የዋልያዎቹ ተጋጣሚ በአቋም መፈተሻ ጨዋታ ነጥብ ተጋርታለች

በቀጣዩ ሳምንት ማክሰኞ ከኢትዮጵያ ጋር የአፍሪካ ዋንጫ ማጣሪያ የምድብ ጨዋታ ያላት ማላዊ በአቋም መለኪያ ጨዋታ አቻ ተለያይታለች።

በአይቮሪኮስት አስተናጋጅነት በሚከናወነው የዘንድሮ የአፍሪካ ዋንጫ ላይ ለመካፈል የምድብ ማጣሪያ ጨዋታዎችን እያደረገ የሚገኘው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ምንም እንኳን ወደ ውድድሩ ለማለፍ ያለው ዕድል እጅግ የጠበበ ቢሆንም የመጨረሻ ሁለት ጨዋታዎችን ለማድረግ ጊዜያዊ አሠልጣኞች መሾሙ ይታወቃል። ብሔራዊ ቡድኑ በቀጣዩ ሳምንት ላለበት ጨዋታ ዝግጅቱን እያደረገ የሚገኝ ሲሆን ተጋጣሚው ማላዊም ለጨዋታው ከፍ ያለ ትኩረት በመስጠት እየተሰናዳ ይገኛል።
\"\"
ያለፉትን ሦስት ሳምንታት በሳምንት ሦስት ቀናት በሀገር ቤት ተጫዋቾች ዝግጅቱን ሲሰራ የነበረው ቡድኑ ከትናንት በስትያ የመጨረሻ ተጫዋቾችን በመያዝ ጨዋታውን ወደሚያደርግበት ሞዛምቢክ ያመራ ሲሆን ትናንት ቀለል ያለ ልምምዱን ሰርቶ በዛሬው ዕለት የአቋም መፈተሻ ጨዋታ ከሞዛምቢክ አቻው ጋር አድርጓል።

በዝግ ስታዲየም በተከናወነው ፍልሚያ የፊታችን እሁድ ከሩዋንዳ ጋር የነጥብ ጨዋታ ያለበት የሞዛምቢክ ብሔራዊ ቡድን በሁለተኛው አጋማሽ ቀድሞ ግብ ቢያስቆጥርም ነበልባሎቹ ከደቂቃዎች በኋላ ግብ አስቆጥረው ጨዋታው በአቻ ውጤት ተፈፅሟል።
\"\"
ለኢትዮጵያው ጨዋታ ከተመረጡት 24 ተጫዋቾች ስድስት አዳዲስ ፊቶችን በስብስባቸው ያካተቱት አሠልጣኝ ፓትሪክ ማቤዲ በፖላና ሴሪና ሆቴል ማረፊያቸውን አድርገው በቀጣይ አምስት ቀናት መደበኛ ልምምዳቸውን ማፑቶ ላይ አድርገው ማክሰኞ ከኢትዮጵያ ጋር የሚጫወቱ ይሆናል።