ሪፖርት | የቅዱስ ጊዮርጊስ የድል ጉዞ ቀጥሏል

በአራተኛው ሳምንት የቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ የሳምንቱ የመክፈቻ ጨዋታ በቅዱስ ጊዮርጊስ እና አዳማ ከተማ መካከል ተከናውኖ የእስማኤል ኦሮ አጎሮ ሁለት ግቦች ቅዱስ ጊዮርጊስን አሸናፊ በማድረግ ተጠናቋል፡፡

አዳማ ከተማ በዳዋ ሆቴሳ ብቸኛ ጎል ሀዋሳን ሲረታ የተጠቀመበትን አሰላለፍ ሳይለውጥ ለጨዋታው ሲቀርብ ቅዱስ ጊዮርጊሶች በበኩላቸው በሲዳማ ቡና ላይ ከተቀናጁት ድል የአንድ ተጫዋች ለውጥ አድርገው ወደ ሜዳ ገብተዋል፡፡ በዚህም መሠረት ዳዊት ተፈራን በአማኑኤል ገብረሚካኤል ተክተው በቋሚ አሰላለፍ ውስጥ አካተዋል፡፡

የሳምንቱ ቀዳሚ በነበረው የሁለቱ ቡድኖች ጨዋታ አጀማመሩ አዳማ ከተማ በአሜ መሀመድ ባደረገው ፈጣን ሙከራ አንፃር የተሻለ ፉክክር የሚያሳየን ይመስል የነበረ ቢሆንም በሂደት ግን እጅጉን የተቀዛቀዘ የጨዋታ አቀራረብን በቡድኖቹ ላይ መመልከት ችለናል፡፡ ይልቁንስ ተደጋጋሚ ጥፋቶች በርክተው በታዩበት የመጀመሪያው አጋማሽ በአዳማ ከተማ በኩል ወሳኙ የመሀል ተከላካይ ሚሊዮን ሰለሞን በእስማኤል ኦሮ አጎሮ ጥፋት ተሰርቶበት ገና በ11ኛው ደቂቃ በዳንኤል ደምሱ ተቀይሮ ለመውጣት ተገዷል፡፡

38ኛው ደቂቃ ላይ ረመዳን የሱፍ ከግራ አቅጣጫ ወደ ጎል የላካትን ኳስ ተከላካዩ አዲሱ ተስፋዬ ከእስማኤል ኦሮ አጎሮ ጋር ኳስ ለመሻማት ባደረገበት ቅፅበት ወደ ራሱ ግብ በግንባር በመግጨቱ ለጥቂት በላይኛው የግቡ ብረት ታካ ወደ ውጪ ወጥታለች ማራኪ ያልነበረው እና 14 ጥፋቶች የተስተናገዱበት ቀዳሚው አጋማሽም 0-0 ተገባዷል፡፡

ከዕረፍት ጨዋታው ሲመለስ ከመጀመሪያው አጋማሽ በተወሰነ መልኩ ቅርፁን የጠበቀ የጨዋታ መንገድን ማስተዋል ጀምረናል፡፡ ቅዱስ ጊዮርጊሶች አብዛኛዎቹን የማጥቂያ መንገዳቸውን ወደ ቀኝ መስመር አስጠግተው በተለይ ቢኒያም በላይ ወደ አማካይ ስፍራ ተጠግቶ ከቸርነት ጉግሳ ጋር ሲጫወት የነበረበት ሂደት አስገራሚ የነበረ ሲሆን አዳማ ከተማዎች በአንፃሩ መሀል ሜዳን ለመቆጣጠር ጥረቶችን ማድረግ ጀምረዋል፡፡

51ኛው ደቂቃ ላይ ቅዱስ ጊዮርጊሶች ቀዳሚ መሆን የቻሉበት ግብ ወደ ካዝናቸው አስገብተዋል፡፡ ጋናዊው ተከላካይ ፍሪምፓንግ ሜንሱ ከራሱ የግብ ክልል በረጅሙ የላካትን ኳስ ቢኒያም በላይ ጋር ደርሳ ፈጣኑ ተጫዋችም ወደ ሳጥኑ እየገፋ ገብቶ ሲመታው በግብ ጠባቂው ክዋሜ ባህ የተመለሰችውን ኳስ አዲሱ ተስፋዬ ለማውጣት ሲጥር ሜዳው አንሸራቶት በመውደቁ አጠገቡ የነበረው ልማደኛው አጥቂ እስማኤል ኦሮ አጎሮ ከመረብ አዋህዷት ቡድኑን ወደ መሪነት አሸጋግሯል፡፡

መሀል ሜዳ በመጠኑም ቢሆን በተረጋጋ ፍሰት ለመንቀሳቀስ የሞከሩት አዳማ ከተማዎች ወደ አቻነት የተሸጋገሩበትን ጎል አግኝተዋል፡፡ 66ኛው ደቂቃ ላይ አማኑኤል ጎበና ከጀሚል ያዕቆብ ጋር ካደረገው ቅብብል በኋላ ያሻገረውን ኳስ አብዲሳ ጀማል በጥሩ ቅልጥፍና ያመቻቸለትን ሳጥን ጠርዝ የነበረው ዳዋ ሆቴሳ የተከላካዮች እና የግብ ጠባቂው ቻርልስን የአቋቋም ስህተት ተመልክቶ አዳማን 1-1 ያደረገች ግብን አስቆጥሯል፡፡ ከጎሏ መቆጠር በኋላ አዳማ ከተማዎች አከታትለው የሦስት ተጫዋቾችን ቅያሪ ካደረጉ በኋላ አመዛኙን የጨዋታ የእንቅስቃሴ የበላይነት ፈረሰኞቹ ወስደዋል፡፡

ከዚህም መነሻነት መደበኛው የጨዋታ ክፍለጊዜ ሊጠናቀቅ ሦስት ያህል ደቂቃዎች ሲቀሩ የአዳማ ከተማው የመሀል ተከላካይ አዲሱ ተስፋዬ በአማኑኤል ገብረሚካኤል ላይ ሳጥን ውስጥ የሰራውን ጥፋት ተከትሎ የተገኘውን የፍፁም ቅጣት ምት እስማኤል ኦሮ አጎሮ ጎል አድርጎታል፡፡ ቶጓዊው አጥቂም በዓመቱ ያስቆጠራቸውን ጎል ዛሬ ካስቆጠረው ሁለት ጭማሪ ጋር ስምንት አድርሶት ጨዋታው በቅዱስ ጊዮርጊስ 2-1 አሸናፊነት ተደምድሟል፡፡

ከጨዋታው መጠናቀቅ በኋላ የአዳማ ከተማው አሰልጣኝ ይታገሱ እንዳለ ለማሸነፍ እንደገቡ ገልፀው ውጥረት እና ጫና የበዛበት ጨዋታ እንደነበር ጠቁመው የዕለቱ ዳኛ የሰጡት የፍፁም ቅጣት ምት ግን ተገቢ አለመሆኑን ለዕለቱ ዳኛ መናገራቸውን ተናግረዋል፡፡ የአሸናፊው የቅዱስ ጊዮርጊስ አሰልጣኝ ዘሪሁን ሸንገታ በበኩላቸው ከባድ ጨዋታ እንደነበር ጠቁመው የፈለጉትን ውጤት ስለማግኘታቸው ሀሳባቸውን ገልፀዋል፡፡