ሲዳማ ቡና አሠልጣኝ ሾሟል

ወንድማገኝ ተሾመን ያሰናበተው ሲዳማ ቡና በምትኩ አዲስ አሠልጣኝ ማግኘቱን ሶከር ኢትዮጵያ አረጋግጣለች።

በተጠናቀቀው ቤትኪንግ ኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ 3ኛ ደረጃን ይዞ የፈፀመው ሲዳማ ቡና በክረምቱ የተጫዋቾች የዝውውር መስኮት ራሱን ለማጠናከር ጥሮ የ2015 ውድድሩን ቢቀርብም ባሰበው መንገድ መጓዝ አልቻለም። ከሦስት ጨዋታዎችም በአንዱ ብቻ ነጥብ በማሳካት በደረጃ ሰንጠረዡ ግርጌ ላይ ተቀምጧል። ይህንን ተከትሎ የክለቡ ቦርድ አሠልጣኝ ወንድማገኝ ተሾመን ከመንበሩ ማንሳቱ ይታወቃል።

ቦታውን ለመረከብ ሦስት አሠልጣኞች ታጭተው የነበረ ሲሆን ድረ-ገፃችን አሁን ከክለቡ ጽሕፈት ቤት ባገኘችው መረጃ ግን አሠልጣኝ ሥዩም ከበደ ትናንት ምሽት ከክለቡ አመራሮች ጋር በአካል ሀዋሳ ላይ ንግግር ካደረጉ በኋላ በሁለት ዓመት ውል ኃላፊነቱን ለመቀበል ተስማምተዋል። በዚህም አሠልጣኙ ረፋድ ላይ አሁን ከሚገኙበት ሀዋሳ ወደ መዲናችን አዲስ አበባ ከተጓዙ በኋላ አመሻሽ ላይ ቡድኑ ወደሚገኝበት ባህር ዳር በማቅናት ትውውቅ እንደሚያደርጉ አረጋግጠናል።