መረጃዎች | 55ኛ የጨዋታ ቀን

ቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ በ14ኛ ሳምንት ጨዋታዎች ሲመለስ ነገ የሚከናወኑትን ሁለት ፍልሚያዎች የተመለከቱ መረጃዎችን አሰናድተናል።

ኢትዮጵያ መድን ከ አዳማ ከተማ

የጨዋታ ሳምንቱ በደረጃ ሰንጠረዡ ሁለት ፅንፎች የሚገኙ ሁለት ቡድኖችን በማገናኘት ይጀምራል። ዘንድሮ ወደ ሊጉ የተመለሰው ኢትዮጵያ መድን በአስከፊ ሽንፈት ዓመቱን ቢጀምርም ጥሩ ጉዞ ባደረገባቸው ቀጣይ 12 ጨዋታዎች 26 ነጥቦችን ሰብስቦ በቅዱስ ጊዮርጊስ በግብ ክፍያ ተበልጦ ሁለተኛ ደረጃ ላይ እንዲቀመጥ አስችለውታል። በአንፃሩ የእስካሁኖቹ ሳምንታት ለአዳማ ከተማ የተደላደሉ ነበሩ ለማለት ያስቸግራል። በእርግጥ ቡድኑ በመጨረሻ ሦስት ጨዋታዎች ያሳካቸው ሰባት ነጥቦች በከፋ ሁኔታ ውስጥ እንዳይቆይ ቢረዳውም አሁንም ለወራጅ ቀጠናው በቅርብ ርቀት ላይ ይገኛል። የመጨረሻዎቹን ጨዋታዎች መልካም አቋም አስቀጥሎ በውጤት ለመረጋጋት የሚያደርገውን ጉዞም ከዕረፍት በኋላ ቢያንስ እስከ ቅዱስ ጊዮርጊስ ቀጣይ ጨዋታ ወደ መሪነት የመመለስ ዕድል ካለው ኢትዮጵያ መድን ጋር በመፋለም ይጀምራል።

ጨዋታውን አስመልክቶ በኢትዮጵያ መድን በኩል ያሉ መረጃዎችን ለማግኘት ያደረግነው ጥረት ባይሳካም ትናንት አመሻሽ ድሬዳዋ የደረሱት አዳማ ከተማዎች በኩል ዳዋ ሆቴሳ በጉዳት የማይኖር ሲሆን አማካዩ ፌደሪክ ሀንሰን ደግሞ ባጋጠመው መጠነኛ ጉዳት ጨዋታዎን በተጠባባቂነት የሚጀምር ይሆናል።

\"\"

ሁለቱ ቡድኖች በሊጉ እስካሁን 18 ጊዜ የተገናኙ ሲሆን አዳማ 6 በማሸነፍ ቅድሚያውን ሲይዝ መድን 3 አሸንፏል ፤ በ9 ጨዋታዎች አቻ ተለያይተዋል። አዳማ 18 ፣ መድን 16 አስቆጥረዋል።

10:00 ላይ የሚጀምረውን ይህንን ጨዋታ በመሀል ዳኝነት ለመምራት የተመደበው ባህሩ ተካ ሲሆን በቅርቡ የኢንተርናሽናል ባጅን ያገኘው ሙስጠፋ መኪ እና ሲራጅ ኑርበገን በረዳትነት ፣ ዮናስ ካሳሁን ደግሞ በአራተኛ ዳኝነት በጋራ ይመሩታል።

ድሬዳዋ ከተማ ከ አርባምንጭ ከተማ

በምሽቱ ጨዋታ ውድድሩ ዳግም ወደ መቀመጫ ከተማቸው የተመለሰላቸው ድሬዳዋ ከተማዎች ከአርባምንጭ ከተማ ጋር ይገናኛሉ። ብርቱካናማዎቹ በከተማቸው በመጨረሻ ሁለት ሽንፈቶችን ያስተናግዱ እንጂ ሰባ ሁለት በመቶ የሚሆነውን ነጥባቸውን ያሳኩት በሜዳቸው ባደረጓቸው ጨዋታዎች እንደመሆኑ ድንገተኛው የውድድር ቦታ ለውጥ መልካም ዜና እንደሆነላቸው መናገር ይቻላል። አበበ ጥላሁን እና ዮሴፍ ተስፋዬን በማስፈረም የተከላካይ መስመራቸውን ያጠናከሩት አርባምንጭ ከተማዎች ውድድሩ ከዕረፍት ሲመለስ ብዙ ለውጥ ካደረጉ ክለቦች ውስጥ ሆነው ለነገው ጨዋታ ደርሰዋል። ከዝውውሮቹ ባሻገር የአሕመድ ሁሴንን ውል ከማራዘማቸው ሌላ የምክትል አሰልጣኞች ለውጥ ጭምር አድርገዋል። እነዚህ ለውጦች ለወራጅ ቀጠናው የቀረበው ቡድን ላይ የሚኖራቸው ተፅዕኖ ምን መሳይ እንደሚሆን ከነገ ጀምሮ የሚታይ ይሆናል።

ከ10 ቀናት ዕረፍት በኋላ ወደ ልምምድ የተመለሱት ድሬዳዋ ከተማዎች ብሩክ ቃልቦሬን በህመም ሱራፌል ጌታቸውን ደግሞ በጉዳት አጥተዋል። በአንፃሩ አቤል ከበደ እና ዳንኤል ተሾመ ከጉዳት ተመልሰዋል። በአርባምንጭ ከተማም በተመሳሳይ ለ10 ቀናት ዕረፍት ሰጥቶ ወደ ልምምድ የተመለሰ ሲሆን በትናንትናው ዕለት ድሬዳዋ ደርሷል። በቡድኑ ውስጥም ከአሸናፊ ኤልያስ ውጪ የተሰማ የጉዳት ዜና የለም።

\"\"

ቡድኖቹ በሊጉ አስር ጊዜ ተገናኝተው አርባምንጭ 4 ሲያሸንፍ ድሬዳዋ 2 አሸንፏል ፤ 4 ጊዜ ደግሞ አቻ ተለያይተዋል። በጨዋታዎቹ አርባምንጭ 10 ፣ ድሬዳዋ ደግሞ 5 ጎሎችን ማስቆጠር ችለዋል።

ከሰሞኑ አንጎላ ላይ የተደረገን የቻምፒዮንስ ሊግ ጨዋታን በአራተኛ ዳኝነት የመራው ኢንተርናሽናል ዳኛ ቴዎድሮስ ምትኩ በዋና ዳኝነት ፣ በተመሳሳይ አንጎላ ቆይታን አድርጎ የመጣው ኢንተርናሽናል ረዳት ዳኛ ተመስገን ሳሙኤል እና ኤፍሬም ኃይለማርያም በረዳትነት ፣ ኢንተርናሽናል ዳኛ ለሚ ንጉሴ በበኩሉ በአራተኛ ዳኝነት ጨዋታውን የሚመሩ ይሆናል።