መረጃዎች | ሲዳማ ቡና ከድሬዳዋ ከተማ

በነገው ዕለት የሚደረገውን የመጀመሪያ ጨዋታ የተመለከቱ መረጃዎች አሰባስበናል።

ሲዳማ ቡና እና ድሬዳዋ ከተማ በደረጃ ሰንጠረዡ የወራጅ ቀጠና ባይገኙም ከስጋት ግን ብዙም አልራቁም። በዚህም ሲዳማ ቡና ከወራጅ ቀጠናው በሁለት ነጥብ እና ሦስት ደረጃዎች ፈቅ ሲል ድሬዳዋ ከተማ ደግሞ በአንድ ደረጃ እና አንድ ነጥብ ብቻ ከፍ ብሎ ተቀምጧል። ይህንን ተከትሎ የነገው ጨዋታ ከወራጅ ቀጠናው በአንፃራዊነት በጥሩ ሁኔታ ለመሸሽ ስለሚረዳ ቡድኖቹ ከፍተኛ ትግል ያደርጉበታል ተብሎ ይጠበቃል።

\"\"

በአሠልጣኝ ሥዩም ከበደ የሚመራው ሲዳማ ቡና ባለፉት አምስት ጨዋታዎች ሽንፈት አለማስተናገደጉ ጥሩ የሚባል ሲሆን ያለፉትን ሁለት ጨዋታዎች ደግሞ ተከታታይ ድል አስመዝግቦበታል። በድምሩ ስድስት ነጥብ ያሳካባቸው 2 ጨዋታዎች ደግሞ ቀጥተኛ የወራጅ ቀጠናው ተፋላሚዎች መሆናቸው የድሎቹን ዋጋ ከፍ ያደርግለታል። በተለይ ደግሞ ነገ ድሬን የሚያሸንፍ ከሆነ የደረጃ ሰንጠረዡን ወገብ የሚቆናጠጥበት ዕድል ያገኛል። የወቅታዊው የቡድኑ ጥሩ ጉዞ ዋነኛ ምክንያት የሆነው አጥቂው እና አምበሉ ሳላዲን ሰዒድ ምርጥ መሆን ደግሞ በነገው ጨዋታ የድሬዳዋዎች ፈተና ሊሆን ይችላል።

በመቀመጫ ከተማቸው እየተጫወቱ የሚገኙት ድሬዳዋ ከተማዎች ባለፉት አራት ጨዋታዎች አንድም ነጥብ ማሳካት አልቻሉም። ከነጥቡ ባለፈ በአራቱ ጨዋታዎች ቡድኑ ስምንት ግቦችን ያስተናገደ ሲሆን በተቃራኒው ተጋጣሚ ላይ ያስቆጠተው ጎል ሁለት ብቻ ነው። ይህ ቁጥር ቡድኑ ምን ያህል በሁለቱም የፍፁም ቅጣት ምት ክልሎች እየተቸገረ እንደሆነ ይጠቁማል። ቡድኑ ካለበት ቦታ ዕድገት ለማምጣት የነገው ጨዋታ ወሳኝ ስለሆነ እየተጠቀመበት ያልሆነውን የደጋፊ ጥቅም ነገ በመጠቀም ለማሸነፍ እንደሚጥር ይታሰባል።

ሲዳማ ቡና መሀሪ መና ከጉዳቱ ያገገመለት ሲሆን አዲስ ፈራሚው ደስታ ደሙም ለጨዋታው እንደሚደርስለት ተጠቁሟል ፤ ጋናዊው አጥቂ አጃይ ግን የመሰለፉ ነገር ነገ ረፋድ እንደሚለይ ተጠቅሷል። በድሬዳዋ ከተማ በኩል ግን ምንም የጉዳት እና የቅጣት ዜና እንደሌለ ተመላክቷል።

\"\"

ድሬዳዋ ከተማ እና ሲዳማ ቡና እስካሁን በሊጉ 19 ጊዜ ተገናኝተዋል። ከእነዚህ ግንኙነቶች ሲዳማ ቡና ዘጠኙን በማሸነፍ ቀዳሚ ሲሆን ሁለት ጊዜ ደግሞ ድሬዳዋ ከተማ ረቷል ፤ ቀሪዎቹ ስምንት የእርስ በርስ ግንኙነቶች በአቻ ውጤት የተፈፀሙ ነበሩ። በጨዋታዎቹ ሲዳማ ቡና 22 ድሬዳዋ ከተማ ደግሞ 10 ግቦችን አስቆጥረዋል።

በነገው ጨዋታ ኢንተርናሽናል ዳኛ ቴዎድሮስ ምትኩ በዋና ዳኝነት ግልጋሎት ሲሰጥ ኢንተርናሽናል ረዳት ዳኛ ይበቃል ደሳለኝ እና አማን ሞላ በረዳትነት እንዲሁም ከሰሞኑ ከከፍተኛ ሊጉ ያደገው ሀይማኖት አዳነ በአራተኛ ዳኝነት ለጨዋታው ተሳትፎ ያደርጋሉ።