ሪፖርት | የቡናማዎቹ እና የጦና ንቦቹ ጨዋታ ያለ ግብ ተጠናቋል

የኢትዮጵያ ቡና እና ወላይታ ድቻ ጨዋታ እንደመጀመሪያው ዙር ሁሉ 0-0 ተፈፅሟል።

ኢትዮጵያ ቡና ከፋሲል ከነማ ጋር አቻ ከተለያየው ስብስብ ምንም ለውጥ ሳያደርግ ወደ ሜዳ ሲገባ ወላይታ ድቻም ከባህር ዳር ከተማ ጋር አቻ ከተለያየው ስብስብ ስንታየሁ መንግሥቱን በዘላለም አባተ ቀይረው ወደ ሜዳ ገብተዋል።

\"\"

ቀዝቀዝ ብሎ በጀመረው የመጀመርያው አጋማሽ በሁለቱም ቡድኖች በኩል ብዙ ጥራት ያላቸው ሙከራዎች ያልታዩበት ነበር። ቃልኪዳን ዘላለም በተሰለፈበት የቀኝ መስመር ለማጥቃት የሞከሩት የጦና ንቦች በአጋማሹ ጥሩ የተንቀሳቀሰው ቃልኪዳን ከሳጥን ውጭ በመታው ኳስ የመጀመርያ ሙከራቸውን አድርገዋል። ቡድኑ በፈጣን የማጥቃት ሽግግር ዕድሎች ቢፈጥርም ወደ ሙከራነት የተቀየሩት ግን ጥቂት ናቸው።

ዘግይተውም ቢሆን የኳስ ቁጥጥር ብልጫውን መልሰው ያገኙት ቡናዎች በነበራቸው ደካማ የፈጠራ አቅም በአጨዋወቱ የጠራ የግብ ዕድል መፍጠር አልቻሉም። ሆኖም ከመስመር በተሻሙ ኳሶች ዕድሎች ፈጥረዋል። በተለይም መስፍን ታፈሰ ከሳጥን ውጭ መትቶ ግብ ጠባቂው ያወጣበት ኳስ እና ብሩክ በየነ ከመስመር የተሻማው ኳስ በግንባር ያደረገው ሙከራ ለግብ የቀረቡ ነበሩ። በአርባ ሦስተኛው ደቂቃም የመሀል ዳኛው ኤፍሬም ደበሌ በወላይታ ድቻ ሳጥን ውስጥ ኳስ በእጅ ተነክቷል በሚል የፍፁም ቅጣት ምት ሰጥተው ከአራት ደቂቃዎች ንትርክ በኋላ አማኑኤል ዮሐንስ መትቶ አምክኖታል።

እንደ መጀመርያው አጋማሽ በተመሳሳይ የጠሩ የግብ ዕድሎች ያልተፈጠሩበት ሁለተኛው አጋማሽ በኳስ ቁጥጥር ረገድ የቡናማዎቹ ብልጫ የታየበት ነበር። ሆኖም ቡናማዎቹ እንደወሰዱት ብልጫ ከኳስ ጀርባ የሚከላከሉትን የጦና ንቦች አልፈው የግብ ዕድሎች ለመፍጠር ተቸግረዋል። ቡናዎች ወደ ሙከራነት ከቀየሯቸው ዕድሎች በኩልም ከማዕዝን የተሻማውን ኳስ አንተነህ ጨርፎት ብሩክ በየነ ከግቡ ፊት ሆኖ ወደ ላይ ያወጣው ኳስ እና አማኑኤል ዮሐንስ ብሩክ በየነ ያመቻቸለትን ኳስ ተጠቅሞ ያደረገው ወደ ግብነት የቀረበ ሙከራ ይጠቀሳሉ።

እንደ አጀማመራቸው በሁለተኛው አጋማሽ ጥሩ እንቅስቃሴ ማድረግ ያልቻሉት የጦና ንቦች በአናጋው ባደግ እና ስንታየሁ መንግሥቱ አማካኝነት ሙከራዎች አድርገው ነበር ፤ በተለይም አበባየሁ በግሩም ሁኔታ አሻምቷት ስንታየሁ መንግስቱ ከመሞከሩ በፊት ክዌኩ ወደ ውጭ ያወጣት ኳስ ቡድኑ ከፈጠራቸው ዕድሎች የተሻለ ለግብ የቀረበች ነበረች።

በቡናዎች በኩልም መሐመድኑር ናስር ከቅጣት ምት በቀጥታ መቷት ግብ ጠባቂው በጥሩ ብቃት ያወጣት ኳስ በሙሉ የጨዋታው ክፍለግዜ በቡድኑ ከተፈጠሩት ሙከራዎች የተሻለ ለግብ የቀረበ ነበር። ቅያሪዎች ከተደረጉ በኋላ በመጨረሻዎቹ ደቂቃዎች የተሻሉ የማጥቃት ለውጦች ያስመለከተን ጨዋታው ምንም እንኳ ጥራት ያላቸው ለግብ የቀረቡ ሙከራዎች ባይታይበትም በፉክክር ረገድ ግን የተሻለው የጨዋታው ክፍለ ግዜ ነበር። ያም ቢሆን ጨዋታው ያለግብ ተጠናቋል።

ከጨዋታው በኋላ በተሰጡ አስተያየቶች የኢትዮጵያ ቡናው አሰልጣኝ ዮሴፍ ተስፋዬ \”ፍፁም ቅጣት ምቱ ቢገባ ጥሩ ነበር ሌላ ዕድሎች ለመፍጠርም መንገድ ይከፍትልን ነበር\” ካሉ በኋላ \”ተጋጣምያችን በዚህ አጨዋወት እንደሚገቡ ጠብቀን ነበር ፤ ክፍተቶች አግኝተንም ዕድሎች ፈጥረናል ፍፁም ቅጣት ምቱም በዛ መንገድ የተገኘ ነበር \” ብለዋል። ስለ አማካዮች እና አጥቂዎች መናበብ የተጠየቁት አሰልጣኙ \”በምንፈልገው ደረጃ እየተንቀሳቀሱ አይደሉም ከጨዋታ ጨዋታ ግን እየተሻሻሉ ነው \” ብለው በጥምረቱ ያላቸው ተስፋ ገልፀዋል።

\"\"

ቀጥለው ሃሳባቸው የሰጡት የጦና ንቦች አሰልጣኝ ፀጋዬ ኪዳነማርያም \”በፍፁም ቅጣት ምቱ ደስተኛ አልነበርኩም \” ብለው ሃሳባቸው የጀመሩ ሲሆን \”ዳኞች ትዕግስት አልባ ሆነዋል\” ካሉ በኋላ ስለ ተጋጣምያቸው የሚከተለውን አሰተያየት ሰጥተዋል። \”ቡና ጠንካራ ቡድን ነው መስርቶ ለመጫወት የሚሞክር ቡድን ነው ፤ በአማካይ መስመር ክፍተት ላለመስጠት ሞክረን ጥሩ ተሳክቶልናል። በስተመጨረሻም ቅያሬዎች አድርገንም በረጃጅም ኳስ ለማጥቃት ሞክረናል ሆኖም የማጥቃት ችግር አለብን\” በማለት ሃሳባቸውን ቋጭተዋል።