አሜ በአህመድ ረሺድ ሳጥን ውስጥ ጥፋት ተሰርቶበት የፍፁም ቅጣት ምት ያገኙ ሲሆን አጋጣሚውንም አምበላቸው ዳዋ እርጋታ በተሞላበት ሁኔታ መረብ ላይ አሳርፎታል።

የጨዋታውን የኃይል ሚዛን ለመያዝ የሚደረገው ፉክክፍ ቀጥሎ መሐል ሜዳ ላይ የነበረው ፍትጊያ ለመመልከት ሳቢ ነበር። በተለይ መቻሎች ወደ ጨዋታው ለመመለስ የሚያገኟቸውን ኳሶች በፍጥነት ሦስተኛው የሜዳ ክፍል ለማድረስ ሲጥሩ አዳማዎች ደግሞ መሪ ከሆኑ በኋላ ኳሱን በእግራቸው በማድረግ ለመከላከል ሲጥሩ ታይቷል። አዳማዎች ይህንን ቢፈልጉም ግን በረከት ደስታ በ36ኛው ደቂቃ ከፍፁም ዓለሙ የደረሰውን ኳስ ከሳጥን ውጪ አክርሮ መትቶ ግብ ሊያስቆጥርባቸው ነበር። በቀሪ የአጋማሹ ደቂቃዎች ሌላ የጠራ ጥቃት ሳይፈጠር አዳማዎች እየመሩ ለእረፍት ወደ መልበሻ ክፍል አምርተዋል።

የቡድን ውህደት ችግር የሚታይበት መቻል ከመጀመሪያው አጋማሽ በተቃራኒ የሚገኙ ኳሶችን በረጅሙ ወደግብ ምንጭነት ለመቀየር ሲጥር ታይቷል። በተለይ አዳማዎች የሚዘጓቸውን የኳስ ቅብብል መስመሮች ለማለፍ ተንጠልጣይ የዐየር ላይ ኳሶችን መላክ ይዘዋል። በተቃራኒው ጨዋታው በሚፈልጉት መንገድ እየሄደላቸው የሚገኘው አዳማዎች የአማካይ መስመራቸውን በማጠናከር ከኳስ ውጪ ታታሪነት የተሞላበት እንቅስቃሴ ሲያደርጉ ነበር።

የሁለተኛው አጋማሽ የመጀመሪያ ዒላማውን የጠበቀ ሙከራ በ64ኛው ደቂቃ ነበር የተስተናገደው። በዚህ ደቂቃ የተገኘው የቅጣት ምት ተመቶ በተከላካዮች ሲመለስ ያገኘው በረከት አክርሮ መትቶ ግብ ጠባቂው ይዞበታል። ከሁለት ደቂቃዎች በኋላም ይሁ የመስመር አጥቂ ተሾመ በላቸውን ቀይሮ የገባው ሳሙኤል ሳሊሶ የሞከረው ኳስ ሲመለስ አግኝቶ ሌላ ጥቃት ሰንዝሮ ዒላማውን ስቶበታል። ከአምስት ደቂቃዎች በኋላ ግን መቻሎች ሁለተኛ ግብ ሊያስተናግዱ ነበር። በዚህም ደስታ ከግራ መስመር ያሻገረውን ኳስ የግቡ ባለቤት ዳዋ ከግብ ዘቡ ተክለማርያም ሻንቆ ጋር በመዝለል በግንባሩ ግብ ለማስቆጠር ዳድቶ ለጥቂት ወጥቶበታል። ከዚህ ሙከራ በተጨማሪ በ80ኛው ደቂቃ አድናን ረሻድ ከቀኝ መስመር ጥሩ ኳስ ልኮ ቦና ዓሊ ሌላ ሙከራ አድርጓል።

ሙሉ የጨዋታው ክፍለ ጊዜ ተጠናቆ ጭማሪ ደቂቃ ሊታይ ሲል አዳማ ከተማ ማስተማመኛውን ጎል አግኝቷል። በዚህም በቡድናዊ መዋቅር በማጥቃቱም ሆነ በመከላከሉ ረገድ በህብረት ሲጫወቱ የነበሩት የአሠልጣኝ ይታገሱ ተጫዋቾች ጫና ፈጥረው የተረከቡትን ኳስ ለመጀመሪያው ጎል መገኘት ምክንያት የሆነው አሜ በግራ እግሩ መረብ ላይ አሳርፎታል። ጨዋታውም በዚሁ ውጤት ተጠናቋል።

ከጨዋታው ሦስት ነጥብ ያገኙት አሠልጣኝ ይታገሱ እንዳለ ጨዋታው ጥሩ እንደነበር ጠቅሰው በመከላከሉ ረገድ ከፋሲሉ ጨዋታ በሚገባ ተሻሽለው እንደመጡ በመናገር በቀጣይ ጨዋታ ባላቸው ሰፊ ቀን ተጠናክረው እንደሚመጡ ሲገልፁ ተደምጠዋል። ተሸናፊው አሠልጣኝ ፋሲል ተካልኝ በበኩላቸው ተጋጣሚያቸው የግብ ቅድሚያ ስለወሰደባቸው ተጫዋቾቹ እንዳይረጋጉ እንዳደረገ ጠቁመው በሁለተኛው አጋማሽ በቁጥር በዝተው ለማጥቃት ቢያስቡም ኳሶች የሚሄዱበት መንገድ ልክ ስላልነበር ግብ እንዳላስቆጠሩ ተናግረዋል።