የአሠልጣኞች አስተያየት | አርባምንጭ ከተማ 0-1 ድሬዳዋ ከተማ

\”ቀጣይ ዓመትም ከተማውን እና ህዝቡን የሚመጥን ቡድን ይዘን እናቀርባለን የሚል እምነት አለኝ\” አሰልጣኝ አስራት አባተ


\”በሌሎች ላይ መንጠልጠላችን አስቸጋሪ ቢሆንም የምንችለውን ሁሉ እስከመጨረሻው እናደርጋለን\” አሰልጣኝ በረከት ደሙ

አሰልጣኝ አስራት አባተ – ድሬዳዋ ከተማ

ስለ ጨዋታው…

እንደ ጠበቅነው ጠንካራ ጨዋታ ነው የገጠመን። አርባምንጭ ጠንካራ ቡድን ነው ፤ ደረጃቸው እዚህ ቢገኝም በስብስብ አኳያ ጠንካራ ቡድን ነው። እኛም በዕረፍቱ ጊዜ ጠንክረን ሰርተናል ፤ ከዚህ በፊት የተሸነፍናቸው ጨዋታዎችም ራሳችን በቀላሉ አሳልፈን ነበር የሰጠናቸው። ዛሬ ግን እነዛ ነገሮች አርመናል ፤ ውጤቱም ይገባናል።

\"\"

ጨዋታው ስለነበረው ውጥረት…

ከጨዋታው በፊት ከእኛ ጋር የሦስት ነጥብ ልዩነት ነበር ፤ ይሄ ጨዋታ ብንሸነፍ ግን ወራጅ ቀጠና ውስጥ እንገኝ ነበር ፤ ይሄም ከጨዋታው በፊት ለእኛ አይመጥነንም ብለን ነበር። ለዛም ዝግጁ ነበርን ፤ እንደምታየው ደጋፊያችም ብዙ ኪሎሜትሮች አቋርጦ መጥቷል። ለዛም ምላሽ ሰጥተናል። ከክቡር ከንቲባችን ጀምሮ የክለቡ የበላይ አመራር በጭንቅ ወቅት ነው ያሉት እና እንኳን ደስ አላቹህ ማለት እፈልጋለሁ።

ድሬዳዋ ከተማ ባለፉት ዓመታት በመጨረሻው ቀን ነበር መትረፉን ስያረጋግጥ የነበረው ፤ ዘንድሮ በአንድ ሳምንት ቀደም ብሎ አረጋግጧል። ቀጣይስ…

ዘንድሮ ያንን ለማለት የምያስችል ደረጃ ላይ አልነበርንም። ቀድመን ደረጃ ውስጥ መግባት የምንችልበት ዕድሎች ነበሩ። የራሳችን የሆኑ ድክመቶች አሉብን ፤ ግን ያሻሻልናቸው ነገሮችም አሉ። ግን ያንን ማስቀጠል አልቻልም ነበር። ዛሬ ግን አሳክተነዋል ፤ ቀጣይ ዓመትም ከተማውን እና ህዝቡን የሚመጥን ቡድን ይዘን እናቀርባለን የሚል እምነት አለኝ።

አሰልጣኝ በረከት ደሙ – አርባምንጭ ከተማ

ስለ ጨዋታው…

ጨዋታው ወሳኝነቱ ግልጽ ነው የሚታወቅ ነው። እኛም በዛ ልክ ተዘጋጅተን መጥተናል። ከፕሮግራም አወጣጦች ጋር ብዙም ግልፅ ባይሆንልንም የተሰጠን ሜዳ ለሁለታችንም ስለሆነ በተዘጋጀነው ልክ ለመጫወት ሞክረናል ግን ያው ጫናው እኛ ላይ ትንሽ ከፍ ይል ነበር። ከዚህ ቀጠና ለመውጣት እጅግ በጣም ጓጉተን ነበር። ሜዳ ውስጥ ገብተን አቅማችንን እንዳናወጣ ጉጉት በተወሰነ መልኩ ይዞብናል። ሆኖም ግን የጨዋታው አጠቃላይ ሂደት ውጤቱን ይወስነዋል ብዬ አላስብም። በጨዋታው መሸነፋችን ኳሱን ላላየ ሰው ብዙም አሳማኝ አይደለም። ጥቃቅን ስህተቶችን ሠርተናል አቅማችንን ለማውጣት በጣም ጭንቀት ውስጥ ስለነበሩብን የተሻለ ነገር ለማሳየት ካለን ጉጉት አንጻር ያለንን 100% አውጥተን ባንጠቀምም የተሸነፍንበት መንገድ ለእኔ አላሳመነኝም።

\"\"

በሁለት አጋጣሚዎች የፍጹም ቅጣት ምት ይገባናል ጥያቄ ስላቀረቡበት ሁኔታ…

ያው ጨዋታ ሲደረግ በተለያየ መንገድ ታጠቃለህ ፤ ስታጠቃ ደግሞ ከቆመ ኳስ ፣ ከፍጹም ቅጣት ምት ከጨዋታ እንቅስቃሴዎችም ጎሎች ይገባሉ። ስለ ዳኛ ይሄ ነው ብሎ መናገር ተገቢ አይደለም ግን ሁለት ፍጹም ቅጣት ምቶች አጥተናል ብዬ አስባለሁ። በዋና ዳኛው እና በረዳቱ ያለው ግንኙነት ዛሬ ግልጽ አልሆነልኝም። ዋና ዳኛው ፊሽካ ለመንፋት ወደ አፉ ከትቶ ነበር ፤ ረዳቱ ደግሞ በቦታው ቆሞ ነበር። አህመድ የመጨረሻ ሰው ነው ከግብ ጠባቂ የተሰጠውን ኳስ ለማግባት ይዞ ሲሄድ ከኋላ በግልጽ ነው የተጠለፈው። ለምን ፍጹም ቅጣት ምት እንዳልተሰጠ አልገባኝም። ምናልባት በ ዲኤስቲቪ በሚታይበት ቦታ ቢሆን ይሄን የፍጹም ቅጣት ምት ይከለክላል የሚል እምነት የለኝም ፤ ግን ሆኗል። ከመቀበል ውጪ አማራጭ የለም።

ወደ ወራጅ ቀጠናው በድጋሚ ስለመግባታቸው…

ዕድሎችን በራሳችን ብንወስን በጣም ጥሩ ነበር። ይህን መወሰን የሚያስችል አቅምም ነበረን። ሜዳ ውስጥ ባለው ነገር የተወሰነ ግፊት ተደርጎብናል ብዬ አስባለሁ። የሰዎችን ዕድል ጠብቀን ነው መትረፍ የምንችለው። ምናልባት አዳማ ፕሮፌሽናል ክለብ እንደሆነ ከዚህ በፊት አይተናል። በተለያየ ጊዜ ውጤቶችን በራሱ መንገድ እንጂ በሰዎች ላይ ተንጠልጥሎ የማይሄድ ቡድን መሆኑን ስላየን ምናልባት አዳማ ወልቂጤን የሚያስጥል ከሆነ እኛ የመጨረሻውን ጨዋታ ጠንክረን በመሥራት እንሻገራለን የሚል እምነት አለኝ። ነገር ግን በሌሎች ላይ መንጠልጠላችን አስቸጋሪ ቢሆንም የምንችለውን ሁሉ እስከመጨረሻው እናደርጋለን።