ሪፖርት | ፈረሰኞቹ እና አዞዎቹ ነጥብ ተጋርተዋል

በታሪክ የመጀመሪያ ሴት የፊፋ ዋና ጸሐፊ የሆኑት ሴኔጋላዊቷ ፋትማ ሳሞራ ስታዲየም ተገኝተው የተከታተሉት የቅዱስ ጊዮርጊስ እና አርባምንጭ ከተማ ጨዋታ 1-1 በሆነ ውጤት ተጠናቋል።

ምሽት 1፡00 ላይ የቅዱስ ጊዮርጊስ እና የአርባምንጭ ከተማ ጨዋታ ሲደረግ ፈረሰኞቹ በአምስተኛው ሳምንት በፋሲል ከነማ 1-0 ሲረቱ ከተጠቀሙት አሰላለፍ የሁለት ተጫዋቾች ለውጥ ሲያደርጉ ሄኖክ አዱኛ እና ጋቶች ፓኖም በሱሌማን ሀሚድ እና ናትናኤል ዘለቀ ተተክተው ጀምረዋል። አዞዎቹ በበኩላቸው በአምስተኛው ሳምንት በኢትዮጵያ ቡና 2-0 ሲረቱ ከተጠቀሙት አሰላለፍ የስምንት ተጫዋቾች ለውጥ ሲያደርጉ አሸናፊ ፊዳ ፣ ላርዬ ኢማኑኤል እና ተመስገን ደረሰ ብቻ ካለፈው ጨዋታ የቀጠሉ ተጫዋቾች ናቸው።

የመጀመሪያው አጋማሽ የመጀመሪያ ደቂቃዎች የተቆራረጡ ኳሶች የበዙበት እና እጅግ አሰልቺ እንቅስቃሴ የታየበት ነበር። አዞዎቹ ከሚታወቁበት ወደተቃራኒ የግብ ክልል ተጠግቶ ቅብብሎች እንዳይጀመሩ በማድረግ እንዲሁም በሚያገኙት ኳስ በተለይም ከቆሙ ኳሶች የግብ ዕድል የመፍጠር አጨዋወት ከተጋጣሚ የግብ ክልል ውስጥ በተደጋጋሚ በቁጥር በዝተው ሲገኙ እና ፈረሰኞቹ ላይ ጫና ሲፈጥሩ ተስተውሏል። ሆኖም የቅዱስ ጊዮርጊስን የኳስ ፍሰት ከማቋረጥ ባለፈ ከኳስ ጋር ስኬታማ ቅብብሎችን ሲከውኑ አልታዩም።

30ኛው ደቂቃ ላይ በርናንድ ኦቼንግ እና አካሉ አትሞ ቅብብል ላይ በሰሩት ስህተት ኳሱን አቋርጦ ማግኘት የቻለው አማኑኤል ገብረሚካኤል በፍጥነት ገፍቶ የወሰደውን ከሳጥን ውጪ በድንቅ አጨራረስ አስቆጥሮ ፈረሰኞቹን መሪ ማድረግ ችሏል። ይሄም በመጀመሪያው አጋማሽ የመጀመሪያው ዒላማውን የጠበቀ ሙከራ ነበር።

ፈረሰኞቹ ከግቧ መቆጠር በኋላ በመጠኑም ቢሆን የተሻለ ሲንቀሳቀሱ 36ኛው ደቂቃ ላይ ረመዳን የሱፍ እና ቢንያም በላይ በጥሩ ቅብብል ወደ ተጋጣሚ ሳጥን ይዘውት የገቡትን ኳስ ረመዳን የሱፍ ሲሞክር ዒላማውን ባለመጠበቁ በግቡ የግራ ቋሚ በኩል ወጥቶበታል።

አዞዎቹ በተደጋጋሚ እየተጫኑ ኳስ ነጥቀው ግብ ለማስቆጠር ሲሞክሩ 40ኛው ደቂቃ ላይ ምኞት ደበበ ኳስ ሲያቀብል በሠራው ስህተት ያገኘው ኤሪክ ካፓይቶ ከግራ መስመር ለተመስገን ደረሰ ሲያቀብል ኳሱን ባልተረጋጋ ሁኔታ ያገኘው ተመስገን በግራ እግሩ ሙከራ ቢያደርግም ኳሱ ዒላማውን ሳይጠብቅ በቀኙ ቋሚ በኩል ወጥቷል። በሦስት ደቂቃዎች ልዩነት ከግራ መስመር ሱራፌል ዳንኤል ያሻማውን ኳስ ያገኘው ተመስገን ደረሰ ኃይል ባልነበረው በግንባር የተገጨ ኳስ ትልቅ የግብ ዕድል አባክኗል።

ከዕረፍት መልስ ጨዋታው እጅግ ተቀዛቅዞ ሲቀጥል 58ኛው ደቂቃ ላይ ቸርነት ጉግሳ በግራ መስመር ወደ ሳጥን ገፍቶ ያስጠጋውና ለእስማኤል ኦሮ አጎሮ ሰጥቶት አጎሮ ወደ ግብ ሞክሮት ግብ ጠባቂው የያዘው ኳስ የተሻለው የመጀመሪያ ሙከራ ነበር። አዞዎቹ በጨዋታው የተሻለ ሙከራ ያደረጉት 75ኛው ደቂቃ ላይ ሲሆን መሪሁን መስቀለ ከረጅም ርቀት ወደግብ የሞከረውን ኳስ መቆጣጠር ያልቻለው ቻርለስ ሉክዋጎ ዕድለኛ ሆኖ ኳሱ ወደ ውጪ ሊወጣለት ችሏል።

ጨዋታው በሚቆራረጡ ቅብብሎች ሲቀጥል 84ኛው ደቂቃ ላይ አካሉ አትሞ ከረጅም ርቀት ኳስ ሲያሻማ የጊዜ አጠባበቅ ስህተት የሰራው በጨዋታው የተረጋጋ ያልነበረው ቻርለስ ሉክዋጎ ኳሱን ባገኘው አህመድ ሁሴን ላይ በሰራው ጥፋት የተሰጠውን የፍፁም ቅጣት ምት ኤሪክ ካፓይቶ አስቆጥሮ አዞዎቹን አቻ ማድረግ ችሏል። ጨዋታውም 1-1 በሆነ ውጤት ተጠናቋል።

ከጨዋታው መጠናቀቅ በኋላ የፈረሰኞቹ አሠልጣኝ ዘሪሁን ሸንገታ ጨዋታው ጠንካራ እንደነበር ገልፀው በመጀመሪያው አጋማሽ ተጋጣሚ በፈጠረው ስህተት ግብ አስቆጥረው መሪ ቢሆኑም በሁለተኛው አጋማሽ ወርደው መታየታቸው እና ባለቀ ሰዓት የግብ ዘባቸው ስህተት በመስራቱ ነጥብ መጋራታቸውን ተናግረዋል። በጨዋታው የማጥቃት አጨዋወታቸውም አጥጋቢ እንዳልነበር አስረድተዋል።

የአዞዎቹ አሠልጣኝ መሳይ ተፈሪ በበኩላቸው ካለፉት አምስት ጨዋታዎች ግምገማ በኋላ ሜዳውን እና ያሉትን ተጫዋቾች ታሳቢ በማድረግ የአጨዋወት ለውጥ እንዳደረጉ ገልፀው ከሽንፈት መጥተው ከጠንካራ ተጋጣሚ አንድ ነጥብ ማግኘታቸው መጥፎ እንዳልሆነ ተናግረዋል። የአቻ ውጤቱም ቡድኑን እና ደጋፊዎቻቸውን እንደሚያነሳሳ ገልፀው ከትዕግስት ጋር በቀጣይ የተሻለውን አርባምንጭ እንደሚያሳዩ ሲናገሩ ተደምጠዋል።