ከማላዊው ጨዋታ በፊት መግለጫ ተሰጥቷል

በኢንስትራክተር ዳንኤል ገብረማሪያም እና በአቶ ባህሩ ጥላሁን መግለጫ የተነሱ ዋና ዋና ሀሳቦችን እንደሚከተለው አቅርበናል።

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ከአይቮሪኮስቱ የአፍሪካ ዋንጫ ውጪ ቢሆንም ቀሪ የምድብ ማጣሪያ ጨዋታዎች ይጠብቁታል። በቅድሚያ ሞዛምቢክ ላይ ከማላዊ ጋር የሚያደርገው አምስተኛ የምድብ ጨዋታን መቃረብ ተከትሎም በአዳማ ዝግጅቱን ቀጥሏል። ዛሬ 09:00 ላይ ይህንን አስመልክቶ ቡድኑን በጊዜያዊ አሰልጣኝነት የያዙት ኢንስትራክተር ዳንኤል ገብረማርያም እና የፌዴሬሽኑ ፅህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ባህሩ ጥላሁን መግለጫ ሰጥተዋል። በዚህ መግለጫ ላይ በቡድኑ ስብስብ ውስጥ ስላልተካተቱ ተጫዋቾች የተነሱ ሀሳቦችን ቀደም ብለን ያስነበብን ሲሆን አሁን ደግሞ በቀሪው የመግለጫው ክፍል ትኩረት የሳቡ ነጥቦችን አቅርበናል።
\"\"
ኢንስትራክተት ዳንኤል ከምክትል አሰልጣኞች ምርጫ ጋር በተያያዘ ለቀረበላቸው ጥያቄ ምክትላቸው አሰልጣኝ ደግአረገ ይግዛው ዘንድሮው በባህር ዳር ከተማ ካሳዩት አፈፃፀም እና ከሚከተሉት የአጨዋወት ሂደት አንፃር እንዲሁም የግብ ጠባቂዎች አሰልጣኝ ውብሸት ደሳለኝም ካላቸው ልምድ አንፃር መመረጣቸውን ተናግረዋል። የተጨዋቾች ምርጫን አስመልክተውም በወቅታዊ አቋም ደከም ያሉትን ከአጨዋወት አንፃር በማየት ለቀጣይ ዓመታት በሚያገለግሉ ወጣት ተጫዋቾች መተካታቸው እነርሱም በየዲፓርትመንቱ ካሉ ልምድ ካላቸው ተጫዋቾች እንደሚማሩ ያላቸውን ዕምነት ገልፀው አሁን ያልተካተቱ ሌሎች ተጫዋቾች በቀጣይ ወቅታዊ አቋማቸው ሲስተካከል እንደሚጠሩም ጠቁመዋል።

በመቀጠል ከሚከተሉት አጨዋወት አንፃር ያላቸውን ምልከታ ሲያስቀምጡ ከሜዳው በቶሎ በመውጣት በተጋጣሚ ሜዳ ላይ ተፅዕኖ የሚፈጥር ቡድን መስራት እንደሚያስቡ የተናገሩት አሰልጣኙ \”በተቻለ መጠን በራሱ ሜዳ ላይ መዘግየትን የማያስብ ቡድን ለመስራት እናስባለን\” ብለዋል።

አቶ ባህሩ ጥላሁን በበኩላቸው የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን የማላዊውን ጨዋታ በሞዛምቢክ ለማስተናገድ የወሰነበትን ሂደት በሰፊው አብራርተዋል። በዚህም በምስራቅ አፍሪካ ደረጃውን የጠበቀ ስታድየም ካላቸው ሀገራት ውስጥ ሱዳን በወቅታዊ የፀጥታ ችግር ታንዛንያ ደግሞ የያንግ አፍሪካ የኮንፌዴሬሽን ዋንጫ ጨዋታ እና የብሩንዲ ብሔራዊ ቡድንን ጨዋታ የምታስተናግድ በመሆኗ ተመራጭ አለመሆናቸውን አብራርተዋል። በተጨማሪም ደቡብ አፍሪካ በዋጋ መወደድ ምክንያት ተመራጭ ባለመሆኗ በካፍ ክለብ ላይሰንሲግ ኃላፊ መሐመድ ሲዳት ጠቋሚነት የፌዴሬሽኑ ምርጫ ሞዛምቢክ ላይ ማረፉን ገልፀዋል። ከሞዛምቢክ እግርኳስ ፌዴሬሽን ጋር በተደረገው ግንኙነት የተጠየቀውን ዋጋ ወደ 8ሺህ ዶላር እንደቀደነሱ ያነሱት ዋና ፀሀፊው ይህም ONEX ከተሰኘው አወራራጅ ተቋም ጋር ባለው የማስታወቂያ ስምምንት እንደሚሸፈን ገልፀው የቀረው አስተዳደራዊ ወጪ ግን በኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን እንደሚሸፈን አስረድተዋል።
\"\"
በሌላ ጥያቄ ስለአሰልጣኞቹ የሥራ ጊዜ ተጠይቀው ሲመልሱ አሁን ያሉት አሰልጣኞች እስከ ግብፁ የአፍሪካ ዋንጫ ጨዋታ ድረስ ቡድኑን ይዘው እንደሚቀጥሉ ሆኖም ከዚያ በኋላ ፌዴሬሽኑ አዲስ አሰልጣኝ ለመሾም ፍላጎት እንዳለው እስከዚያው ግን በቴክኒክ ዳይሪክተሩ የዋና አሰልጣኝነት ክፍተቱን ለመሙላት መወስኑን ተናግረዋል።