ሪፖርት | ኢትዮጵያ መድን በለገጣፎ ላይ የጎል ናዳ አዝንቧል

ኢትዮጵያ መድን ለገጣፎ ለገዳዲን 7-1 በመርታት ከመሪው ጋር ያለውን ልዩነት ወደ ሦስት ቀንሷል።

\"\"

ኢትዮጵያ መድን ከአርባምንጩ ጨዋታ አንፃር በአንድ ተጫዋች ላይ ብቻ ለውጥ አድርጓል። በለውጡም ሀቢብ መሐመድን በቴዎድሮስ በቀለ ሲተኩ ለገጣፎዎች በበኩላቸው በቅጣት በሌለው ኮፊ ሜንሳህን እና ተስፋዬ ነጋሽን ፣ በሚካኤል ጆጂ እና ተስፋዬ በቀለ ለውጠዋል።

መድኖች ጨዋታውን በራሳቸው ቁጥጥር ስር በማድረግ መሐል ሜዳው በዋናነት ተጠቅመው በሁለቱ የመስመር አጥቂዎቻቸው ብሩክ እና ሐቢብ አማካኝነት አጋጣሚዎችን ለመፍጠር የሔዱበት መንገድ ደቂቃው ብዙም ሳይጋመስ ነበር ከጎል ጋር ያገናኛቸው። 11ኛው ደቂቃ ላይ መነሻዋ ከመሐል ክፍሉ አድርጋ የደረሰችውን ኳስ ብሩክ ሙሉጌታ በቀኝ የለገጣፎ የሜዳ ክፍል ለሚገኘው ሐቢብ ሰጥቶት ተጫዋቹም አስቆጥሯት በጊዜ ቡድኑን መሪ አድርጓል። የኋላ ቅብብሎችን በማብዛታቸው በጨዋታው ተፅዕኖ ለመፍጠር የተቸገሩት ለገጣፎዎች በተደጋጋሚ የሚሰሩት ስህተት ለመድኖች ምቹነት የፈጠረላቸው ሆኗል። በቁጥር በዛ ብሎ መሐል ሜዳ ላይ ይደረጉ ከነበሩ ንክኪዎች የብሩክ እና ሐቢብን ፍጥነት ለመጠቀም የመስመር አጨዋወት ላይ ይበልጥ ትኩረታቸውን የቀጠሉት መድኖች በሲሞን ፒተር ካደረጉት ተጨማሪ ሙከራ በኋላ ሁለተኛ ጎልን ወደ ካዝናቸው አስገብተዋል።

\"\"

22ኛው ደቂቃ ላይ ከአማካዩ ጋብሬል አህመድ እግር ስር ባሰሩ ዑመር የነጠቃትን ኳስ ለሲሞን ፒተር አቀብሎት አጥቂው የመጀመሪያ ጎል ወደ ተቆጠረችበት አቅጣጫ ያመቻቸለትን ብሩክ ሙሉጌታ ከመረቡ ጋር ደባልቋታል። በስህተት የተሞላን አጋማሽ በአብዛኛው ያሳለፉት ለገጣፏዎች በተወሰነ መልኩ በማሊያዊው አጥቂ ሱለይማን ትራኦሬ አማካኝነት ወደ ጨዋታ ቅኝት ለመመለስ በተለይ የጨዋታው ደቂቃ ሊጠናቀቁ ሲቃረቡ አድርገው ተስተውሏል። 33ኛው ደቂቃ ላይ ቻላቸው መንበሩ መሐመድ አበራ ላይ ሳጥን ውስጥ ጥፋት መስራቱን ተከትሎ የተሰጠችውን የፍፁም ቅጣት ምት ትራኦሬ መቷት ወደ ላይ ሰዷታል አጥቂው ሁለተኛ አጋጣሚን ከግራ በኩል አግኝቶ ወደ ጎል ሲመታ ቴዎድሮስ በቀለ ከግቡ መስመር ላይ አውጥቶበታል። መደበኛው የአጋማሹ ደቂቃ ተጠናቆ በጭማሪ ደቂቃ መድኖች ፍቅሩ አለማየሁ ሳጥን ውስጥ መንካቱን ተከትሎ ያገኙትን የፍፁም ቅጣት ምት ሐቢብ ከማል መቷት ሚካኤል ጆጂ አድኗት በተደረገ ፈጣን መልሶ ማጥቃት ትራኦሬ ድንቅ አጋጣሚን ፈጥሮ አቡበከር ኑራ በጥሩ ቅልጥፍና መልሶበት አጋማሹ በ2ለ0 ውጤት ተገባዷል።

\"\"

ከዕረፍት ጨዋታው ሲመለስ ለገጣፎ ለገዳዲዎች ሜዳ ላይ የሚታይባቸው አለመረጋጋቶች ሐቢብን በኪቲካ ለውጠው የፊት መስመራቸውን ባሰሉት መድኖች አሁንም ብልጫ ተወስዶባቸዋል። የአማካይ ክፍላቸውን ለተጨማሪ ጎሎች ከመስመር አጥቂዎቻቸው ጋር አጣምረው ቀጥለውም ሦስተኛ ጎላቸውን አግኝተዋል። ፒተር ሲሞን ከዮናስ ገረመው ያገኛትን ኳስ ወደ ግብ ሞክሮ ግብ ጠባቂው ሚኪያስ ጆጂ ካዳነበት ሙከራ በኋላ ነበር ጎል ያገኙት በጥሩ የጨዋታ ፍሰት ቻላቸው መንበሩ በቀኝ የሜዳው ክፍል ሲያሻግር ሲሞን ፒተር በአግባቡ ተጠቅሞ አስቆጥሯታል። ራሱ ሲሞን ከሁለት ደቂቃዎች መልስ ኪቲካ ጀማ ከጋብሬል ነጥቆ የሰጠውን ባሲሩ ዑመር በተከላካዮች መሐል አሾልኮ ሰጥቶት ኡጋንዳዊው አጥቂ ለራሱ ሁለተኛ ለቡድኑ አራተኛ ጎል አድርጓታል።

\"\"

ጥቂት የማጥቃት ተሳትፎን በተለይ ትራኦሬን ማዕከል ባደረገ መልኩ ለገጣፎዎች ለመንቀሳቀስ ቢሞክሩም የኋላ መስመራቸው በአግባቡ አለመሸፈናቸው ለመድኖች ተጨማሪ ጎሎችን እንዲያገኙ ሆኗል። ከመስመር መነሻዋን አድርጋ መሐል ሜዳው ላይ የደረሰችን ኳስ ሀብታሙ ሸዋለም ወደ ሳጥን ሲያሻማ የግብ ጠባቂው ሚኪያስ ጆጂ የጊዜ አጠባበቅ ስህተት ታክሎበት ኪቲካ ጀማ በግንባር አምስተኛ ጎልን ከመረብ አገናኝቷል። ጨዋታው ሊጠናቀቅ አንድ ደቂቃ ሲቀረው ኪቲካ ከግራ ወደ ውስጥ የላካትን ኳስ ያሬድ አመቻችቶለት ወጣቱ አጥቂ ወገኔ ገዛኸኝ ወደ ጎልነት ቀይሯት ስድስተኛ ጎል ሆናለች። የመድኖችን ጥቃት መመከት ፍፁም የከበዳቸው ለገጣፎዎች በኪቲካ ጀማ ሰባተኛ ጎል ሊያስተናግዱ ተገደዋል። ጨዋታው ሊጠናቀቅ የጭማሪ ሽርፍራፊ ሰከንድ ሲቀር በፍፁም ቅጣት ምት ካርሎስ ዳምጠው የማስተዛዘኛ ብቸኛ ጎልን ለለገጣፎ አስቆጥሮ በ7ለ1 አስገራሚ የመድኖች ድል አድራጊነት ተቋጭቷል።

\"\"

ከጨዋታው መጠናቀቅ በኋላ የለገጣፎው አሰልጣኝ ዘማርያም ወልደጊዮርጊስ በአጠቃላይ በስነ ልቦናው በኩል ሞኝ ስለነበርን ተበልጠን ተሸንፈናል ካሉ በኋላ ለተጋጣሚያችን እንደልብ እንዲጫወት በመፍቀዳችን ተሽለው መድኖች በመጫወታቸው ተበልጠን ተሸንፈናል ብለዋል። የአሰልጣኝ ገብረመድህን ኃይሌን አለመኖር ተከትሎ ቡድኑን በአሰልጣኝ የመራው ረዳት አሰልጣኙ ለይኩን ታደሰ (ዶ/ር) በእግርኳስ ከሚፈጠሩ ነገሮች አንዱ ዛሬ እንደተፈጠረ ጠቁሞ አሰልጣኝ ገብረመድህን ባይኖርም መንፈሱ አብሮን ስለ ነበር ውጤቱ እንደተገኘም ገልፆ የተገኙ ዕድሎችን በአግባቡ በመጠቀማቸው ውጤታማ መሆን እንዳስቻላቸው በንግግራቸው ገልፀዋል።