መረጃዎች| 108ኛ የጨዋታ ቀን

የቤትኪንግ ኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ የ29ኛ ሳምንት ተጠባቂ ጨዋታዎችን የተመለከቱ መረጃዎች እንደሚከተለው አቅርበናል።

አርባምንጭ ከተማ ከ ድሬዳዋ ከተማ

የሀያ ዘጠነኛው ሳምንት መክፈቻ የሆነው ተጠባቂ ጨዋታን የተመለከቱ መረጃዎች እንደሚከተለው አቅርበናል።

የአሰልጣኝ ለውጥ ካደረጉ በኋላ በሊጉ የመትረፍ ተስፋቸው ያለመለሙት አዞዎቹ ከለውጡ በኋላ ባደረጓቸው ሦስት ጨዋታዎች ማግኘት ከሚገባቸው ዘጠኝ ነጥቦች ሰባቱን አሳክተዋል። በተጠቀሱት ጨዋታዎችም ሰባት ግቦች አስቆጥረዋል ፤ ይህ ማለት በአንድ ጨዋታ በአማካይ 2.3 ግቦች ተጋጣሚ ላይ አስቆጥረዋል ማለት ነው። ኢትዮ ኤሌክትሪክ፣ ሲዳማ ቡና እና ለገጣፎ ለገዳዲ በገጠሙባቸው ሦስቱም ጨዋታዎች ሦስት ግቦች ብቻ ተቆጥሮባቸዋል።

ቁጥሮቹ እንደሚመሰክሩት አዞዎቹ በጥሩ ወቅታዊ አቋም ላይ ይገኛሉ ፤ በተለይም የግብ ማስቆጠር አቅማቸው በዚህ መጠን መሻሻሉ በሊጉ ውስጥ የመቆየት ዕድላቸው አስፍቶላቸዋል። የነገው ዕለት ተጋጣምያቸው ድሬዳዋ በተመሳሳይ ላለመውረድ በሚደረግ ትግል ውስጥ መኖሩ እና ልዩነቱ የሦስት ነጥቦች ብቻ መሆኑ ሲታይ ግን በነገው ጨዋታ የሚገጥማቸው ፈተና ቀላል እንደማይሆን ለመገመት አያዳግትም። ሆኖም ቡድኑ ያለፉትን ሦስት ጨዋታዎች ምርጥ ብቃት የሚያስቀጥል ከሆነ ጠንካራ ተጋጣሚ እንደሚሆን እሙን ነው።
\"\"
በመጨረሻዎቹ ሁለት ጨዋታዎች በአዳማ ከተማ እና ወላይታ ድቻ ሽንፈት ገጥሟቸው ከነበሩበት ደረጃ ለመንሸራተት የተገደዱት ብርቱካናማዎቹ በሊጉ ለመቆየት ከዚህ ጨዋታ ነጥብ ይዞ መውጣት ግድ ይላቸዋል። ድሬዳዋዎች ከነገው ተጋጣሚያቸው አርባምንጭ በሦስት ነጥቦች ብቻ ከፍ ብለው አስራ ሁለተኛ ደረጃ ላይ ሆነው ወደዚህ ጨዋታ የሚገቡ ሲሆን በነገው ጨዋታ የተከላካይ ክፍላቸው አሻሽለው ጥሩ የነበረው እና ከተከታታይ አስራ አምስት ጨዋታዎች በአንዱ ብቻ ግብ ሳያስቆጥር የወጣው የአጥቂ ክፍላቸውን ዳግም አጠናቅረው የማይቀርቡ ከሆነ ግን አደጋ ውስጥ መግባታቸው አይቀርም። ምክንያቱም ጠንካራው ቅዱስ ጊዮርጊስ ከሚገጥሙበት የሊጉ መገባደጃ ጨዋታ በፊት ቢያንስ በነጥቦች ከፍ ብለው መገኘት ስላለሚገባቸው የነገው ጨዋታ ወሳኝ ነው።

በተለይም ከአሰልጣኝ ለውጥ በኋላ ተሻሽሎ የነበረውና በመጨረሻዎቹ ሁለት ጨዋታዎች አምስት ግቦች የተቆጠረበት የቡድን የተከላካይ ክፍል ጠንክሮ መቅረብ ይኖርበታል ፤ ምክንያቱም የተጋጣሚው የማጥቃት ክፍል በጥሩ ወቅታዊ አቋም ላይ የሚገኝ እና ግቦች ለማስቆጠር የማይቸገር ቡድን ስለሆነ።

በድሬዳዋ በኩል ያሬድ ታደሰ እና ያሲን ጀማል በጉዳት ምክንያት ከነገው ጨዋታ ውጪ ናቸው። በአርባምንጭ በኩልም የአካሉ አትሞ መሰለፍ አጠራጣሪ ነው ፤ ተመስገን ደረስ ግን ከጉዳት አገግሟል።

ወላይታ ድቻ ከ ወልቂጤ ከተማ

በተመሳሳይ ሁለት በሦስት ነጥብ ብቻ የሚራራቁ ቡድኖችን የሚያገናኘው ተጠባቂውን ጨዋታ የተመለከቱ መረጃዎች እንደሚከተለው አሰናድተናል።

በመጨረሻው ሳምንት ድሬዳዋ ከተማን ሦስት ለአንድ አሸንፈው ደረጃቸው ማሻሻል የቻሉት ወላይታ ድቻዎች አሁንም ከአደገኛው ወረዳ አልራቁም። ወጥነት የሌለው ብቃት በማሳየት የሚገኘው ክለቡ ከመጨረሻው ጨዋታ በፊት ካደረጋቸው አምስት ጨዋታዎች ሦስት ነጥቦች ብቻ በማግኘቱ አሁን ላለበት የአደጋ ወረዳ ዳርጎታል። በነገው ጨዋታም የጀመረው የድል መንገድ ማስቀጠል ካልቻለ ይባሱኑ ወደ ግርጌ ስለሚያወርደው በዚህ ጨዋታ ይበልጥ ጠንካራ መሆን ይጠበቅበታል።

አራት ግቦች አስቆጥረው በተመሳሳይ አራት ግቦች ካስተናገዱበት የመጨረሻ ሁለት ጨዋታዎች ውጭ ለወትሮ ጠጣር በሆነ አቀራረብ የሚታወቁት የጦና ንቦች በመጨረሻዎቹ ሳምንታት የተወሰነ የአጨዋወት ለውጥ እንዳደረጉ ከእንቅቃሴያቸው በተጨማሪ በቁጥሮች መረዳት ይቻላል። የነገው ጨዋታም ወሳኝ እንደመሆኑ በተወሰነ መልኩ ክፍት የሆነ አጨዋወት መርጠው የሚገቡበት ዕድል አለ ተብሎ ይገመታል።
\"\"
በብዙ የሜዳ ውጭ ችግሮች ተተብትበው ጨዋታዎቻቸው በማድረግ የሚገኙት ሰራተኞቹ በግብ ክፍያ ተበልጠው በወራጅ ቀጠናው ለመቀመጥ ተገደዋል። መጨረሻ ካረጓቸው አምስት ጨዋታዎች ኢትዮጵያ መድንን አሸንፈው ፤ ከሀድያ ሆሳዕና እና ፋሲል ከነማ ጋር አቻ ወጥተው በተቀሩት ሁለት ጨዋታዎች ደግሞ ሽንፈት ገጥሟቸው በተጠቀሱት ጨዋታዎች አምስት ነጥቦች(በአማካይ በአንድ ጨዋታ አንድ ነጥብ) መሰብሰብ የቻሉት ወልቂጤዎች በወሳኝ ምዕራፍ ላይ ይገኛሉ።

ወልቂጤዎች ለማሸነፍ በተቸገሩበት ጨዋታዎች ጭምር ግቦች ለማስቆጠር የማይቸገር ጌታነህ ከበደ የያዘ የአጥቂ ክፍል ነበራቸው። በመጨረሻዎቹ አምስት ጨዋታዎች ግን ሦስት ግቦች ማለትም በአማካይ በጨዋታ 0.6 ግቦች ብቻ ነው ማስቆጠር የቻሉት። በነገው ጨዋታም ይህንን ወቅታዊ ግብ የማስቆጠር ድክመታችው ማስተካከል ይጠበቅባቸዋል። ወልቂጤዎች ምንም እንኳ በወራጅ ቀጠና ውስጥ ቢገኙም ባለፉት አምስት ጨዋታዎች ጠንካራ የሚባል የተከላካይ ክፍል ነበራቸው። በተጠቀሱት ጨዋታዎችም በሦስቱ ግባቸውን ሳያስደፍሩ ወጥተዋል፤ የተቆጠሩባቸው ግቦችም አራት ብቻ ናቸው። በነገው ጨዋታ ይህንን ጠንካራ ጎናቸው ማስቀጠልም ተቀዳሚ ተግባራቸው መሆን ይጠበቅበታል።

ወልቂጤዎች አፈወርቅ ኃይሉ እና አዳነን በጉዳት ምክንያት አያሰልፉም። በወላይታ ድቻ በኩልም በረከት ወልደ ዮሐንስ ከጉዳት ሲመለስ አንተነህ ጉግሳ፣ በኃይሉ ተሻገር እና ሳሙኤል ተስፋዬ በጉዳት ምክንያት አይሰለፉም።