ሪፖርት | ተጠባቂው ጨዋታ ብርቱ ፉክክር ተደርጎበት አቻ ተጠናቋል

በጉጉት የተጠበቀው እና ለተመልካች ማራኪ ፉክክር ያስተናገደው የ26ኛ ሳምንት ተስተካካዩ የቅዱስ ጊዮርጊስ እና ባህርዳር ከተማ ጨዋታ 2-2 ተጠናቋል።

በተስተካካይ መርሐግብር በይደር ተይዞ የነበረው የ26ኛው ሳምንት ተጠባቂ ጨዋታ 10:00 ላይ ሲጀመር ፈረሠኞቹ በ27ኛው ሳምንት ለገጣፎ ለገዳዲን 2-1 ሲያሸንፉ ከተጠቀሙት አሰላለፍ ግብ ጠባቂውን ቻርለስ ሉክዋጎን በባህሩ ነጋሽ ፍሪምፖንግ ሜንሱን ደግሞ በአማኑኤል ተርፉ ተክተው በማስገባት ሲቀርቡ የጣና ሞገዶቹ በበኩላቸው በተመሳሳይ ሳምንት መቻልን 3-2 ከረታው አሰላለፋቸው ፉዓድ ፈረጃን አስወጥተው ቻርለስ ሪባኑን በማስገባት ጨዋታውን ጀምረዋል።

\"\"

ሁለቱም ቡድኖች የመረጡትን ጥንቃቄ የተሞላበት አጨዋወት እያስመለከተን የጀመረው ጨዋታ 14ኛው ደቂቃ ላይ በቅዱስ ጊዮርጊሶች አማካኝነት ግብ ተቆጥሮበታል። ቢንያም በላይ በቀኝ መስመር ከእስማኤል ኦሮ አጎሮ ጋር ተቀባብሎ ያሻማውን ኳስ ያገኘው ቸርነት ጉግሣ በግሩም ሁኔታ በግንባሩ በመግጨት ግብ አድርጎታል። በአንድ ደቂቃ ልዩነትም ቢንያም በላይ በድጋሚ በውጪ እግሩ በመምታት በድንቅ ዕይታ ያሻገረለትን ኳስ ያገኘው ቸርነት ጉግሣ ያደረገውን ሙከራ ግብ ጠባቂው ፋሲል ገብረሚካኤል መልሶበታል።

ግብ ከተቆጠረባቸው በኋላ የአቻነት ግብ ለማስቆጠር ተጭነው መጫታቸውን የቀጠሉት ባህር ዳሮች በአጋማሹ የመጀመሪያ የተሻለ ሙከራቸውን 20ኛው ደቂቃ ላይ አድርገዋል። የመሃል ተከላካዩ ፈቱዲን ጀማል ከረጅም ርቀት ያደረገው ሙከራ በግቡ የቀኝ ቋሚ በኩል ለጥቂት ወጥቶበታል። ሆኖም ወደፊት የሚያደርጉትን እንቅስቃሴ በመደጋገምም 29ኛው ደቂቃ ላይ ግብ ለማስቆጠር ተቃርበው ነበር። የአብሥራ ተስፋዬ ከግራ መስመር ለማሻማት በሚመስል መልኩ ያሻገረው ኳስ መሬቱ ላይ በመንጠር ባልተጠበቀ መንገድ የግቡን አግዳሚ ገጭቶ ተመልሶበታል። በአንድ ደቂቃ ልዩነት ግን ጥረታቸው ተሳክቶ የአቻነት ግብ አግኝተዋል። ግቧንም ቻርለስ ሪባኑ ያቀበለውን ኳስ አለልኝ አዘነ በመጀመሪያ ንክኪው ከረጅም ርቀት በድንቅ ሁኔታ አስቆጥሮታል።

ጊዮርጊሶች ጨዋታውን መምራት እስኪጀምሩ ድረስ የነበራቸውን እንቅስቃሴ ግብ ከተቆጠረባቸው በኋላ ለማሳየት መቸገራቸውን ሲቀጥሉ ከራሳቸው የሜዳ ክፍል ላይ የሚደረገው ፍልሚያ ወደ ተጋጣሚ የግብ ክልል በተደራጀ መልኩ እንዳይደርሱ ሲያስቸግራቸው ተስተውሏል። ሆኖም ጨዋታው ወደ ዕረፍት ሊያመራ ሴኮንዶች ሲቀሩ 45+3\’ ላይ ፍራኦል መንግሥቱ ከቀኝ መስመር ያሻገረው ኳስ ሳይታሰብ መረቡ ላይ አርፎ የጣና ሞገዶቹ አጋማሹን መርተው መጨረስ ችለዋል።

ከዕረፍት መልስ ጨዋታው በተለይም በቅዱስ ጊዮርጊሶች በኩል በመጠኑ ተሻሽሎ ሲቀጥል ሀይደር ሸረፋን አስወጥተው ጋቾች ፓኖምን በማስገባት መሃል ሜዳው ላይ የተወሰደባቸውን ብልጫ በማስመለስ እንደ መጀመሪያው አጋማሽ ሁሉ በመጀመሪያዎቹ ደቂቃዎች ብልጫ መውሰድ ሲችሉ 49ኛው ደቂቃ ላይ የጠራ የግብ ዕድል ፈጥረው ነበር። ቸርነት ጉግሣ ከሱሌማን ሐሚድ ጋር ተቀባብሎ በሳጥኑ የግራ ክፍል ላይ በግሩም ሁኔታ ገፍቶ የወሰደውን ኳስ ከማቀበል አማራጭ ጋር ወደ ግብ ቢመታውም የኳሱ ኃይል የለሽነት ተጨምሮበት ግብ ጠባቂው ፋሲል ገብረሚካኤል ይዞበታል። ሆኖም በተደጋጋሚ ያደረጉት ጥረት ተሳክቶም 58ኛው ደቂቃ ላይ ግብ አስቆጥረዋል። ቢንያም በላይ ከሳጥኑ የቀኝ ከፍል ወደ ውስጥ የቀነሰውን ኳስ ያገኘው አቤል ያለው በጥሩ አጨራረስ መረቡ ላይ አሳርፎታል።

ግብ ከተቆጠረባቸው በኋላ አደም አባስን በፍጹም ጥላሁን ተክተው ያስገቡት የጣና ሞገዶች በአጋማሹ የመጀመሪያውን የግብ ዕድላቸውን 61ኛው ደቂቃ ላይ ሲፈጥሩ ፍራኦል መንግሥቱ ከረጅም ርቀት ከግራ መስመር ለማሻማት ያሻገረው ኳስ አቅጣጫ በመቀየር መሬቱ ላይ አርፎ ወደ ግብ ሲሄድ ግብ ጠባቂው ቻርለስ ሉክዋጎ አስወጥቶታል።

ማራኪ ፉክክር እየተደረገበት የቀጠለው ጨዋታ በኳስ ቁጥጥሩ ብልጫ ለመውሰድ ብርቱ ፍልሚያ ቢደረግበትም የግብ ዕድሎች ግን እየተቀዛቀዙ ሄደዋል። የባህርዳር ከተማው ፉዓድ ፈረጃ 84ኛው ደቂቃ ላይ ከቅጣት ምት 87ኛው ደቂቃ ላይ ደግሞ ማማዱ ሲዲቤ ከቀኝ መስመር ባሻገረለት ኳስ ያደረጋቸው ዒላማቸውን ያልጠበቁ ሙከራዎች ተጠቃሽ ነበሩ። ሆኖም ጨዋታው 2-2 ተጠናቋል። ውጤቱን ተከትሎም ፈረሠኞቹ በአምስት ነጥብ ልዩነት መምራታቸውን ቀጥለዋል።

ከጨዋታው በኋላ በተሰጡ አስተያየቶች ከገባባቸው በኋላ በትዕግስት መጫወታቸው ወደ ጨዋታው እንደመለሳቸው በማስረዳት የጀመሩት አሰልጣኝ ደግአረገ ይግዛው የልምድ ማነስ ወደ አቻ እንደመጣቸው አስረድተው ከጅምሩ አጥቅተው የመጫወት ዕቅድ እንደነበራቸው ገልፀው ከዕረፍት መልስ ማፈግፈግ ምርጫቸው ባይሆንም ጎል ያስተናገዱበት መንገድ የሚያስቆጭ እንደነበር አልሸሸጉም። አሰልጣኝ ዘሪሁን ሸንገታ በበኩላቸው ጨዋታው ጠንካራ መሆኑን አንስተው ከዕረፍት መልስ ባደረጓቸው ቅያሪዎች ተጨማሪ ግቦችን ማስቆጠር እንደነበረባቸው እንደሚያምኑ ጠቁመው ያላቸውን ጠንካራ ጎን ባሰቡት መንገድ አለመጠቀማቸውን አስረድተዋል።

\"\"