በዋልያዎቹ ወቅታዊ ስብስብ ውስጥ ያልተካተቱ ተጫዋቾች ጉዳይ…

አሰልጣኝ ዳንኤል ገብረማሪያም በብሔራዊ ቡድን ዝርዝር ውስጥ ስላልተካተቱ ቁልፍ ተጫዋቾች ሀሳብ ሰጥተዋል።

\"\"

ሞዛምቢክ ላይ በአፍሪካ ዋንጫ ማጣሪያ ከማላዊ ጋር የምድብ ጨዋታ የሚጠብቀው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ዝግጅቱን አዳማ ከተማ ላይ እያደረገ ይገኛል። የዝግጅት ጊዜውን አስመልክቶም ዛሬ ከ09:00 ጀምሮ ዋና አሰልጣኝ ዳንኤል ገብረማሪያም እና የፌዴሬሽኑ ፅህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ባህሩ ጥላሁን መግለጫ በመስጠት ላይ ይገኛሉ። በዚሁ መግለጫ ላይ ቀዳሚውን ማብራሪያ የሰጡት ዋና አሰልጣኙ በወቅታዊው የብሔራዊ ቡድን ስብስብ ውስጥ ስላልተካተቱ ተጫዋቾች አስተያየት ሰጥተዋል። የአሰልጣኝ ቡድን አባላትን ከማዋቀር ጀምሮ 41 ተጫዋቾች በመለየት እና ወደ መጨረሻ ስብስብ በመቀነስ ጨዋታው ከሚከናወንባት ሞዛምቢክ ጋር ተመሳሳይ የአየር ሁኔታ ባላት አዳማ ሲዘጋጁ እንደቆዩ የተናገሩት ዋና አሰልጣኙ በስብስባቸው ሊያካትቷቸው ከሞከሩ ተጫዋቾች ጋር የነበራቸውን ግንኙነት አብራርተዋል።

በቅድሚያ ከዚህ ቀደም ከብሔራዊ ቡድን ራሱን ማግለሉን ያሳወቀው ጌታነህ ከበደን እንዳወያዩ የተናገሩት አሰልጣኙ ተጫዋቹ ጥሪያቸውን አክብሮ መገኘቱን አድንቀው ሆኖም ዝግጁ አለመሆኑን በመግለፁ በስብስባቸው አለመካተቱን አንስተዋል። በደቡብ አፍሪካ ከሚገኘው አቡበከር ናስር ጋር ባደረጉት ውይይት ደግሞ ተጫዋቹ ከቁርጭምጭሚት ጉዳት የማገገሚያ ሥራ ላይ በመሆኑ ለጨዋታው አለመድረሱን ጠቁመዋል። በተመሳሳይ ዳዋ ሆቴሳ ሙሉ ለሙሉ ከጉዳት ነፃ ባለመሆኑ እንዲሁም ወደ ልምምድ የተመለሰው አማኑኤል ገብረሚካኤልም የጨዋታ ብቁነት ላይ ባለመድረሱ ከማላዊው ጨዋታ ውጪ መሆኑን አስረድተዋል። አሰልጣኙ ከዚሁ ማብራሪያቸው ጋር አያይዘው ተጫዋቾችን በዘለቄታዊነት ለመጠቀም ያሉበትን የጉዳት ደረጃ ከግምት ማስገባት አስፈላጊ እንደነበር አስረድተዋል።

\"\"