የማላዊ አሠልጣኝ እና አምበል ከዛሬው ጨዋታ በፊት ምን አሉ?

አመሻሽ 11 ሰዓት ኢትዮጵያ እና ማላዊ ከሚያደርጉት ጨዋታ በፊት የቡድኑ አሠልጣኝ እና አምበል የግድ ማሸነፍ ስላለባቸው ጨዋታ ሀሳብ ሰጥተዋል።

ዘንድሮ በአይቮሪኮስት አስተናጋጅነት በሚከናወነው የአፍሪካ ዋንጫ ላይ ለማለፍ የአህጉራችን ብሔራዊ ቡድኖች የምድብ ማጣሪያ ጨዋታዎችን እያደረጉ ወደ ውድድሩ የሚወስዳቸውን ትኬት እየቆረጡ የሚገኝ ሲሆን በምድብ 4 ከግብፅ፣ ማላዊ እና ጊኒ ጋር የተደለደለው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን በበኩሉ ቀሪ 2 ጨዋታዎች እያሉት የማለፍ ዕድሉ ሙሉ ለሙሉ መምከኑ ይታወቃል። ቡድኑ ማለፍ ባይችልም ከሚቀሩት ሁለት የምድብ ጨዋታዎች መካከል አንዱን ዛሬ ሞዛምቢክ ማፑቶ ላይ ያከናውናል።
\"\"
ለጨዋታው ከፍ ያለ ትኩረት በመስጠት ዝግጅቷል እየሰራች የምትገኘው ተጋጣሚው ማላዊ በሀገር ቤትም እንዲሁም ጨዋታው በሚደረግበት ሞዛምቢክ ልምምዷን ሰርታ ጨዋታውን እየተጠባበቀች ትገኛለች። ከቡድኑ የመጨረሻ ልምምድ በኋላ ደግሞ አምበሉ ጆን ባንዳ ከጨዋታው በፊት ተከታዩን አስተያየት ሰጥቷል።

\”ሞዛምቢክ የሚገኘው ቡድን የሚጠበቅበትን ስራ ለመስራት ዝግጁ ነው። ጥሩ ነገር የሚያሳዩ በርካታ ወጣት ተጫዋቾች አሉን። እዚህ ደረጃ ላይ እንድንገኝ ያደረጉንን ያለፉ ስህተቶች ደግመን መስራት የለብንም።

\”ምን እንደሚጠበቅብን እናውቃለን። የዛሬውን ጨዋታ ማሸነፍ ብቻ የማለፍ ተስፋችንን ያሰፋልናል። ወደ አፍሪካ ዋንጫው መመለስ አለብን። ለዚህ የዛሬው ጨዋታ ወሳኝ ቢሆንም ጫና ውስጥ ግን አንገኝም። ስራችን ኳስ መጫወት ስለሆነ አንደናገጥም። እርግጥ በቡድኑ ውስጥ አንዳንዶቹ አዳዲስ ተጫዋቾች ናቸው ፤ ግን ልምድ ያለን ተጫዋቾች ነገሮችን እንዲለምዱ እገዛ እናደርጋለን።\”

የቡድኑ ጊዜያዊ አሠልጣኝ ፓትሪክ ማቤዲ በበኩላቸው \”ለጨዋታው በሚገባ ተዘጋጅተናል። ለጉዟችን ወሳኝ ለሆነው ለዛሬው ጨዋታም ትኩረት ሰጥተናል። በዚህም ከጨዋታው ማክሲመም ነጥብ ለማግኘትም እንጥራለን።\” ካሉ በኋላ ስለተጋጣሚያቸው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ተከታዩን አጠር ያለ ሀሳብ ገልፀው ሀሳባቸውን አገባደዋል።
\"\"
\”የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ጥሩ ቡድን ነው። በመጀመሪያው ጨዋታ ብናሸንፈውም ጥሩ ተጫውቷል። በቡድኑ ውስጥ ጥሩ ተጫዋቾችም አሉ። ስለዚህ በአቀራረባችን ላይ ጥንቃቄ ማድረግ አለብን።\” ብለዋል።

ከኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ጋር እኩል 3 ነጥቦች ያሉት የማላዊ ብሔራዊ ቡድን በእርስ በርስ ግንኙነት ዋልያዎቹን በልጦ በምድቡ 3ኛ ደረጃ ላይ የተቀመጠ ሲሆን የዛሬውን እንዲሁም በመስከረም ወር ከጊኒ ጋር የሚደረገውን ጨዋታ የሚያሸንፍ ከሆነ ግብፅን ተከትሎ ወደ አፍሪካ ዋንጫው የማለፍ ዕድል አለው።