ሪፖርት | ድሬዳዋ ከተማ በቢኒያም ጌታቸው ብቸኛ ጎል በሊጉ መቆየቱን አረጋግጧል

በሊጉ ለመቆየት ወሳኝ በነበረው ጨዋታ ድሬዳዋ ከተማ አርባምንጭ ከተማን 1-0 በመርታት በፕሪምየር ሊጉ ላይ መሰንበቱን ሲያረጋግጥ አርባምንጮች አጣብቂኝ ውስጥ ገብተዋል።

ሊጉ ለብሔራዊ ቡድን ከመቋረጡ በፊት አርባምንጭ ከተማዎች ለገጣፎን ከረቱበት ስብስባቸው አበበ ጥላሁን ፣ ቡታቃ ሻመና እና ተመስገን ደረሰን በአሸናፊ ፊዳ ፣ መሪሁን መስቀለ እና ኤሪክ ካፓይቶ ሲተኳቸው በወላይታ ድቻ ሽንፈት አስናግደው የነበሩት ድሬዳዋዎች በበኩላቸው ብሩክ ቃልቦሬን በዮሴፍ ዮሐንስ ፣ ኤልያስ አህመድን በአቤል አሰበ ለውጠው ቀርበዋል።

\"\"

በሊጉ ለከርሞ ለመሰንበት በእጅጉ ወሳኝ መልክ በነበረው የሁለቱ ቡድኖች ጨዋታ በተሻለ መነሳሳት ከተከላካይ ጀርባ በሚጣሉ ኳሶች ወደ ተጋጣሚ ሦስተኛው የሜዳ ክፍል በመድረሱ አርባምንጭ ከተማዎች ሻል ብለው ተስተውሏል። በዚህ የጨዋታ እንቅስቃሴያቸው የቀጠሉት አዞዎቹ አሸናፊ ኤልያስ ከግራ ወደ ውስጥ ጠለቅ ብሎ ከሳጥን ውጪ አክርሮ በመታት እና የግቡን የቀኝ ቋሚን ታካ በወጣች ኳስ ቀዳሚ ሙከራን ማድረግ ችለዋል። ሜዳው ምንም እንኳን ኳስን ለማንሸራሸር ምቹ ባይሆንም ድሬዳዋ ከተማዎች ኳስን በንክኪ መሐል ሜዳውን ተጠቅመው የጥቃት መነሻ የሆኑ ኳሶችን ለአጥቂው ቢኒያም በድግግሞሽ በማድረስ ግብ ለማስቆጠር ጥረት ያደረጉበትን ሒደቶች መመልከት ችለናል።

14ኛው ደቂቃ ላይ ከቅጣት ምት አብዱለጢፍ መሐመድ ወደ ጎል መቶ ይስሀቅ ተገኝ በያዘበት ወደ ተቃራኒ ክልል ለመጠጋት የሞከሩት ድሬዎች ዳዊት በጥሩ ዕይታ ለቢኒያም ሰጥቶት በግብ ጠባቂው ይስሀቅ ጥሩ ቅልጥፍና ከከሸፈችዋ አጋጣሚያቸው በኋላ በጨዋታው በጥራት ደረጃ ከፍ ያለችን ሙከራ በድሬዳዋ በኩል ተመልክተናል። 24ኛው ደቂቃ ላይ አቤል አሰበ በአርባምንጭ ተከላካዮች መሐል ለመሐሌ ያሾለከለትን ኳስ ቢኒያም ከግብ ጠባቂው ይስሀቅ ጋር አንድ ለአንድ ተገናኝቶ ወደ ጎልነት ለወጠው ተብሎ ሲጠበቅ ግብ ጠባቂውን ተጫዋቹ አሳቅፎታል። ጨዋታው ከነበረው የሜዳ ላይ ውጥረት አኳያ ጥቂት ሙከራዎችን ብቻ አስመልክቶን ያለ ጎል ወደ መልበሻ ክፍል አምርቷል።

\"\"

ጨዋታው ከዕረፍት ተመልሶ ሲቀጥል ቡድኖቹ በመጀመሪያው አጋማሽ ከነበራቸው የጨዋታ ቅርፅ ብዙም ያልተሻሻሉ እንቅስቃሴዎቻቸው ጎልተው የታዩበት ቢሆንም በአንፃራዊነት አርባምንጭ ከተማዎች በተሻጋሪ ኳስም ይሁን ኳስን በመያዘ ረገድ የተሻለ መልክን ተላብሰው በተለይ የአጋማሹ የመጀመሪያዎቹ ደቂቃዎች ላይ ብናስተውልም ሒደቱ ግን ወጥነት የጎደለው ነበር። 56ኛው ደቂቃ ላይ ከግቡ ጠርዝ ላይ ዮሴፍ ዮሐንስ ኳስን በእጅ መንካቱን ተከትሎ የተገኘውን የቅጣት ምት አሸናፊ ኤልያስ አክርሮ ወደ ጎል ሲመታው ፍሬው ጌታሁን በጥሩ ዕይታ ኳሷን ወደ ውጪ አውጥቷል። በእንቅስቃሴ ይበልጥ ይጉሉ እንጂ ሙከራዎችን በማድረጉ አርባምንጮች ድክመቶች ነበረባቸው። የተጫዋች ለውጥን እያደረጉ ከመጡ በኋላ ይበልጥ ወደ ጨዋታ ቅኝት ውስጥ እየገቡ የመጡት ድሬዳዋ ከተማዎች በጥሩ የሽግግር አጨዋወት ቢኒያምን በመጠቀም ጥቂት የማይባሉ ዕድሎችን አግኝተው ተስተውሏል። ድሬዎች በቀዳሚ ሙከራቸው 64ኛው ደቂቃ ቢኒያም አንድ ለአንድ ከይስሀቅ ጋር ተገናኝቶ የግብ ጠባቂው አስደናቂ ብቃት ኳሷን ከጎልነት ታድጓታል።

ሙከራ ካስተናገዱ ከሦስት ደቂቃዎች መልስ አርባምንጭ መልስ የሰጡበትን አጋጣሚ ፈጥረው ነበር። ከቀኝ በኩል ወርቅይታደስ አበበ በረጅሙ ወደ ጎል ሲያሻግር አህመድ ሁሴን በግንባር ገጭቶ የግቡ የላይኛው አግዳሚ ብረት መልሶበታል። ተጨማሪ የተጫዋች ለውጥን አድርገው ግብ ለማስቆጠር አልመው ሲንቀሳቀሱ የታዩት ድሬዳዎች ጨዋታው 70ኛ ደቂቃ ላይ እንደደረሰ ጎል አስቆጥረዋል። ተቀይሮ ወደ ሜዳ የገባው ኤልያስ አህመድ ከአርባምንጭ አማካዮች የተቋረጥን ኳስ አግኝቶ ያሻገረለትን ቢኒያም ጌታቸው የይስሀቅ ተገኝን ከግብ ክልል መውጣትን ተመልክቶ በአናቱ የለቀቃት ኳስ ከመረብ ተገናኝታ ድሬዳዋ ከተማን ወደ መሪነት አሸጋግሯል። 

ጎልን ማስተናገዳቸው በይበልጥ እያነቃቸው የመጡት አዞዎቹ የመጨረሻዎቹን አስር ደቂቃዎች ወደ አቻነት ሽግግር ለማድረግ አቀራረባቸውን በይበልጥ አሻሽለው ጥረት ማድረግ ጀምረዋል። በዚህም ከሁለተኛ ቅጣት ምት ቡታቃ መቶ ፍሬው ያዳነበት እንዲሁም አቡበከር ሻሚል ከሳጥን ውጪ መትቶ በድጋሚ ግብ ጠባቂው ፍሬው በቀላሉ ከያዘበት ሙከራቸው በኋላ ጨዋታው 1ለ0 በሆነ የብርቱካናማዎቹ ድል ፍፃሜውን አግኝቷል። ውጤቱን ተከትሎ ድሬዳዋ በሊጉ መሰንበቱን ሲያረጋግጥ በአንፃሩ አርባምንጭ የመጨረሻውን ጨዋታ ለመጠበቅ ተገዷል።