ዋልያዎቹ በአቋም መፈተሻ ጨዋታ በአርባምንጭ ከተማ ተሸንፈዋል

በልምምድ የአቋም መፈተሻ ጨዋታ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን በአርባምንጭ ከተማ ተረቷል።

በአዳማ ሳይንስ እና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርስቲ ስታዲየም በተከናወነው ጨዋታ ላይ የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን ፕሬዝዳንት አቶ ኢሳይያስ ጂራ፣ ምክትል ፕሬዝዳንቱ ዳኛቸው ንግሩ (ዶ/ር) እና ዋና ሥራ-አስፈፃሚው አቶ ባህሩ ጥላሁን የተገኙ ሲሆን ብሔራዊ ቡድኑም ለ60 60 ደቂቃዎች ለሁለት ተከፍሎ የአቋም መፈተሻ ጨዋታውን አከናውኗል።

\"\"

በመጀመሪያው 60 ደቂቃ የቡድኑ ጊዜያዊ አሠልጣኝ ኢንስትራክተር ዳንኤል ባህሩ ነጋሽ፣ ረመዳን የሱፍ፣ ያሬድ ባየ፣ ሚሊዮን ሰለሞን፣ ሔኖን አዱኛ፣ አለልኝ አዘነ፣ ከነዓን ማርክነህ፣ አበባየሁ ሀጂሶ፣ ብሩክ ሙሉጌታ፣ አቤል ማሙሽ እና ቢኒያም በላይን አሰልፈዋል።


ብዙም ሳቢ እንቅስቃሴዎች ባልተደረገበት ጨዋታ ላይ ዋልያዎቹ በአንፃራዊነት ወደ ግብ በመድረሱ ረገድ የተሻሉ ነበሩ። በዚህም በ15ኛው ደቂቃ የመዓዘን ምትን መነሻ ባደረገ አጋጣሚ፣ በ22ኛው ደቂቃ ከነዓን ከርቀት ምት በሞከረው ኳስ፣ በ30ኛው ደቂቃ አቤል ከቢኒያም በተቀበለው እንዲሁም በ43ኛው ደቂቃ በተመሳሳይ ብሩክ ከቢኒያም በደረሰው እና በ50ኛው ደቂቃ ግብ ጠባቂው አቤል ማሞ ወደ ኋላ የተሰጠውን ኳስ ለማፅዳት በሚል ሲሞክር ብሩክ ደርሶት በሞከረው ኳስ የግብ ማግባት ሙከራዎችን አድርገዋል።


አርባምንጭ ከተማ በበኩሉ በ28ኛው ደቂቃ የመጀመሪያውን ጥቃት ሲሰነዝር ከዘጠኝ ደቂቃዎች በኋላም በላይ በተከላካዮች ስህተት ሌላ ሙከራ አድርጓል። የመጀመሪያው 60 ደቂቃ ክፍለ ጊዜ ሊጠናቀቅ ሦስት ደቂቃዎች ሲቀሩት አዞዎቹ ከተከላካይ ጀርባ ጥሩ ኳስ ልከው የተሻለ ቦታ ላይ የነበረው በላይ ገዛኸኝ ግብ አስቆጥሮ ቀዳሚው ጨዋታ 1ለ0 ተጠናቋል።

\"\"

በሁለተኛው 60 ደቂቃ ቀድመው ከተጫወቱት ተጫዋቾች መካከል የቀጠለው ብቸኛው ተጫዋች ያሬድ ባየ ሲሆን እሱም አካፋይ ደቂቃ ላይ በሚሊዮን ተቀይሯል። አሠልጣኙ ባደረጉት ለውጥ ሰዒድ ሀብታሙ፣ ፍራኦል መንግስቱ፣ አማኑኤል ተረፉ፣ ዓለምብርሃን ይግዛው፣ አማኑኤል ዮሐንስ፣ ወገኔ ገዛኸኝ፣ ሽመልስ በቀለ፣ ዱሬሳ ሹቢሳ፣ ሀብታሙ ታደሰ እና ዮሴፍ ታረቀኝ ወደ ሜዳ ገብተዋል።


በዚህ የጨዋታ ክፍለ ጊዜ በአንፃራዊነት (ከመከላከል አጨዋወት ውጪ) የተሻለ የነበረው ቡድኑ በመጀመሪያዎቹ 20 ደቂቃዎች ሦስት ጥሩ ጥሩ ዕድሎችን ፈጥሮ ነበር። በዚህም በቅድሚያ ዱሬሳ ከመስመር ያሻማውን ኳስ ሀብታሙ ሞክሮት ሲወጣበት ከሁለት ደቂቃዎች በኋላ ደግሞ በተመሳሳይ መስመር ፍራኦል ሌላ ጥብቅ ኳስ መትቶ በግብ ጠባቂ መክኖበታል። ዮሴፍም ሌላ ዕድል ከረጅም ርቀር በደረሰው ኳስ ፈጥሮ በተከላካዮች ተመልሶበታል።

በእጃቸው የገባውን ድል አሳልፈው ላለመስጠት የታተሩት አርባምንጮች ዘለግ ያለውን ደቂቃ ከኳስ ጀርባ ሆነው ቢጫወቱም በመጨረሻዎቹ ደቂቃዎች እጅግ ያለቀላቸው ሦስት ዕድሎችን ፈጥረው መሪነታቸውን ሊያሳድጉ ነበር። በዚህም በተከታታይ ከግብ ጠባቂ ጋር የተገናኙበትን ሁነት ፈጥረው የግብ ዘቡ ቢኒያም ሁለቱን ሲያመክን አንዱ ወደ ውጪ ወጥቷል።


ጨዋታው ሊገባደድ ደቂቃዎች ሲቀሩት ሀብታሙ ላይ ጥፋት ተሰረቶ ዋልያዎቹ የፍፁም ቅጣት ምት ቢያገኙም ዱሬሳ ሹቢሳ ዕድሉን ሳይጠቀምበት ቀርቷል። ጨዋታውም በአርባምንጭ ከተማ አንድ ለምንም አሸናፊነት ተጠናቋል።