ሪፖርት | ነብሮቹ ከመመራት ተነስተው ጣፋጭ ድል አግኝተዋል

በሁለተኛው አጋማሽ ከፍተኛ መሻሻል ያሳዩት ሀዲያ ሆሳዕናዎች በድንቅ ሁኔታ በተቆጠሩት አራት ግቦቻቸው ታግዘው ከሲዳማ ቡና ሦስት ነጥብ ወስደዋል።

በመጀመሪያው ሳምንት በመቻል አንድ ለምንም የተሸነፉት ሀዲያ ሆሳዕናዎች ሦስት ነጥብ ካስረከቡበት ጨዋታ ሳምሶን ጥላሁን እና እያሱ ታምሩን በዳግም ንጉሴ እንዲሁም ራምኬል ሎክ ተክተው ወደ ሜዳ ሲገቡ በተመሳሳይ ሳምንት ከድሬዳዋ ከተማ ጋር ሁለት አቻ ተለያይተው የዛሬውን ጨዋታ የቀረቡት ሲዳማ ቡናዎች በበኩላቸው የቀይ ካርድ ቅጣት ላይ የሚገኘው ጊትጋት ኩትን ጨምሮ አማኑኤል አንዳለ፣ አበባየሁ ዮሐንስ እና ሳላዓዲስ ሰዒድን በአንተነህ ተስፋዬ፣ ደግፌ ዓለሙ፣ ሙሉቀን አዲሱ እና አዲሱ ተጫዋቻቸው ጎድዊን ኦባጄ ለውጠዋል።

በመጀመሪያዎቹ አስር ደቂቃዎች ቀዝቃዛ እንቅስቃሴ ሲያሳይ የነበረው የሁለቱ ቡድኖች ጨዋታ በ11ኛው ደቂቃ በተሰነዘረ የመጀመሪያ ዒላማው በጠበቀ ሙከራ ግብ አስተናግዷል። በዚህም ሔኖክ አርፊጮ የቀኝ መስመር ተከላካዮ ደግፌ ዓለሙ ላይ የሰራውን ጥፋት ተከትሎ የተሰጠውን የቅጣት ምት ፍሬው ሠለሞን ሲያሻመው ያኩቡ መሐመድ በግንባሩ መረብ ላይ አሳርፎት ሲዳማ ቡና ቀዳሚ ሆኗል።

ሀዲያ ሆሳዕናዎች ገና በጊዜ መሪነት ቢወሰድባቸውም ወዲያው ወደ ጨዋታው ለመመለስ መንቀሳቀስ ይዘዋል። በመጀመሪያዎቹ ደቂቃዎች የተወሰደባቸውን የኳስ ቁጥጥር ብልጫም በመያዝ ወደ ተጋጣሚ ግብ ክልል እየደረሱ የአቻነት ግብ ለማስቆጠር የጣሩ ሲሆን በተለይ በ21ኛው ደቂቃ ፀጋዬ ብርሃኑ ከባዬ ገዛኸኝ የደረሰውን ኳስ ወደ ግብ የመታው አጋጣሚ ለግብ የቀረቡበት ሁነት ነበር። ከዚህ ሙከራ በተጨማሪም በ37ኛው ደቂቃ ብርሃኑ በቀለ ላይ በተሰራ ጥፋት የተገኘውን የቅጣት ፍቅረየሱስ ተ/ብርሃን አሻምቶት ፍሬዘር ካሣ ጥሩ ኳስ በግንባሩ ሞክሮ ነበር። በቀሪ የአጋማሹ ደቂቃዎች ግን ግብ ሳይስተናገድም ተጫዋቾች ወደ መልበሻ ክፍል አምርተዋል።

አካላዊ ጉሽሚያዎች የበረከቱበት ጨዋታው በሁለተኛው አጋማሽም እምብዛም የጠሩ የግብ ማግባት አጋጣሚዎች አልተፈጠሩበትም። እየተመሩ የመጀመሪያውን የጨዋታ ክፍለ ጊዜ ያገባደዱት ሀዲያዎች ግን በአንፃራዊነት በፍላጎት በቁጥር በርከት ብለው ለማጥቃት ሲሞክሩ ነበር። በ53ኛው ደቂቃም ፀጋዬ ከወደ ግራ ባደላ የሳጥኑ ጫፍ የመጀመሪያ ሙከራውን አድርጎ አቻ ሊያደርጋቸው ነበር። በተቃራኒው ሁለተኛውን አጋማሽ ተዳክመው የጀመሩት ሲዳማዎች ምንም እንኳን በጥራት ባይታጀብም በሀዲያዎች ጫና በዝቶባቸው ታይቷል።

ጨዋታው 60ኛው ደቂቃ ላይ ሀዲያዎች የልፋታቸውን ውጤት አግኝተዋል። በዚህም ብሩክ ማርቆስ የሲዳማ ተጫዋቾች የሰሩትን የቅብብል ስህተት ግርማ በቀለ ሲሰጠው ከሳጥኑ ውጪ በግራ እግሩ በድንቅ ሁኔታ መክብብ ጀርባ የሚገኘው መረብ ላይ አሳርፎታል። ሀዲያ ከስድስት ደቂቃዎች በኋላ በሌላ የሲዳማ ተከላካዮች ስህተት ወደ መሪነት የተሸጋገሩበትን ግብ አግኝተዋል። በተጠቀሰው ደቂቃም ፍቅረየሱስ ከባዬ የደረሰውን ኳስ ከሳጥኑ ጫፍ ግብ አስቆጥሯል።

ወደ መሪነት ከተሸጋገሩ በኋላም ዳግም ሌላ ግብ ለማስቆጠር መጣር የያዙት ነብሮቹ በ73ኛው ደቂቃ አደገኛ ጥቃት ሰንዝረዋል። በእጃቸው የነበረውን መሪነት የተነጠቁት ሲዳማዎች በበኩላቸው በሁለተኛው አጋማሽ እጅግ የወረደ ብቃት ቢያሳዩም አሠልጣኝ ወንድማገኝ ዘግይተውም ቢሆን የተጫዋቾች ለውጦችን በማድረግ ወደ ጨዋታው ለመመለስ ጥረዋል። በመጨረሻ ደቂቃዎችም የአደራደር ቅርፅ ለውጥ በማድረግ ግብ ፍለጋቸውን ቢቀጥሉም አንድም ዒላማውን የጠበቀ ሙከራ ሳያደርጉ ቀርተዋል። ይባስ በመጨረሻዎቹ ደቂቃዎች ተጨማሪ ሁለት ግቦችን አስተናግደዋል።

በቅድሚያ ሙሉ የጨዋታ ክፍለ ጊዜው ሊጠናቀቅ ሁለት ደቂቃዎች ሲቀሩት በጥሩ መናበብ የሲዳማን ተከላካዮች ሲፈትኑ የነበሩት ባዬ እና ፍቅረየሱስ ዳግም ተጣምረው በቀኝ መስመር ራሱን ነፃ አድርጎ ለነበረው ፀጋዬ ብርሃኑ ያመቻቹለትን ኳስ ፀጋዬ በቀኝ እግሩ የቡድኑ ሦስተኛ ግብ አድርጎታል። አራተኛ ዳኛው እያሱ ፈንቴ በጨመሩት አራት ደቂቃዎች መባቻ ላይ ደግሞ ከመሐል ሜዳ አካባቢ የተገኘውን የቅጣት ምት ሔኖክ ሲያሻማው ፀጋዬ ሦስተኛውን ጎል እንዲያስቆጥር አመቻችቶ ላቀበለው ባዬ ውለታ የመለሰበትን ኳስ በደረቱ ሰጥቶት ባዬ የማሳረጊያውን ጎል አስቆጥሯል። በአጠቃላይ 41 ጥፋቶች የተሰሩበት ጨዋታውም በሀዲያ ሆሳዕና 4ለ1 አሸናፊነት ተጠናቋል።

ከጨዋታው ሦስት ነጥብ ያገኙት አሠልጣኝ ያሬድ ገመቹ በድህረ-ጨዋታ አስተያየታቸው ከጨዋታው የፈለጉትን ሦስት ነጥብ አጥቅተው በመጫወት እንዳገኙ በመጠቆም ከእረፍት መልስ የሲዳማ ተከላካዮች እንዲሳሳቱ ጫና ፈጥረው በመጫወት ውጤት እንዳገኙ አመላክተዋል። በጨዋታው ቀዳሚ ቢሆኑም በመጨረሻ እጅ የሰጡትን ሲዳማዎች የሚመሩት አሠልጣኝ ወንድማገኝ ተሾመ በበኩላቸው በመጀመሪያው አጋማሽ ጨዋታውን ተቆጣጥረው እየመሩ ቢያጠናቅቁም በሁለተኛው አጋማሽ ከጠበቁት ውጪ ሲዳማን የማይመጥን ውጤት እንደተመዘገበ ተናግረዋል። በተለይ ደግሞ በተከላካይ፣ በተከላካይ አማካይ እና በአጥቂ አማካዮች ላይ የነበረው ክፍተት ቡድኑን ደካማ እንዳደረገው ሳይሸሽጉ ገልፀዋል።