መረጃዎች | 72ኛ የጨዋታ ቀን

የቤትኪንግ ኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ የ18ኛ ሳምንት የመክፈቻ ሁለት ጨዋታዎችን የተመለከቱ መረጃዎች እንደሚከተለው አሰባስበናል።

ቅዱስ ጊዮርጊስ ከሲዳማ ቡና

በወቅታዊው የደረጃ ሰንጠረዥ በቅደም ተከተል በዋንጫ ፉክክር እና በወራጅ ቀጠናው ግብግብ ውስጥ የሚገኙት ቅዱስ ጊዮርጊስ እና ሲዳማ ቡና በያሉበት ሩጫ ነገ የሚያደርጉት ፍልሚያ ከፍ ያለ ግለት ይኖረዋል ተብሎ ይጠበቃል።

የወቅቱ የሊጉ ሻምፒዮን ቅዱስ ጊዮርጊስ ዳግም ከዋንጫው ጋር ለመገናኘት በጥሩ ሁኔታ ሊጉን እያከናወነ ይገኛል። እስካሁን አንድ ጊዜ ብቻ የተረታው ቡድኑ ያለፉትን አራት ጨዋታዎች በዋንጫ ፉክክር እንዲሁም በወራጅ ቀጠናው ውስጥ የሚገኙ ክለቦችን ገጥሞ ያሳካው ድል በትክክል የዋንጫ ቡድን እንደሆነ ያሳየ ነበር ማለት ይቻላል። በማጥቃቱም ሆነ በመከላከሉ ረገድ ጠንካራ የሆነው ስብስቡም በተለይ በተለያዩ መንገዶች የሚያገኛቸው የግብ አማራጮች ተጋጣሚ በቀላሉ እንዳይገመት አድርጓል። ነገ ደግሞ በሊጉ ሁለተኛ ብዙ ግቦች ያስተናገደውን ሲዳማ መግጠሙ ነገሮችን የበለጠ ቀለል ያደርግለታል ተብሎ ይታሰባል።

\"\"

በውጤት ማጣት ምክንያት አሠልጣኝ ቀይሮ ከባዱን ፍልሚያ እየተጋፈጠ የሚገኘው ሲዳማ ቡና አሁንም ከወራጅ ቀጠናው መራቅ አልቻለም። ቡድኑ ከአራት ጨዋታዎች በኋላ ሁለት ተከታታይ ድሎችን አስመዝግቦ እየተሻሻለ እንደነበር ፍንጭ ቢሰጥም ባለፉት ሁለት ጨዋታዎች ዳግም ወደ ሽንፈት ውጤት ተመልሷል። ከምንም በላይ ደግሞ የወረደው የመከላከል አደረጃጀቱ በየጨዋታው ዋጋ እንዲከፍል ያደርገው ይመስላል። ይህንን የኋላ ሽንቁር ለማስተካከልም አሠልጣኝ ስዩም ባሳለፍነው ሳምንት የተከላካይ መስመራቸው ላይ የውቅር ለውጥ ቢያደርጉም ግብ ከማስተናገድ አልዳኑም።

ቅዱስ ጊዮርጊስ አማኑኤል ገብረሚካኤል ፣ ሀይደር ሸረፋ እና አቤል ዮናስ በነገው ጨዋታ በጉዳት ምክንያት ሲያጣ ሲዳማ ቡና በበኩሉ አሁንም የአጥቂው ይገዙ ቦጋለ እና የተከላካይ አማካዩ ሙሉአለም መስፍንን ግልጋሎት በጉዳት አያገኝም።

ሁለቱ ቡድኖች በሊጉ 25 ጊዜ ተገናኝተው ቅዱስ ጊዮርጊስ 16 ጊዜ በማሸነፍ ሰፊ የበላይነት ያለው ሲሆን ሲዳማ ቡና ሁለት ጊዜ ብቻ አሸንፏል። በቀሪዎቹ ሰባት ጨዋታዎች ደግሞ ቡድኖቹ አቻ ተለያይተዋል። በጨዋታዎቹ ቅዱስ ጊዮርጊስ 37 ሲዳማ ቡና ደግሞ 12 ጎሎችን አስመዝግበዋል።

ጨዋታውን ኢንተርናሽናል ዳኛ በላይ ታደሰ በዋና ዳኝነት ኢንተርናሽናል ረዳት ዳኛ ተመስገን ሳሙኤል እና ሲራጅ ኑርበገን በረዳትነት እንዲሁም ተከተል ተሾመ በአራተኛ ዳኝነት ይመሩታል።

አርባምንጭ ከተማ ከመቻል

በስድስት ደረጃዎች እና በአምስት ነጥቦች ተበላልጠው 14ኛ እና 8ኛ ደረጃ ላይ የተቀመጡት አርባምንጭ ከተማ እና መቻል በተመሳሳት በአንድ ጎል ልዩነት ካስመዘገቡት ሽንፈት ወደ ድል ለመመለስ የሚያደርጉት ፍጥጫ ይጠበቃል።

ካለፉት ስምንት የሊጉ ጨዋታዎች አንዱን ብቻ ያሸነፈው አርባምንጭ ከተማ የወትሮ መገለጫ የሆኑት የማጥቃት እና የመከላከል ባህሪው አሁን አብረውት ያሉ አይመስልም። በተለይ በመከላከል ቡድናዊ አጨዋወት የማይታማ የነበረው ስብስቡ ከ17 ጨዋታዎች ግቡን ሳያስደፍር የወጣው በሦስት አጋጣሚዎች ብቻ ነው። ይህ ክፍተት እጅግ ዋጋ እያስከፈለው ስለሆነ አሠልጣኝ መሳይ በቶሎ መላ ሊዘይዱለት ይገባል። በተቃራኒው ግብ ለማስቆጠር ብዙ ስለማይቸገር ከሚገኝበት አስጊ ቦታ ለመሸሽ እና በጨዋታዎች ላይ ያለውን ተፅዕኖ በውጤት ለማሳጀብ ይህንን ክፍል በአጠቃላይ ውቅር አልያም ግለሰባዊ ለውጥ ማስተካከል አለባቸው።

\"\"

በአሠልጣኝ ፋሲል ተካልኝ የሚመሩት መቻሎች በሰባት ተከታታይ ጨዋታዎች አንድም ሽንፈት ሳያስተናግዱ ቆይተው በ17ኛ የጨዋታ ሳምንት ውድድሩ እየተከናወነበት በሚገኘው ከተማ ክለብ አዳማ ተረተዋል። ይህ ውጤት ቀስ በቀስ ወደ ጥሩ መንገድ እየመጣ የነበረውን የቡድን ውህደት የማያጠለሽ ከሆነ የነገውን ጨዋታ በአንፃራዊነት ከበድ ላሉት ለቀጣዮቹ ሁለት የፋሲል እና መድን ጨዋታዎች መንደርደሪያ ሊጠቀምበት ይችላል። እርግጥ መቻል ወሳኝ ተጫዋቹ ፍፁም ዓለሙን በከባድ ጉዳት ምክንያት ማጣቱ በነገው ጨዋታ ላይ ተፅኖ እንደሚፈጥርበት ቢታመንም ምናልባት አሠልጣኙ የፍፁም አይነት ባህሪ ያላቸው ሌሎች ተጫዋቾች ስላሉዋቸው ክፍተቱን ሊሞሉት ይችላሉ።

መቻል በነገው ጨዋታ የግብ ዘቡ ዳግም ተፈራ እና ፍፁም ዓለሙን ሲያጣ የተከላካይ አማካዩ ተስፋዬ አለባቸውም የመግባቱ ነገር አጠራጣሪ ነው ተብሏል።

ሁለቱ ቡድኖች ከዚህ ቀደም ለ17 ጊዜያት የተገናኙ ሲሆን ዕኩል አምስት አምስት ጨዋታዎችን በድል ተወጥተው
በቀሪዎቹ 7 ጨዋታዎች ደግሞ ነጥብ ተጋርተዋል።

የምሽቱ ጨዋታን ጨዋታ ባህሩ ተካ በመሀል አጋፋሪነት፣ አንጋፋው ካሳሁን ፍፁም እና ሀብተወልድ ካሳ በረዳት ዳኝነት እንዲሁም ሶሬሳ ካሚል በበኩሉ አራተኛ ዳኛ ሆነው በጋራ ይመሩታል።