ከፍተኛ ሊግ | የምድብ ሐ ውሎ

በከፍተኛ ሊጉ 7ኛ ሳምንት ሆሳዕና ላይ ከተደረጉ የዛሬ ሦስት ጨዋታዎች ሁለቱ ነጥብ በመጋራት ሲጠናቀቁ ሀምበርቾ ዱራሜ በስድስት ነጥቦች ልዩነት ምድቡን እንዲመራ ያስቻለውን ድል አሳክቷል።

በጫላ አቤ

ሶዶ ከተማ 0-1 ሀምበርቾ ዱራሜ

በዕለቱ ቀዳሚ ጨዋታ የመጀመሪያው አጋማሽ ሀምበሪቾ ዱራሜዎች ተሽለው የተገኙ ሲሆን ቶሎ ቶሎ ወደ ተቃራኒ ግብ በመድረስ ጫና ሲፈጥሩ እና የግብ ዕድል ሲያገኙ ተስተውሏል ፤ ሆኖም ወደ ግብ መቀየር ቀላል አልሆነላቸውም። በተመሳሳይ በሶዶ ከተማ በኩል አልፎ አልፎ የሚያገኙትን የግብ ዕድል መጠቀም ሳይችሉ ቡድኖቹ ያለ ምንም ግብ ወደ መልበሻ ክፍል አምርተዋል።

\"\"

ሁለተኛው አጋማሽ ሞቅ ብሎ የተጀመረ እና ፈጣን እንቅስቃሴ የታየበት ነበር። ሀምበሪቾ ዱራሜ ግብ ለማስቆጠር በጣም ተጭነው ለመጫወት የሞከሩበት እና ሶዶ ከተማ ወደ ኋላ በማፈግፈግ ግብ እንዳይቆጠርበት ሲጥር የታየበት አጋማሽ ነበር። ሆኖም በ82ኛው ደቂቃ ላይ ሀምበሪቾ ዱራሜዎች ግብ ለማስቆጠር ከጫፍ ደርሰው የሶዶ ከተማ ግብ ጠባቂ እና የግቡ ቋሚ ብረት ወደ ውጪ በመውጣቱ የተገኘውን የማዕዘን ምት የኋላ ደጀናቸው እና የቡድኑ አምበል የሆነው እንዳለ ዮሐንስ የተሻገረለትን ኳስ በማስቆጠር ሀምበሪቾ ዱራሜ ስድስተኛ ተከታታይ ድላቸውን እንዲቀናጁ ማድረግ ችለዋል።
በውጤቱም ሽንፈትን የቀመሰው ሶዶ ከተማ እዛው በደረጃ ግርጌ ላይ ሲቆይ ድል ያደረገው ሀምበሪቾ ዱራሜ ተከታዮቹ ደሴ ከተማ እና ኮልፌ ክፍለ ከተማ ነጥብ መጣላቸውን ተከትሎ የነጥብ ልዩነቱን ወደ ስድስት ማስፋት ችሏል።

ጅማ አባ ጅፋር 1-1 የካ ክፍለ ከተማ

\"\"

በዕለቱ ሁለተኛ ጨዋታ የመጀመሪያው አጋማሽ ለዓይን ሳቢ እና ፈጣን እንቅስቃሴ የታየበት ጨዋታ በሁለቱም በኩል የማይቆራረጥ የኳስ ቅብብል ያየንበት ነበር። በ32ኛው ደቂቃ የካዎች በጥሩ የኳስ ቅብብል ያገኙትን የግብ ዕድል በፉዓድ መሐመድ አማካኝነት በማስቆጠር መሪ መሆን የቻሉበትን አጋጣሚ ፈጥረው አጋማሹን በበላይንነት ጨርሰዋል።

ሁለተኛው አጋማሽ ጅማ አባ ጅፋሮች ግብ ለማስቆጠር ከፍተኛ በሆነ ፍላጎት በመግባታቸው የካዎች ላይ ጫና በማሳደር ግብ ለማስቆጠር ጥረት ሲያደርጉ ተመልክተናል። በ66ኛው ደቂቃ ለጅማ አባ ጅፋር ተቀይሮ በገባው ሱራፌል ፍቃዱ ላይ የየካ ክ/ከተማ ሳጥን ውስጥ በተሰራበት ጥፋት የተገኘውን ፍፁም ቅጣት ምት ሱራፌል ዐወል በማስቆጠር ጅማ አባ ጅፋርን አቻ ማድረግ ችሏል። በጨዋታው ከተፈጠሩ ሁነቶች ውስጥ 60ኛው ደቂቃ ላይ የየካው የፊት መስመር ተጫዋች ወደ ጅማ አባ ጅፋር የግብ ክልል አክርሮ የመታትን ኳስ ለማዳን ሲጥር የነበረው የአባ ጅፋሩ ግብ ጠባቂ ዮሐንስ በዛብህ ከግቡ ቋሚ ጋር በመጋጨቱ ምክንያት ከበድ ያለ አደጋ በማስተናገዱ ጨዋታው ለተወሰነ ደቂቃ ተቋርጦ የነበረበት አጋጣሚ ትኩረትን የሳበ ነበር።

ኦሜድላ 0-0 ሮቤ ከተማ

በዕለቱ የመጨረሻ ጨዋታ የመጀመሪያው አጋማሽ ቀዝቀዝ ያለ እና ብዙ የግብ ሙከራ ያልተመለከትንበት አጋማሽ ነበር። በኳስ ቁጥጥሩ በኩል ኦሜድላዎች ተሽለው የተገኙ ሲሆን በሮቤ ከተማ በኩልም በረጃጅም ኳሶች ለመጠቀም ሲጥሩ ተመልክተናል።

ሁለተኛው አጋማሽ ከመጀመሪያው አጋማሽ የተሻለ እንቅስቃሴ የታየበት እና በሁለቱም በኩል ግብ ለማስቆጠር ፍላጎት ያየንበት አጋማሽ ነበር። የኦሜድላው የመሀል አማካይ ቻላቸው ቤዛ ጥሩ እንቅስቃሴ ሲያደርግ እና የቡድኑን የኳስ ስርጭት ሲያደራጅ ተመልክተናል። ሆኖም ሁለቱም ቡድኖች ግብ ሳያስቆጥሩ ነጥብ ተጋርተው ወጥተዋል።

\"\"